የታዳጊዎች ስፖርት ልማትና የክልሎች እንቅስቃሴ

በዓለም አቀፍ መድረኮች ሀገርን ማስጠራት የሚችሉ ውጤታማ ስፖርተኞችን ለማፍራት ታዳጊዎች ላይ መሥራት ግዴታ መሆኑ አያከራክርም። በመሆኑም ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ ታዳጊዎችን ለማፍራት በሀገር አቀፍ ደረጃ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ልማት ላይ ትኩረት አድርጋ መሥራት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።

በዚህ ሀገር አቀፍ የስፖርት ልማት ፕሮጀክት በተለያዩ ስፖርቶች ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች በመለየት በሳይንሳዊ ሥልጠና እንዲያልፉ ለማድረግ ክልሎች ትልቅ አቅም አላቸው። ስለሆነም በርካታ ክልሎች በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ አትሌቲክስ እና ብስክሌት ባሉ ስፖርቶች ውጤታማና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ስኬታማ የሆኑ ስፖርተኞችን ካፈሩ ክልሎች መካከል አንዱ ትግራይ ነው። አቶ ሃፍቶም በርሄ በክልሉ የስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ሥልጠና አስተባባሪ ሲሆኑ፣ በቅርቡ በተካሄደው ሀገር አቀፉ የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ምዘና ውድድር ቡድን መሪ ናቸው። እንደ አቶ ሃፍቶም ገለፃ፣ በክልሉ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የታዳጊ ወጣቶች ፕሮግራም ተቋርጦ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም፣ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ካለፈው ዓመት አንስቶ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በተደረገለት ድጋፍ ወደ ሥልጠና ተመልሷል። በዚህም በወላይታ በተካሄደው የምዘና ውድድር ላይ ተሳታፊ ሊሆን ችሏል። በ147 ታዳጊዎችም በ 6 የስፖርት ዓይነቶች (አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ) ተሳታፊ ሆኗል።

በክልሉ የታዳጊዎች ስፖርት ልማትን ጨምሮ እንደ አጠቃላይ ስፖርቱ እያንሰራራ ሲሆን፤ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በሚደረግለት ድጋፍ መሠረት በተለያዩ ስፖርቶች የታዳጊዎች ሥልጠናው እየሰጠ ይገኛል። በሥልጠናው ተሳታፊ የሚሆኑ ታዳጊዎችም ምልመላ ሲከናወን በዘመናዊ መሣሪያዎች በታገዘ የዕድሜ ልየታ በመደረጉ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንደተቻለ ቡድን መሪው ያስረዳሉ። አሠልጣኞችም እንደየስፖርት ዓይነቱ ብቁ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል። በየዓመቱ በክልሉ በሚከናወን ውድድር የሠልጣኞችን አቅም በመለካትም ከክለቦች ጋር በተፈጠረው ትስስር መሠረት ምልመላ እንዲከናወን ይደረጋል። በዚህም ቀደም ሲል በአትሌቲክስ ስፖርት በተደረገ ምዘና ሠልጣኞችን ለማስመረጥ ተችሏል፤ በሀገር አቀፉ የምዘና ውድድርም መሰል ዕድሎች ለሠልጣኞች ይኖራል በሚልም ይጠበቃል። በቀጣይም ይህንኑ በማጠናከር ክልሉ ወደነበረበት ከፍታና ተፎካካሪነት ለመመለስም በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ቡድን መሪው አረጋግጠዋል።

ታዳጊዎች ላይ በትኩረት እየሠሩ ከሚገኙና በምዘናውም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ከቀረቡ ክልሎች አንዱ የኦሮሚያ ነው። በምዘና ውድድሩ የኦሮሚያ ክልል ልኡክ ቡድን መሪ የሆኑት ቶሎሳ ጨመዳ፤ በክልሉ 280 ፕሮጀክቶች በ11 የስፖርት ዓይነቶች ታዳጊዎችን እያሠለጠነ መሆኑን ይጠቁማሉ። ፕሮጀክቶቹ ከክልሉ የስፖርት ምክር ቤት እስከ ወረዳ ድረስ የሚደገፉ ሲሆን፤ የክልሉ ስፖርት ቢሮም የቁሳቁስና የባለሙያዎች ሥልጠና ድጋፍም ይደረግላቸዋል። ስፖርቱ እንደሀገር ያለበትን ስብራት በመለየት መፍትሄው ታዳጊ ላይ መሥራት መሆኑን በመረዳት በትኩረት እየተሠራ ሲሆን፣ እንደየስፖርት ዓይነቱ በባለሙያዎች የቅርብ ክትትልም ይደረግለታል። በተጨማሪም ክልል አቀፍ ውድድሮችን በማዘጋጀት የሠልጣኞች አቅም ምዘና ይካሄዳል።

የታዳጊ ፕሮጀክቶች ሥልጠና የተሻለ ብቃት ያላቸው ስፖርተኞችን ለማሠልጠኛ ማዕከላት አካዳሚዎችና ክለቦች ግብዓት እንዲሆኑ ማፍራት ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ክልሉ ሠልጣኞቹን በምዘናው ለመልማዮች ከማቅረብ ባለፈ በደራርቱ ቱሉ አካዳሚ ገብተው ሊሠለጥኑ የሚችሉ ታዳጊዎችን በሀገር አቀፍ የምዘና ውድድሩ ከተሳተፉና የተሻለ አቋም ካላቸው አትሌቶች የሚመለምል መሆኑንም ቡድን መሪው ያመላክታሉ። ይህንን ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎች በምዘናው ወቅት የተሠማሩ ሲሆን፤ ምልመላውም እንደሀገር ምርጥ ብቃት ያላቸውን ታዳጊዎች ኢላማ ያደረገ ነው። በመሆኑም በወላይታ ሶዶ ከተማ የተደረገው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ምዘና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውና በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት የሚያስችል መሆኑ ያስረዳሉ።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You