ከአይረን ኦር በተጨማሪ ወርቅና መዳብ ለማምረት የተዘጋጀው ድርጅት

ኢትዮጵያ ካሏት የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች መካከል የሚጠቀሱት ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ናቸው፤ እነዚህ ማዕድናት በሀገሪቷ የተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ። ጥናቶች እንዳመለከቱት፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች ከአንድ ቢሊዮን ቶን በላይ የብረት ማዕድን ክምችት አለ። ይህ ክምችት እንዲለማ ቢደረግ የሀገር ውስጥ ፍጆታ በማሟላት ለብረት ማዕድን የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት እንደሚያስችል መረጃው ያሳያል።

እነዚህ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት እምቅ ሀብት ካሏቸው ክልሎች መካከል የሶማሌ ክልል ይጠቀሳል። ክልሉ ሌሎች በርካታ የማዕድን ሀብቶች ያሉት ሲሆን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ክምችት እንዳለውም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ ማዕድናት መካከል ብረት፣ መዳብ፣ ወርቅ፣ ክሮማይት፣ ኒኬል፣ ማንጋነስ፣ ዚንክና ሌሎችን ይጠቀሳሉ።

ክልሉ ቀደም ባሉት ጊዜያት እነዚህን ሀብቶች አልምቶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ እምብዛም ሠርቷል ሊባል ባይችልም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በማዕድን ዘርፉ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑ ይገለጻል።

መንግሥት የማዕድን ዘርፉን በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚው ምሰሶዎች አንዱ እንዲሆን በማድረጉ በዘርፉ ላይ መነቃቃት እየተፈጠረ መጥቷል፤ ዘርፉ ለኢንቨስትመንት ክፍት በመደረጉም በርካታ ኢንቨስተሮች በዘርፉ እየተሠማሩ ይገኛሉ።

በዘርፉ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የሶማሌ ክልል የማዕድን ሀብቶችን ለማልማት እያስቻለ ነው፤ በርካታ ባለሀብቶችና ድርጅቶች በክልሉ በዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲሠማሩ አስችሏል።

በክልሉ ማዕድን ለማልማት ከተሰማሩ በርካታ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ‹‹ሀሰንቴ ማይኒንግ ኮምፓራቲቭ›› የተሰኘው ድርጅት በክልሉ የተለያዩ ማዕድናት ለማምረት የሚያስችለውን ፍቃድ ወስዶ በዘርፉ ከተሰማራ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል።

ድርጅቱ የክልሉን ማዕድናት በማጥናት እና በማልማት ከውጭ የሚገቡ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ ማዕድናቱን ለማስመጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማዳንና በማዕድን ዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማስፋት እንዲቻል ሲሠራ መቆየቱን ይገልጻል።

የሀሰንቴ ማይኒንግ ኮምፓራቲቭ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲቃ ሀኑ ‹‹ድርጅቱ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ እቅዶችን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ በመግባት እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ በክልሉ ማዕድናት ላይ ጥናት በማድረግና በዘርፉ ለመሠማራት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖሩን በማረጋገጥና በአጭር ጊዜ ውስጥም ራሱን በቁሳቁስ እና በሰው ኃይል በማደራጀት ነው ወደ ሥራው የገባው። የአጭርና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ እቅድ አውጥቶም ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ድርጅቱ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል ዋንኛዎቹ የክልሉን ማዕድናት ማጥናት፣ ማልማትና ወደ ገበያ ማቅረብ የሚሉት ናቸው። በተለይ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገቡ ማዕድናት በሀገር ውስጥ መተካት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።

ሀሰንቴ ማይኒንግ ኮምፓራቲቭ በክልሉ የአይረን ኦር፣ መዳብ፣ ክሮማይት፣ ወርቅ እና የመሳሰሉት ማዕድናት ከፍተኛ ክምችት መኖሩን አረጋግጦ ማዕድናቱን ለማልማት አቅዶ መነሳቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ያመላክታሉ። ድርጅቱ ወደ ሥራ እንደገባም ለማዕድን ለማልማት ምቹ የሆኑ ሥራዎች በመሥራት በተለይ አይርን ኦር ወደ ማምረት መግባቱን ያስታውሳሉ። ቀጥሎም እንደ መዳብ እና ወርቅ ያሉትን ማዕድናት ለማልማት የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል ይላሉ።

የሚያመርተውን አይረን ኦር የተሰኘ የብረት ማዕድን ለገበያ ማቅረብ ከጀመረም መቆየቱን ይገልጻሉ። ድርጅቱ ምርቶቹን የሚረከቡ አቅራቢዎች እንደነበሩት አስታውሰው፣ አቅራቢዎቹም ለደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የአይረን ኦር ምርቱን ሲያቀርቡ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ይሁንና ድርጅቱ ምርቶችን ከሚፈለገው መጠን በላይ ማምረት ቢችልም ባጋጠመው የገበያ እጦት ምክንያት መቀጠል አለመቻሉን ዋና ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

ምርቱን ተረክበው ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያቀርቡት ማኅበራት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። ማኅበራቱ አይረን ኦሩን ከድርጅቱ በርካሽ ዋጋ ተረክበው ዋጋ ጨምረው እያቀረቡ መሆናቸውና ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ሕገወጥ ደላሎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ገበያ ለማጣቱ ምክንያቶቹም እነዚህ አካላት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም የምርቱ ዋጋ ከተጠበቀው በታች እንዲሆንና ገዢ እንዳይኖር ማድረጉንም አመልክተዋል። የምርቱ ዋጋ እንዲወርድ በመደረጉ ብዙ ምርት እንዲከማች ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሲሰጠው የነበረው ዋጋ ድርጅቱ ምርቱን ለማምረት የሚያወጣውን ወጪ ለመሸፈን እንደማያስችልም ይገልጻሉ። ድርጅቱ ማዕድን በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ከፍተኛ የሰው ጉልበት ይጠቀማል፤ ብዙ ሀብትም ያወጣል ሲሉም አብራርተዋል። የተሻለ ገበያ ለመፈለግም ምርቱን በቀጥታ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለማቅረብ ጥረት ቢያደርግም በቦታው ላይ ባሉ ያልተገባ ጥቅም ፈላጊዎች የተነሳ ችግሩን መፍታት እንዳልተቻለም ያመለክታሉ።

አሁን ላይ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ከተለያዩ አቅራቢ ድርጅቶችና ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ እየተደረሰ መሆኑንም ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ አሁን ላይ ከአይረን ኦር ምርት ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ከማዕድን ሚኒስቴር እና ከክልሉ ማዕድን ቢሮ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። የገበያ ችግሩ ከተፈታ ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ በሌሎች ማዕድናት ልማት ላይ ለመሠማራት የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርለት ይገልጻሉ።

ዋና ሥራ አስኪያጁ እንዳብራሩት፤ የክልሉ የአይረን ኦር ክምችት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ፋብሪካ ቢከፈት ብዙ ማምረትና የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ ለውጭ ገበያም ማቅረብ የሚያስችል ነው። የአይረን ኦር ምርቱ የጥራት ደረጃውን የጠበቀና ከውጭ ከሚመጣው ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ጥራት ያለውም ነው።

በክልሉ በዳዋ ዞን ሞያሌ፣ ሁዴት እና ሙባረክ ወረዳዎች የአይረን ኦር፣ የመዳብና የወርቅ ከፍተኛ ክምችት እንዳለም ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰው፤ ‹‹ድርጅቱ ማዕድን የማልማት ሥራውን በአይረን ኦር ማምረት ይጀምር እንጂ ወርቅና መዳብ ለማምረትም ጥናቱን አጠናቀቆ ወደ ማምረት እንቅስቃሴ ገብቷል›› ሲሉም ጠቁመዋል።

በክልሉ ያለው የወርቅ ማዕድን ክምችት ቀላል የማይባል መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ድርጅቱ ወርቅ ለማምረት የሚያስፈልጉ ማሽኖችን በማስመጣት ለሥራ ዝግጁ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። በሚቀጥለው ወር ወደ ማምረት እንደሚገባም ይገልጻሉ። በክልሉ ጥሩ የሚባል የወርቅ ምርት ማግኘት እንደሚቻል የሚያሳዩ አመላካቾች እንዳሉም አመላክተዋል።

ድርጅቱ ወደ ሥራ ከገባ አንስቶ ለዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑም ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ብቻ ለ97 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል። በቀጣይ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችልም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ድርጅቱ በቀጣይም አሁን ላይ እያካሄደ ያለውን የማዕድናት ልማት ጨምሮ ሌሎች ማዕድናትን ለማልማት ይሠራል። በተለይ አይረን ኦርን በማምረት እንደ ሀገር ያለውን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።

ክልሉ ያለው የመዳብ ክምችት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከውጭ የሚመጣውን የመዳብ ምርትም እንዲሁ በሀገር ውስጥ በመተካት ሀገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስረቀት የሚያስችሉ ሥራዎችን ይሠራል ብለዋል። ወደፊት መዳብ በብዛት ለማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ አቋቋሞ ለመሥራት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የድርጅቱ ባለሙያ አቶ ኢብራሂም አብዱላ እንዲሁ ድርጅቱ ያመረተው ብዙ የአይረን ኦር ክምችት እንዳለ ይገልጻሉ። ድርጅቱ እያመረተ ያለው አይረን ኦር ብዙ ቢሆንም ግን ምርቱን የሚረከብ አቅራቢ ማግኘት ፈተና እንደሆነበትም ገልጸዋል። ቀደም ሲል ምርቱን ወስደው ለሰሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያቀርቡ አቅራቢዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ አቅራቢዎቹ ወደ ሌላ አካባቢ ፊታቸውን ማዞራቸውንና ገበያውንም መውሰዳቸውም ይጠቅሳሉ። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

አይረን ኦር የተሰኘው ማዕድን ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለተለያየ ግብዓትነት በብዛት እንደሚገለገሉበት ጠቅሰው፣ ይሁንና ድርጅቱ ያመረተው አይረን ኦር በተመረተበት ቦታ ተከምሮ እንዲቀመጥ መደረጉን ይጠቁማሉ።

የመዳብና የወርቅን ፍለጋ ሥራው ተጠናቅቆ በሚቀጥለው ወር ጀምሮ ወደ ማምረት እንደሚገባ አቶ ኢብራሂምም አመላክተዋል፤ እነዚህ ማዕድናት ከመመረታቸው በፊት ገበያ በማፈላለግ ረገድ ማዕድናቱን ከሚረከቡ አካላት ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ሥራዎች መጀመራቸውንም ይገልጻሉ፡፡

ለዚህም በተለይ በተያዘው ዓመት ኅዳር ወር የተዘጋጀው 3ኛው የዓለም አቀፍ የማዕድን ኤክስፖ ለድርጅቱ መጥቀሙን ገልጸው፤ በክልሉ ያሉት ማዕድናትና ድርጅቱ በተሠማራበት በማዕድን ዘርፍ እየሠራ ያለውን ሥራ አስመልክቶ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራቱንም ተናግረዋል፡፡

በገበያ በኩልም በሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር መፍጠር የሚችሉበት ዕድል እንደተከፈተላቸው ይገልጻሉ። ከዚያ ወዲህ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ከብዙ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በዚህም የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ክልሉ በማዕድን ዘርፍ ገና ያልተነካ እምቅ ሀብት አለው። የማዕድን ሀብት ያለውና እነዚህ አልምቶ ጥቅም ላይ ማዋል ለክልሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ብዙ ጥቅም ያስገኛል፡፡

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ካለው አቅም አንጻር በተወሰኑት ማዕድናት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ሥራውን የጀመረ ቢሆንም፣ በቀጣይ ሌሎች ማዕድናትን በማልማት ሥራ ይሠማራል።

በቀጣይ ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ ለማምረት እየተሠራ መሆኑን እሳቸውም ጠቅሰው፤ አሁን መሠረተ ልማት ከመገንባት ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖችን የማሟላቱ ሂደት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በሚቀጥለው ወር ሥራ እንደሚጀመርም አመላክተዋል። በብረት ላይም እንዲሁ የሚታየውን የገበያ እጥረት ለመፍታት ማሽኖችን በማስመጣት በፋብሪካ ደረጃ ብረት ለማምረት አቅዶ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ የክልሉን ማዕድን በማልማት ሥራ ላይ ተሠማርቶ እየሠራ እንደመሆኑ በክልሉ ያሉ ማዕድናት ከማስተዋወቅ ጀምሮ እስከ ማልማት ያለውንም ሥራ ይሠራል። በዚህም ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡትን ማዕድናት በሀገር ውስጥ በመተካት የሚወጣው ወጪ በማስቀረት እንደሀገር ተጠቃሚ ለመሆን እየተሠራ ነው። ማዕድናትን በማልማት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You