
‹‹ኑክሌር›› የሚለው ስም ሲጠራ በብዙዎቻችን አዕምሮ ውስጥ ብቅ የሚለው ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያ ነው:: በተለይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1945 አሜሪካ በጃፓን ሂሮሽማና ናጋሳኪ ላይ የጣለችው አውቶሚክ ቦምብ እና ያስከተለው አሰቃቂ እልቂት በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ታትሞ ቀርቷል። በሌላ መልኩ በዚህ ጦር መሣሪያ የበለፀጉ ሀገራት ሃያልነታቸውን ለማሳየት የሚያደርጉት ዘመናዊ የኑክሌር ተሸካሚ የጦር መሣሪያና ማብላያ ጣቢያዎች ግንባታ የኑክሌር ሃይልን ከሌሎች በጎ ጉዳዮች ጋር እንዳናያይዘው አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮብናል።
ዛሬ ኑክሌርን በተመለከተ የምናነሳው ጉዳይ ግን ፍፁም አሉታዊ ጎን የለውም። በተቃራኒው ኑክሌር ለሰው ልጆች ጥፋት ሳይሆን ለጤናቸው መጠበቅ ያለውን ፋይዳ በዝርዝር ለመመልከት ወድደናል። ኑክሌር ለውድመት ብቻ ሳይሆን ለደህንነትም እንደሚውል እናስቃኛችኋለን::
ለመሆኑ ምን ያህሎቻችን ነን ስለ ኑክሌር ሕክምና የምናውቀው? በተለይ በኢትዮጵያ እምብዛም ተግባራዊ አለመሆኑ ብዙዎች በሚገባ ያውቁታል ለማለት ያስቸግራል:: በዚህ ምክንያት ዛሬ በ ‹‹ማህደረ ጤና›› የሕክምና ዘዴው ምን እንደሚመስል፤ እንዴት እንደሚተገበር፤ ጥቅሙና በሀገራችን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በውስጥ ደዌ ሕክምና ክፍል የኑክሌር ሕክምና ክፍል የኑክሌር ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ቤቴልሔም ወርቁን አነጋግረናል::
በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን የህክምና ዘዴዎች ፍፁም በተራቀቀ ቴክኖሎጂና መንገድ ተግባራዊ የደረጋሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሰው ልጆችን ጤና አጠባበቅ እያቀለሉት መጥተዋል:: በዚህ ምክንያት ረቂቅ የሚባሉ ህክምናዎች ለፈውስ ፍፁም አስቸጋሪ የተባሉትን በሽታዎች ሁሉ መፍትሄ ሲያገኙላቸው ተመልክተናል። ይህንን መሰል አገልግሎት ለመስጠት ከሚያስችሉ የሕክምና ጥበቦች አንዱ የኑክሌር ሕክምና ይገኝበታል።
የኑክሊር ሕክምና ምንነት
የኑክሊር ሕክምና ጨረር አመንጪ መድኃኒቶችን (radiopharmaceutical) በተለያየ ዘዴ ለታካሚው በቀጥታ በመስጠት አብዛኛው የሰውነት ክፍሎችን ለመመርመር የሚያስችለን የሕክምና ዘዴ ነው። ይህ የምርመራ ዓይነት በሌሎች የሕክምና መመርመሪያ ዘዴዎች በቤተሙከራ /Laboratory/፣ በራዲዮሎጂ /ሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ … ወዘተ/ ምርመራዎች ማግኘት የማንችላቸውንና የተደበቁ በሽታዎችን ለማግኘት የሚያስችል ሲሆን፤ የሕክምና ዘዴው ከመመርመር ባለፈ የሚሠራበት ነው::
የኑክሌር ሕክምና የሰውነት ክፍሎችን ወይም የህዋሳትን የአሠራር ሥርዓት የሚመረምር ሲሆን፤ ይህ ባህሪው ከሌሎች የመመርመሪያ ዘዴዎች ልዩ ያደርገዋል። ሕክምናው አንዳንድ ሕመሞችን (የእንቅርት በሽታን፣ በካንሠር የተጎዳ ህዋስ በቀዶ ሕክምና ከወጣ በኋላ የካንሰሩ ህዋሶች ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል እንዳይሰራጩ ባሉበት በጨረር ለመግደል … ወዘተ) የሚያስችልም ነው:: ይህ የሕክምና ዘዴ አንድ የሰውነት ክፍል ቅርጹን ከመቀየሩና በገጠመው እክል ከመጎዳቱ አስቀድሞ የአሠራር ሥርዓቱ ላይ ችግር ሲያጋጥም ቀድሞ ለማወቅም ያግዛል። በዚህም አንድ የሰውነት አካል አሠራሩን መርምሮ ችግር ካለ ሳይጎዳ በፊት ለማከም የሚቻልበት ነው።
ሕክምናው በኢትዮጵያ መቼ ተጀመረ
የኑክሌር ሕክምና በዓለም ደረጃ በእጅጉ እየረቀቀና የተሻሉ እድሎችን ይዞ እየመጣ የሚገኝ የሕክምና ዘዴ ሲሆን፤ አሁን ላይ ፔት ኤም አር አይ ( PET/MRI) የተባለው መሣሪያን በመጠቀም ኤም አር አይን፤ ራዲዮሎጂውንና ኑክሌር ሕክምናውን አዋህዶ የሚሰጥበት ዘዴ ነው:: በአፍሪካ ደረጃ ሰሜንና ደቡብ አፍሪካ ላይ በስፋት ተግባራዊ እየሆነ የሚገኝ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መተግበር የጀመረው እ.ኤ.አ በ1984 ነው:: ተግባሩ እውን የሆነበት ሆስፒታል ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነው፤ የተቋቋመውም በዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ እንደነበረ ዶክተር ቤተልሔም ይናገራሉ::
ሕክምናውን በሆስፒታሉ ለማስጀመር ሲነሳ የኑክሌር ሕክምና መስጪያ መሣሪያ አልነበረም:: ነገር ግን እውቀቱም ፣ አቅሙም የነበራቸው ሐኪም ነበሩና እርሳቸውን በመያዝ ሌሎች ባለሙያዎችን በመጨመር ኑክሌር ሕክምና የሚለው ጽንሰ ሃሳብ እንዲታወቅ ተደረገ:: ‹‹ስፔክት/SPECT›› በሚባል መሣሪያ አማካኝነት የተለያዩ ምርመራዎችን ማድረግ ተጀመረ:: ለአብነት የእንቅርት፤ የአጥንትና የኩላሊት ሕክምናዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው::
እአአ በ2013 ደግሞ ነባር ክፍሎች በአዲስ ተደራጅተው ለሕክምናው አመቺ የሚሆኑበት እድል ተመቻቸ:: ከዚያም ከሁለት ዓመት በፊት በገቡት እንደ ‹‹ስፔክ ሲቲ/SPECT/CT›› አይነት መሣሪያዎች ሥራውን እውን ወደ ማድረጉ ተገባ:: በሀገር ደረጃም ጥሩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ተጀመረ:: አሁን ላይ ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባሻገር ሰባት የማስፋፊያ ሆስፒታሎች ተመርጠው እየሠሩ ይገኛሉ:: የጅማ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምናውን ለማስጀመር የሚጠቅም ስፔክት/SPECT የሚባል መሣሪያ ስላላቸው ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን ዶክተር ቤተልሄም ይገልፃሉ::
ጤና ሚኒስቴርና ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ በመተባበር ሆስፒታሉ የኑክሌር ሕክምና አገልግሎቱን ዳግም በዘመናዊ መንገድ ለመስጠት የሚያስችለውን መሣሪያዎችና ግብዓቶች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ አሁን ላይ የኑክሌር ሕክምና ስፔሻሊስት ሃኪሞች፣ ራዲዮ ፋርማሲ ባለሙያዎች፣ የኑክሌር ሕክምና ቴክኖሎጂስቶች እና የራዲዮ ኢሚኖሀሴ ባለሙያዎች በድምሩ 11 የሚደርሱ ባለሙያዎችን በመያዝ ሥራው መጀመሩንም ዶክተር ቤተልሔም ነግረውናል::
የኑክሌር ሕክምና ጥቅም
በኑክሌር ሕክምና የሕክምና መድሃኒቶች ጨረር የሚያመነጭ አካልና ለመድሃኒትነት የሚውል ክፍል ያለ ሲሆን፤ ለአብነት አንድ የኑክሌር መድሃኒት ለኩላሊት ምርመራና ሕክምና ከታሰበ መድኃኒቱ ኩላሊት ዘንድ በተለያዩ መንገዶች (በደም ስር፣ በትንፋሽ፣ በሚዋጥ እንክብል መድኃኒት መልክ ወዘተ) እንዲደርስ ይደረጋል። በዚህም ጨረሩ ቀጥታ ወደ ታካሚው ገብቶ ከውስጥ ወደ ውጭ በመውጣት የታካሚውን የሰውነት ክፍል ያሳያል። ይህ መሆኑ ደግሞ ከዚህ ቀደም በሚደረጉ ሕክምናዎች ይደረግ የነበረውን አሠራር በብዙ መልኩ ይቀይረዋል:: የኑክሌር ሕክምና ጨረርን ከውስጥ ወደ ውጭ ስለሚያሳይ የተሻለ መረጃ ይዞ ፤ የአካሉን ክፍል በደንብ አውቆ ለማከም ተመራጭነት አለው::
የተጎዳው አካል ‹‹ምን ችግር አለበት?፤ የደም ዝውውርና መሰል የጤና ችግሮች ተከስተዋል ወይስ አልተከሰቱም?›› የሚለውን የደህንነት ጉዳይ ቁልጭ አድርጎ በተለያዩ ቴክኖሎጂ መረጃውን በምስል ጭምር ደግፎ ያሳያል፤ በቀላሉም መረጃና ምስሉን በመያዝ ሕክምናውን ለማከናወን ያስችላል:: የሕክምና ባለሙያዎችም ከግምት በፀዳ የጠራ መረጃ ሕክምናውን እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል::
የኑክሌር ሕክምና ሌላኛው ጠቀሜታ አንድ ሰው ኩላሊቱን ለሌላ ሰው ለመለገስ ሲያስብ የለጋሹ አካል የሆነውን የኩላሊቱን ሁኔታ ቅድሚያ ማወቅ እንዲቻል ያግዛል:: የቀኝም ሆነ የግራ ኩላሊቶቹ ምን ያህል እንደሚሠሩ ምርመራ ለማድረግም በዋነኝነት ሕክምናው ያገለግላል::
አንዳንድ ህመሞች ላይ ቀጥታ ሕክምና ለመስጠትም ይጠቅማል። በተለይ ደግሞ አንድ ሰው እንቅርት ኖሮበት እንቅርቱ ከፍተኛ ሆርሞን የሚያመነጭ ከሆነ፤ በቀዶ ሕክምና እንቅርቱን (Toxic Multinodular goiter) ማውጣት ሳያስፈልግ በጨረሩ ተመሳሳይ ሕክምና መስጠት ያስችላል። በተጨማሪም ሌሎች የሰውነት ክፍሎች (አጥንት፣ ጭንቅላት፣ ልብ፣ ጉበት …) የአሠራር ሥርዓታቸው ላይ ምርመራ በማካሄድ በሌሎች የመመርመሪያ ዘዴ ያልተገኙና የተደበቁ በሽታዎችን መርምሮ ለማግኘትም ሁነኛ ዘዴ ነው።
በተለይ የኑክሌር ሕክምና የካንሰር ህመም ስር ከመስደዱና ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ በሽታውን ለማወቅና ተገቢውን ሕክምና ለመስጠት ወይም ታካሚው ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኝ ለማድረግ ወሳኝነት አለው። ካንሰሩ ከተገኘ በኋላም ያለበትን ሒደት አውቆ ሕክምናውን ለመስጠትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል::
ይህ ሕክምና በተለይም እንደ እኛ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ወሳኝነቱ ከፍተኛ ነው:: ምክንያቱም የካንሰር ታማሚዎቻችን ወረፋ ይዘው ረጅም ጊዜ የሚጠብቁ፤ በቀላሉ ሕክምናውን ለማግኘት የማይችሉ ናቸው:: ስለዚህም መድሃኒቱና የተሟላ መሣሪያው ካለ ዜጎች በሀገራቸው በተመጣጠነ ዋጋ አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማስቻል የዜጎችን እንግልት እና ከፍተኛ ወጪን ለመቀነስ ያስችላል:: ሕክምናው እንደ ሀገር በኢትዮጵያ በበቂ ሁኔታ ከተስፋፋ ብዙዎች ወደ ውጭ የሚሄዱበትን እድል ያስቀራል፤ ሀገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪም ይቀንሳል።
በጥቅሉ የኑክሌር ሕክምና ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ምርመራ ያደርጋል፤ ሕክምናም ይሰጣል። ሕክምናውም ለአብዛኛው ታካሚዎች አስፈላጊና ጠቃሚ ነው::
የሚያጋጥሙ ችግሮች
የኑክሌር ሕክምና ለመስጠት የሚያስችሉ መድሃኒቶችም ሆኑ መሣሪያዎቹ በጣም ውድ ናቸው:: በመሆኑም የግለሰብ አቅምን ብቻ ሳይሆን የሀገርን ከፍተኛ ሀብት ይጠይቃሉ:: በዚህ ምክንያት በሚፈለገው ልክ ህክምናውን ለዜጎች ለማድረስ አዳጋች ነው። የተወሰኑ መሣሪያዎችንም በርዳታ ጭምር የሚገቡ ናቸው። መሣሪያዎቹን በፍጥነት ለማስገባትም እንዲሁ አይቻልም።
በዚህ ምክንያት በኑክሌር የታገዘ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ረጅም ጊዜ የሚወስድ ወረፋን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። መድሃኒቱ እስኪገባ ድረስ ሆስፒታሎች ታካሚዎችን መዝግበውና ተራቸውን ጠብቀው እየደወሉ በመጥራት ሥራቸውን ያከናውናሉ።
እንደ ዶክተር ቤተልሄም ሃሳብ ሕክምናውን ከመንግሥት ሆስፒታሎች ውጪ ለማድረግ አብዛኛው ማህበረሰብ ይከብደዋል:: ከሀገር ውጭ ወጥቶ ለመታከምም እንዲሁ የማይታሰብ ነው:: በመሆኑም ሕክምናውን ለማግኘት ያልታደሉ ብዙዎች ናቸው:: የጤና ቅብብሎሽ ሥርዓት የመጨረሻውና ከፍተኛው የጤና እንክብካቤ መስጫ በመሆኑ ሕክምናውን ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚመጡ ዜጎች ጥራት ያለው አገልግሎት በተመጣጠነ ዋጋ እንዲያገኙ ለማስቻል ልዩ ልዩ ተግባራትን በሀገር ውስጥ ማከናወን ይቻላል:: ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አይነቶች የባለሙያ እጥረት እንዳያጋጥማቸው መሥራትና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አንዱ ቀዳሚ ርምጃ ነው::
ሌላው በዘላቂነት ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችለው መፍትሄ በኢትዮጵያ የሕክምና መሣሪያዎቹንም ሆነ መድሃኒቶቹን የሚመረቱበትን እድል መፍጠር ነው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን እቅድ መሬት ላይ ለማውረድ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ::
እንደ አገር የሰው ሃይል እና የፋይናንስ አቅምን በአንድ አቀናጅቶ ከተሠራ በኑክሌር የሚሰጥ ሕክምናን በበቂ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ መስጠት ይቻላል። ሕክምናውን ለመስጠት የሚያስችሉ መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት እና ፍላጎትን መሸፈንም እንዲሁ ቀላል ይሆናል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ የኑክሌር ሃይልን ሕክምናን ጨምሮ ለበጎ ዓላማ የሚያውሉ ፕሮጀክቶችን ይፋ አድርጋለች። ይህ እቅድ ወደ መሬት ሲወርድ የሕክምና ዘርፉ እና ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም