ወደ ኋላ የሚመልሱ ሃሳቦችን ለማሸነፍ ምን እናድርግ?

በሕይወት ላይ ለስኬትና ውድቀት የሚኖረን በጎ እሳቤ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በተለይ እምነታችን ግባችንን ለማሳካት በእጅጉ ጠቃሚ ነው። በተቃራኒው በራስ መተማመን የሌለንና ያለን እምነት ዝቅተኛ ከሆነ የምንፈልገውን ለማሳካት ይቸግረናል። በመሆኑም በማንኛውም ሙያ፣ ሥራና የሕይወት መንገድ ላይ ወደ ተግባር ከመግባታችን አስቀድመን አስተሳሰባችንን ማረቅ ተገቢ መሆኑን መገንዘብ አለብን።

ለመሆኑ በራሳችን ላይ ያለንን አስተሳሰብ እንዴት ማስተካከል እንችላለን? በነገሮች ላይ ያለን አስተሳሰብ ወደ ኋላ የሚጎተተን እንዳይሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ በዛሬው “የመጋቢ አዕምሮ “አምድ ላይ እንደሚከተለው አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ወድጃለሁ።

ስኬታማ እንዳንሆን ምን ያግደናል?

በሕይወታችን ላይ ስኬታማ ለመሆን እንዳንችል ብዙ አሉታዊ ነገሮች እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። ይህንን እክል ተሻግሮ ውጤታማ ለመሆን ደግሞ በራስ መተማመን እና በጎ እሳቤን መገንባት ይኖርብናል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ወጣቶች በሕይወት የሚሹትን ነገር በቀላሉ ለማድረግና ለመራመድ ሲቸገሩ እናስተውላለን። ህልማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ሚሊዮኖች ቢኖሩም ከእነዚህ ውስጥ ጥቁቶቹ ብቻ ከግባቸው ይደርሳሉ። በዚህ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ በተለይ ወጣቶች በአንድ ቦታ ላይ ተወስነው እንዲቀሩና ደስተኛ ሕይወት እንዳይመሩ ምክንያት ይሆናል።

የሥነ ልቦናና የሕይወት ክህሎት ምሁራን ይህንን መሰል ስሜት (በራስ መተማመን መሸርሸር) በወጣቶች የሚስተዋለው አስተሳሰባቸውን እና በራሳቸው ላይ ያለውን እምነት ስለሚገድቡት እንደሆነ የሠሩትን ጥናቶች ዋቢ በማድረግ ይገልፃሉ። ይህንን መሠረት በማድረግ ወጣቶች በራሳቸው ላይ ያላቸውን እምነት መገደብ ከስኬታማነት እንደሚያስቀራቸውና ወደ ኋላ እንደሚጎትታቸው ያስረዳሉ። በውጤቱም ራሳቸውን እንዲጠራጠሩ እና አዳዲስ ነገሮችን እንዳይሞክሩ የሚያደርጉ እሳቤዎችን እንዲያጎለብቱ ምክንያት ይሆናል።

በአንድ ቦታ ላይ ተወስኖ የመቆየት ስሜትን የሚያዳበሩና ስኬታማነት የሚርቃቸው ወጣቶች ከዚህ አሉታዊ ስሜት መውጣት ይችላሉ። ይሁን እንጂ በቅድሚያ በራሳቸው ላይ ያላቸውን እምነት ወይም መገደብ መለወጥናና በአዎንታዊ አስተሳሰብ መሞላት ይኖርባቸዋል። ይህንን መሰል ቸግር መፍታት የሚጀመረው ቅድሚያ በነገሮች ላይ የሚኖረንን እሳቤ በማወቅ እና እነሱን ለማሸነፍ ርምጃዎችን በመውሰድ ነው።

ምን ማረግ አለብህ***

ገደብ ያለው እምነት አንድ ነገር ማሳካት እንደማትችል እንዲሰማህ የሚያደርግ ማንኛውም ሃሳብ ነው። ለምሳሌ “ይህን ፈተና ለማለፍ ብለህ አይደለሁም” ወይም “ንግድ ለመጀመር ገንዘብ የለኝም” ብለህ ልታስብ እና አዕምሮህን በአሉታዊ እሳቤ ልታጨናንቀው ትችላለህ። ነገር ግን እነዚህ ሃሳቦች ሁል ጊዜ እውነት አለመሆናቸውን ማወቅ ይኖርብሃል። ስለራስህ ያዳበርከው እምነት አሊያም እሳቤ በአእምሮህ ውስጥ ስለሚደጋገሙ እውነተኛ እንደሆኑ አምነህ ልትቀበላቸው ትችል ይሆናል።

እነዚህ አስተሳሰቦች በጊዜ ሂደት አቅምህን እንዳታውቅ አሊያም የምትፈልገው ስኬት ላይ እንዳትደርስ ሊያግዱህ ይችላሉ። በዚህ አሉታዊ አመለካከት የተነሳ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ይህን ፈተና ይጋፈጣሉ። ድህነት፣ የትምህርት እጦት እና የማህበረሰብ ጫናዎች ደግሞ በውስጥህ የሚዘሩትን አሉታዊ እምነቶች የበለጠ ጠንካራ ያደርጋቸዋል። መለወጥ አልችልም አሊያም ደካማ ነኝ ብለህ በራስ መተማመንህ ዝቅ እንዲል ምክንያት ይሆናሉ። እውነታው ግን ከዚህ ተቃራኒ መሆኑን ማወቅ አለብህ። ፈተናዎቹን ተጋፍጠህ፤ አሉታዊ እሳቤዎችን ቀይረህ ህልምህን መኖር ትችላለህ።

ለውጥ ሁሌም ይቻላል። አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ተመልከት ህልሙን ከዳር ለማድረድስ ለአዕምሮው አሉታዊ የሆነውን ‹‹አይቻልም›› የሚል እሳቤ ሳይሆን ‹‹ይቻላል›› የሚል በጎ አመለካከትን ነበር የነገረው። በውጤቱም በዓለማችን ላይ እውቅ አትሌቶች መካከል ቁጥር አንድ ከመሆን ባሻገር በንግድ ሕይወቱም ስኬታማ መሆን ችሏል።

ከአሉታዊ አስተሳሰብ ነፃ ለመውጣት የመጀመሪያው ርምጃ ያለህን ውስን እምነት መለየት ነው። ለሃሳብህ ትኩረት ስጥ። “ስለ ራሴ ምን አምናለሁ?” ብለህ ራስህን ጠይቅ። ወይም “ስለ የወደፊት ሕይወቴ ምን አምናለሁ?” እነዚህን ሃሳቦችህን በማስታወሺያ አሊያም ዲያሪ ላይ ጻፍ። ለምሳሌ “በአደባባይና ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ መናገር አለችል” ወይም “በአስተዳደጌ የተነሳ ሊሳካልኝ አይችልም” የሚል አሉታዊ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል። ይህ እምነትህ በስኬታማነትህ ላይ ጠላ የሚያጠላ አሉታዊ አስተሳሰብ ነው።

እነዚህን እምነቶችና አመለካከቶችህን አንዴ ከለየሃቸው እዳው ገብስ ነው (ለችግሮችህ መፍትሄ ለመስጠት በእጅጉ ቀላል ነው)። ቀጣዩ ርምጃ መሆን ያለበት ደግሞ በውስጥህ ለዓመታት የተከማቹት እነዚህ አስተሳሰቦች ምን ያክል እውነት እንደሆኑ መፈተሽ ነው። በመሆኑም “ይህ እምነት አሊያም አመለካከቴ ምን ያክል እውነት ነው?” ብለህ ራስህን ጠይቅ።

ለምሳሌ በአንድ ነገር ጎበዝ እንዳልሆንክ ካሰብክና በተደጋጋሚም አስተሳሰብህ የሚፈትንህ ከሆነ ጥሩ ያደረክበት ወቅት ላይ ብቻ አተኩርና በዚያ ዙሪያ አዕምሮህ እንዲያስብ አድርግ። ምናልባት ከዚህ በፊት በአነስተኛ ስብሰባ ውስጥ አሊያም በቡድን ስብስብ ላይ በልበ ሙሉነት ተናግረህ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባት አስቸጋሪ የሚመስለውን ችግር ፈትተህ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ምሳሌዎች የሚያሳዩት አሉታዊ እሳቤህ አሊያም በራስ የመተማመን ችግርህ (እምነትህ) ሙሉ በሙሉ እውነት እንዳልሆነ ነው።

ሌላው በራስ መተማመንህን የሚጨምር ነገር ከስኬታማ ሰዎች ምክሮችን ማግኘት ነው። ለምሳሌ እምነትህን የሚያጠነክሩልህ ወይም አሉታዊ አስተሳሰብህ የተሳሳተ መሆኑን የሚያስረዱህና አንተ ከዚህ የተሻለ ማድረግ እንደምትችል በመንገር የሚያበረታቱህ ሰዎች ጋር ደጋግመህ መገናኘትና መነጋገር አለብህ። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ስኬታማ ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ስኬታማ መሆን ችለዋል። እነዚህ ግለሰቦች በጥቂቱ ቢጀምሩም ትልቅ ስኬት አግኝተዋል። አንተም ከእነርሱ ልትማር ይገባል። በመሆኑም ምክሮችን ለማግኘት ስለ ጥረታቸው፣ ስለደረሱበት ስኬት እና ስለ ጉዟቸው ጠይቃቸው። እነሱም በአንድ ወቅት ልክ እንዳንተ በራሳቸው ላይ ጥርጣሬ እንደነበራቸው እና ፈተናዎች እንዳጋጠሟቸው በእርግጠኝነት ይነግሩሃል። ነገር ግን ጥርጣሬያቸውና በራስ መተማመን የማጣት እሳቤ ወደ ኋላ እንዳልጎተታቸው ትገነዘባለህ። ከእነዚህ ሰዎች ተሞክሮ መማር ስለራስህ በተለየ መንገድ እንድታስብ ሊያነሳሳህ ይችላል።

በተጨማሪ በሕይወት ጉዞህ ላይ ትናንሽ ርምጃዎችን መውሰድም አስፈላጊ መሆኑን ተገንዘብ። ውስጥህ ያለው እሳቤና እምነትህ ገንዘብ መቆጠብ እንደማትችል ደጋግሞ የሚነግርህ ከሆነ ያንን ችላ ብለህ በየሳምንቱ በትንሽ መጠን በመቆጠብ ጀምር። ማወቅ ያለብህ አንድ እውነት ከጊዜ በኋላ ይህ ትንሽ ልማድ ያድጋል። እናም ከዚህ ቀደም በውስጥህ ሰርፆ የነበረው እምነት አሊያም እሳቤ የተሳሳተ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ያስችልሃል። በተመሳሳይ በተሠማራህበት አሊያም ልትሠማራ ባሰብክበት ሙያ ላይ ያለህ ችሎታ ጥሩ እንዳልሆኑ ካሰብክ በየቀኑ በየጊዜው እራስህን ማለማመድ (አጫጭር ሥልጠናዎችን መውሰድ) ጀምር። ብዙ በተለማመድክና የእውቀት አድማስህን ባሰፋህ ቁጥር በራስ የመተማመን ስሜት ከምንጊዜውም በላይ እያደገ ይመጣል። በዚህ ወቅት የሚጎትትህን እሳቤ ማሻሻል እና ወደ ስኬት መስመር ለመግባት ትችላለህ።

አካባቢያችን አስተሳሰባችንን (ለራሳችን ያለንን እምነትን) በመቅረጽ ረገድም ትልቅ ሚና ይጫወታል። ተስፋ ከሚያስቆርጡህ ሰዎች ጋር አብዛኛውን ጊዜህን የምታሳልፍ ከሆነ አሉታዊና ገደብ የለሽ እምነትህ እየጠነከረ ይሄዳል። በመሆኑም በምትኩ ባንተ እውቀት፣ ችሎታና የማድረግ አቅም ከሚያምኑ እና በሕይወት ልትደርስባቸው የምታስባቸውን ህልሞችህን ከሚደግፉ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ ሞክር። አዎንታዊ ተጽእኖዎች እራስህን በተሻለ መልኩ መመልከት እንድትችል ይረዳሃል። በዙሪያህ ደጋፊ ሰዎች ከሌሉ ደግሞ ተመሳሳይ ህልም ያላቸው ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን አሊያም ማህበረሰቦችን በመፈለግ ለመቀላቀል ሞክር። ያን ጊዜ ያለ ጥርጥር ውጤቶቹን ትመለከታቸዋለህ።

ደጋግመህ ሞክር

‹‹አልችልም›› ወይም ‹‹አይሆንልኝም›› የሚሉ አስተሳሰቦች ቀደም ሲል ከደረሰብን ውድቀት ወይም አለመሳካት ሊመነጩ ይችላሉ።

አንዳንድ ጊዜ በራሳችን ያለንን እምነትና መተማመን መገደብ የምንጀምረው ካለፉት ልምዶች ተነስተን ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ጊዜ ብቻ ሞክረህ ካልተሳካህ ሁል ጊዜ እንደምትወድቅ እንድታስብ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ እሳቤ ትክክል አይደለም። በአንድ ወቅት ሞክረህ መውደቅህ ሊያስተምርህ እንጂ ተስፋ ሊያስቆርጥህ አይገባም። እያንዳንዱ ስኬታማ ሰው ብዙ ጊዜ ወድቋል። ስኬታማ የሚያደርጋቸው አንዱ ቁም ነገር ተስፋ አለመቁረጣቸው ነው። ከስህተታቸው ተምረው ደጋግመው መሞከራቸው ግባቸውን እንዳይስቱና ያለሙት የስኬት ማማ ላይ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗቸዋል። አንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ። በውድቀቱ ላይ ከማተኮርህ ይልቅ ከዚያ ምን እንደተማርክ አውጠንጥን። በሚቀጥለው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እቅድህን ለማሳካት ካለፈው ስህተትህ ትምህርት ውሰድ። ያኔ የሄድክበትን መንገድ መድገም ሳይሆን ማሻሻልና ዳግም መሞከርን ምረጥ።

አስተሳሰብህን አዎንታዊ ለማድረግ ሌላኛው ቁልፍ ትምህርት ነው። እንደተቸገርክ እና ከዚህ ሁኔታ ውስጥ በቶሎ ለመውጣት ስታልም በተቻለህ መጠን እራስህን በእውቀት ለማስታጠቅ ሞክር። ሥራ ማግኘት እንደማትችል ካሰብክ ስለ ሥራ እድሎች ሁኔታ አውጠንጥን። ከማህበራዊ ሚዲያ፣ በይነ መረብ እና ሌሎች ፕላትፎርሞች በየጊዜው ግንኙነት እና ችሎታህን ለማሻሻል እንድትችል አጫጭር ሥልጠናዎችን በመውሰድ ተማር። የበለጠ ባወቅክ መጠን በራስ የመተማመን ስሜትህ እያደገና በእጅጉ እየጎለበተ ይሄዳል። በኢትዮጵያ ውስጥ እራስን ለማሻሻል፣ ለመማር እና ለማደግ የሚረዱ የነፃ መድረኮች አሉ። በዎርክሾፖች እና የማህበረሰብ ፕሮግራሞች ላይ ተሳተፍ። ለምሳሌ በምትኖርበት ወረዳ አሊያም አካባቢ ላይ የሚገኙ መድረኮችን ተጠቀምባቸው።

የብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አንዱ ፈተና ‹‹እድሎች ውስን ናቸው›› ብሎ ማመን ነው። ምንም እንኳን ሀገሪቱ ካላት ኢኮኖሚ አንፃር ለወጣቶች ያለው እድል እምብዛም ሊሆን ቢችልም በእጥረቱ አሊያም በአሉታዊ እሳቤው ላይ ማተኮር ግን ተገቢ አይደለም። በምትኩ ባለህ ውስን ነገርም ቢሆን እንዴት ልትጠቀምና ልታድግ እንደምትችል ደጋግመህ ማሰብና መፍትሄ መፈለግ ይኖርብሃል። ለምሳሌ የእጅ ስልክ (ስማርትፎን) ካለህ በኢንተርኔት ከማህበራዊ ሚዲያ አዳዲስ ክህሎቶችን ለመማር ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ነፃ ጊዜ ካለህ በበጎ ፈቃደኝነት ወይም በግል ፕሮጀክቶች ላይ ለመሥራት ልትጠቀምበት ትችላለህ። እነዚህ ትናንሽ የሚመስሉ ግን ጠንካራ አስተሳሰብን በውስጣችን ለመዝራት አቅም ያላቸው ድርጊቶች አዳዲስ የስኬት በሮችን ሊከፍቱልህ እንደሚችሉ አትጠራጠር።

እኔ (የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ) የኢትዮጵያ ወጣቶች ትልቅ አቅም አላቸው ብዬ አምናለሁ። አሉታዊ አስተሳሰብህንና እምነትህን በመለየት እንዲሁም ይህንን ተቃውመህ እራስህን ለመለወጥ በመሞከር ውጤት ማምጣት ትችላለህ ብዬ አስባለሁ። ከትልልቅ ሳይሆን ከትናንሽ ርምጃዎች ጀምር። በእርግጠኝነት ለራስህ ብሩህ የወደፊት ጊዜ መፍጠር ትችላለህ። ሁሌም አንድ ነገር አስታውስ፤ ብቸኛው የስኬትህ ጠላትና ገደብ በአዕምሮህ ውስጥ ያስቀመጥካቸው አሉታዊ እሳቤዎች ናቸው። በመሆኑም ‹‹ከዛሬ ጀምሮ እነዚህን እኩይ እምነቶች›› መለወጥ አችላለሁ ብለህ ጉዞህን ጀምር። ይሳካልሃል!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You