
ርብቃ ተካልኝ እና ባለቤቷ ዮሐንስ ትዳር ከመሠረቱ አራት አመት ያህል ጊዜን አስቆጥረዋል። አስቀድመው ይኖሩበት ከነበረው የሽሮ ሜዳ ሰፈር ለቀው ወደ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አያት አካባቢ ወደተከራዩት አዲሱ ቤታቸው የገቡት ርብቃ የመጀመሪያ ልጇን ከወለደች በኋላ ነው። አሁን የገቡበት ከዚህ በፊት ይኖሩበት ከነበረው አንፃር በስፋትም ሆነ የጋራ መኖሪያ አፓርትመንት በመሆኑ የተሻለ ነፃነት ያለው በመሆኑ ወደውታል ።
ርብቃም ሆነ ባለቤቷ የየዕለት ተግባራቸውን በሥራ ከቤት ውጪ የሚያሳልፉ ቢሆንም የመጀመሪያ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ ግን የዮሐንስ እና የርብቃ እናት እየተፈራረቁ እናቲቱን የማረስ እና የወሊድ ፈቃድ ጊዜዋ አልፎ ወደሥራ በምትመለስበት ጊዜ የርብቃ እናት አብረዋቸው ለተወሰነ ጊዜ በመኖር የልጅ ልጃቸውን ይዘው ይቆይዋት ነበር ። ርብቃ ልጇ ናሆም ምንም እንኳን ሁለተኛ ልጇ ቢሆንም እናት ናትና በሥራ ቦታዋ ልቧ እንደሌላው ጊዜ አርፎ ሊቀመጥላት አልቻለም። ልጇን ከእናቷ ጋር ትታው መምጣቷ ጥቂት እረፍት ቢሰጣትም የልጇን ደኅንነት እና ሁኔታ በየሰዓቱ እየደወለች ታጣራለች:: ሥራዋን አስቀድማ በምትጨርስበት ጊዜም በጊዜ ወደቤቷ በመሄድ የልጇን ሁኔታ ትከታተላለች።
ርብቃና ባለቤቷ ሥራቸው ለኑሯቸው የሚያስፈልጋቸውን እና ለወደፊት የሕይወት እቅዳቸውን ለማሳካት የሚያግዛቸው በመሆኑ ለተወሰኑ ዓመታት ርብቃም በምትሠራው ሥራ ላይ መቆየቷን በጋራ ተስማምተው የወሰኑት ጉዳይ ነው:: ልጃቸውን ናሆምን ምንም እንኳን በርብቃ ሥራ ቦታ አቅራቢያ የሚገኝ የሕጻናት መዋያ ብታስገባውም በንጽሕና ጉድለት ምክንያት ልጇ ናሆም በተደጋጋሚ በመታመሙ አንድ የቤት ውስጥ አጋዥ ለመቅጠር ትወስናለች:: ከምትኖርበት አካባቢም ደላላ ቤት በመሄድ ሠራተኛ ትቀጥራለች::
ዘውዲቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በቤት ውስጥ ሠራተኝነት ስትሠራ መቆየቷ እና ከሰዎች ጋር ያላት ተግባቦት መልካም በመሆኑ ርብቃ ከዘውዲቱ ጋር ቶሎ በመግባባት ሥራውን በአግባቡ እንደምታከናውንላት በመተማመን የቤተሰቡ አንድ አባል አድርጋታለች:: ዘውዲቱ ከቤት ውስጥ ካለ ሰው ጋር በቶሎ መግባባት፣ ሕጻናትን በጥሩ ሁኔታ መያዝ ላይ ጥሩ ልምድ ያላት ትመስላለች::
በቤት ውስጥ ካለው ሦስት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ ከቀሩት ገና አፉን በመፍታት ላይ ካለው ሕፃን ናሆም ጋር በቶሎ ለመግባባት ችለዋል:: ርብቃም ዘወትር ወደሥራ ከመሄዷ በፊት ለልጇ የሚሆነውን እያንዳንዱን ምግብ አዘጋጅታ እና ለዘውዲቱ በማሳየት ወደሥራዋ ትሄዳለች ::
ባለቤቷ ዮሐንስ የራሱ የግል መኪና ያለው በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ከባለቤቱ ርብቃ ጋር ወደሥራ አብረው የሚወጡ ሲሆን ርብቃ በምታመሽበት ወቅት ተጠባብቀው ወደቤታቸው ይገባሉ:: ርብቃ የልጇ ናሆም አዲሷን የቤት ውስጥ አጋዥ በቶሎ መላመዱ በጥቂቱም ቢሆን እረፍት ሰጥቷታል:: ምክንያቱም ልጇ እንዴት ዋለ የሚለውን ነገር ላይ መጨነቅ ምግብ መብላት አለመብላቱን በየሰዓቱ እየደወለች የማጣራቱ ነገር ቀነስ ብሎላታል::
ዘውዲቱም ሕፃን በመያዝ እና የቤቱን ነገር መቆጣጠር ላይ ጥሩ ስትሆን ርብቃን ምቾት የነሳት ነገር ግን ዘመዶቼን ላገኝ ነው በሚል በእረፍት ቀኗ ወጥታ የምትቆየውና የምታመሸው ነገር፤ በአካባቢው ካሉ ርብቃም ሆነ ባለቤቷ ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ረጅም ሰዓት ስታወራ መመልከታቸው ምቾት አልሰጣቸውም:: ጉዳዩን እርስ በእርሳቸው ከማውራት በዘለለ ግን ለዘውዲቱ ስለጉዳዩ ምንም ያሏት ነገር የለም ::
ያልታሰበ ዱብ ዕዳ
እለቱ ቅዳሜ ቀን በመሆኑ ርብቃም ሆነ ባለቤቷ በቤት ውስጥ ናቸው:: ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጊዜ ለማሳለፍ እንግዶችን ቤታቸው ጠርተው የቤተሰብ ጊዜን በማሳለፍ ላይ ናቸው:: ዘውዲቱም ለእንግዶቹ ተብለው የተዘጋጁ ምግቦችን አቅርባ እና አስተናግዳ እንደባሕሉም ቡናዋን አፍልታ ሥራዋን አጠናቃለች:: በሌላው ጊዜ ከእሷ ጋር መዋልን የለመደው ናሆምም ከስሯ ስለማይጠፋ ቤት ውስጥ እያለቀሰ እና እየተነጫነጨ በሚያስቸግራት ጊዜ ማስቲካ እንግዛ በማለት ይዛው ወጣች::
ርብቃም ሆነ ባለቤቷ አካባቢው ሱቅ በቅርበት የሚገኝበት ስፍራ በመሆኑ ርቀው አይሄዱም በሚል ወደጨዋታቸው ተመልሰዋል:: ቤት ውስጥ ብዙ ሰዎች ያሉ በመሆናቸው ምንም እንኳን እርስ በእርስ ማውራቱ እና መጫወቱ በርከት ቢልም ርብቃ ግን መለስ እያለች ወደበር መመልከቷ አልቀረም:: በጨዋታ መሐል ድንገት የስልኳን ሰዓት የተመለከተችው ርብቃ ግን ከተቀመጠችበት ቦታ ደንገጥ ብላ ወደ ውጪ እንድትወጣ አደረጋት:: ዘውዲቱ ናሆምን ማስቲካ እንግዛ በማለት ይዛው ከወጣች ወደ 2 ሰዓት ያክል አልፏል:: በፍጥነት ከቤቷ የወጣችው እናት ግን በአካባቢው ልጇንም ሆነ የቤት አጋዧን ማየት አልቻለችም:: በቅርብ ወዳለው ሱቅ በመሄድ ብትጠይቅ አየን የሚል ሰው ግን አልነበረም:: ለጥቂት እየተፈጠረ ያለው ነገር እውነት መሆኑን ለማመን የተቸገረችው ርብቃ ልጇ የት ሄዶ ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ብትሞክርም መፍትሔ ግን አላገኘችም ::
ቀኑ ወደመምሸቱ እየተጠጋ ነው:: እረፍት ቀን በመሆኑ እምብዛም እንቅስቃሴ አይታይም:: ጭር ከማለቱ ጋር ተያይዞ ርብቃን ልጇን የሰወረው አንዳች ነገር ምን እንደሆነ ለማሰብ ከበዳት:: እንደሌላው ጊዜ ከሕጻናት ጋር ሊጫወት ይወጣል እንዳይባል በየቤቱ እየገባች ለመጠየቅም ድፍረት አጣች:: በአካባቢው ሲያልፉ አፓርትመንቱ መውጫ ላይ ያለ ጥበቃን እንደ አንድ የመፍትሔ አማራጭ አድርጎ የጠየቀው አባት ዮሐንስ ምንም መረጃ እንደሌላቸው እና ብዙ ሕጻናት ይወጡ ይገቡ ስለነበር መለየት እንደማይችል ነገራቸው::
በአፓርትመንቱ መግቢያ ላይ የርብቃና የባለቤቷን እንዲሁም የቤተሰቡን ወዲያ ወዲህ ማለት የተመለከቱት አንዳንድ ሰዎች ጉዳዩን ጠጋ ብለው ሲያጣሩ እና የሕጻናት መጥፋት እንደሆነ ሲያውቁ በቦታው ያለው የሰዎች ቁጥር መጨመር ጀመረ:: ታዲያ ሁሉም ሰው የየራሱን ሀሳብ ይሰነዝራል፤ አንዳንዱ መንገድ ጠፍቶባቸው ሊሆን እንደሚችል ሲናገር፤ ሌሎች ደግሞ ምናልባት ሆን ብላ ይዛው ጠፍታ እንዳይሆን በመገመት የእናትና እና አባትን የልብ ትርታ ከፍ ያደርጉት ይዘዋል:: እናት አንዱንም ምክንያት ለማመን ፍቃደኛ አይደለችም ምክንያቱም ልጇ ናሆም ገና አፉን እንኳን ያልፈታ የሁለት ዓመት ከ 11 ወር ልጅ ነው::
ድፍረት በየፈርጁ
ቀኑ ወደመምሸቱ ተጠጋ:: አይደለም አፉን ያልፈታ ሕጻን ልጅ ይቅርና ዙሪያ ገባውን የሚያውቅ ትልቅ ሰው ራሱ ለመንቀሳቀስ በማይደፍርበት ሁኔታ እየመሸ መጣ:: በድንገት ግን የናሆም አባት ዮሐንስ ስልክ አንድ የማያውቀው ቁጥር ተደወለለት:: ርብቃ የልጇን ነገር የሚያውቅ ቢሆን ደስታዋ ነው፤ ዮሐንስ ፀጥታ ለማግኘት ወደ አንድ ቦታ ጠጋ በማለት ስልኩን አነሳው፤ ደዋዩ ሰው ማንነቱን ካጣራ በኋላ የልጁ የናሆም ሕይወት በእጁ እንደሚገኝ እና 10 ሚሊዮን ብር የማይከፍል ከሆነ ግን በሕይወት እንደማያገኘው ነገረው:: ይህ ሌላ ዱብዕዳ መፍትሔ ለመፈለግ እንኳን ዕድል የሚሰጥ አልሆን አለ::
ከአቅም በላይ ሲሆን
ጉዳዩ ጠንከር ያለ እና እንደተባለውም ሠራተኛዋ ዘውዲቱ መንገድ ጠፍቶባት አለመሆኑን ሲረዳ ጉዳዩ ላይ የሕግ አካላት ርዳታ እንደሚያስፈልግ በማመን ወደ አቅራቢያው የለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ጉዳዩን አስረዱ::
ፖሊስ ጉዳዩ ጥቅምት ስድስት ቀን 2015 ዓ.ም ላይ ከቀኑ በግምት 10 ሰዓት በክፍለ ከተማው አያት ጣዕመ ዳቦ በቤት አካባቢ ሁለተኛ ተከሳሽ ያላትን ዘውዲቱ ገብሬ በሠራተኝነት ትሠራበት ከነበረው ቤት እድሜው የሁለት አመት ከ11 ወር የሆነ ሕፃን ናሆም ዮሐንስን ማስቲካ ልግዛለት በማለት አታልላ ይዛው ከቤት ከወጣች በኋላ ከሌሎች አባሪዎቿ ሦስት ተከሳሾች ጋር በመሆን ልጁን ወደሌላ ቦታ ይዘው በመሄድ በተደጋጋሚ ወደ አባት ዮሐንስ ስልክ ላይ በመደወል ገንዘብ ካላመጣችሁ ልጃችሁን እንገድለዋለን በማለት ሲያስፈራሯቸው ፖሊስ ጉዳዩ ላይ የተለያዩ ማጣራቶችን በማድረግ እና ወደ አባት አቶ ዮሐንስ የሚደረጉ የስልክ ልውውጦችን ጥንቃቄ በመከታተል ሕጻን ናሆምን ከሠራተኛዋ ተከሳሽ ዘውዲቱ ገብሬ እና ከሌሎች አባሪዎቿ ጋር በኦሮሚያ ክልል ኢጀሬ ወረዳ አዲስ ዓለም ከተማ ጨረታ ሰፈር በሚገኘው 1ኛ ተከሳሽ አስቀድሞ በተከራየው ቤት ውስጥ በቁጥጥር ሊያውል ችሏል ::
የወንጀሉ ዝርዝር
በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ መሪጌታ ምስጢሩ ይግዛው፣ 2ኛ ዘውዲቱ ገብሬ እና 3ኛ ብሩክ ቸኮል የተባሉት ተከሳሾች ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 10፡00 ሲሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አያት ጣዕመ ዳቦ ቤት አካባቢ 2ኛ ተከሳሽ በቤት ሠራተኛነት ተቀጥራ ስትሠራበት ከነበረው ቤት ሕፃን ጠልፈው ብር ለመቀበል ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመስማማት ዕድሜው ሁለት ዓመት ከ11 ወር የሆነውን ሕፃን ናሆም ዮሐንስን ማስቲካ ልግዛለት በማለት አታልላ ይዛው ከቤት ከወጣች በኋላ በአካባቢው ይጠብቋት ከነበሩ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመገናኘት ሕፃኑን ይዘው ወደ ኦሮሚያ ክልል ኢጀሬ ወረዳ አዲስ አለም ከተማ ጨረታ ሰፈር በሚገኘው 1ኛ ተከሳሽ አስቀድሞ በተከራየው ቤት ወስደው ይደብቁታል::
1ኛ ተከሳሽም ለሕፃኑ ወላጆች ስልክ በመደወል 10 ሚሊዮን ብር ክፈሉና ልጁን ውሰዱት አለበለዚያ እንሸጠዋለን፣ ኩላሊቱ ሱዳን ይፈለጋል፣ ጎንደር አዞዞ ተራራ ላይ ሄዳችሁ አስከሬኑን ውሰዱ በማለት፣ 2ኛ ተከሳሽም ቶሎ ብሩን ክፈሉ ልጁን መተማ ሊወስዱት ነው እኔንም እጄን ቆርጠውኛል በማለት፣ 3ኛ ተከሳሽም የግል ተበዳይ ወላጅ አባት ጋር ስልክ በመደወል አስፈራርቶ ገንዘቡን ለመቀበል እየተደራደሩ በፀጥታ አካላት በተደረገ ጥረት በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል:: በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላም በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ 32/1/ሀ/፣ 590/1/ለ እና /2/ሠ መሰረት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ክስ አቅርቦባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል::
ውሳኔ
ተከሳሾች በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ክስ አቅርቦባቸው ክርክር ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ማስረጃቸውን አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም የቀረበባቸውን ማስረጃ መከላከል ባለመቻላቸው ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ መሠረት የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ መሪጌታ ምስጢሩ ይግዛው በ7 ዓመት ፅኑ እስራት፣ 2ኛ ተከሳሽ ዘውዲቱ ገብሬ በ6 ዓመት ፅኑ እስራት እና እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ ብሩክ ቸኮል በ5 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም