ብዙዎች የሚመኟት የተስፋይቱ ምድር

ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ ዛሬ የነጻነት ተምሳሌት ሆና ዘልቃለች። መላው አፍሪካ እና ጥቁር ሕዝብ በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ሲማቅቅ ከመላው ጭቁኖች ጎን ተሰልፋ በርካታ ትግሎችን ያቀጣጠለች እና አፍሪካውያን ለነጻነታቸው እንዲታገሉ መንገድ ያመላከተች ብቸኛ ሀገር ነች።

ይህ ደግሞ በርካታ የጥቁር መብት ተሟጋቾችን ቀልብ እንድትስብ አድርጓታል። አንዳንዶችም መለኮታዊ ሥፍራም ሰጥተዋታል። ብዙዎቹም የመጨረሻ መዳረሻቸው እና መኖሪያቸው ኢትዮጵያ ኢንዲሆን እየተመኙ ኖረዋል። አሁንም ቢሆን ይህ ምኞታቸው አንድ ቀን እውን እንደሚሆን የሚጠብቁ በርካቶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ ባላት ከፍተኛ ድርሻ ብቻ ሳይሆን በነበራት ተጽእኖም ሆነ ተደማጭነትና ዝና በጭቆና ስር የነበሩ ጥቁር ሕዝቦች በተስፋ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለከቱ አስገደዳቸው። እንደ ኢትዮጵያና ግብጽ በሰው ልጅ የሥልጣኔ ታሪካዊ ድርሳን ውስጥ በተደጋጋሚ የተወሳላቸው ሀገሮች በአፍሪካ ውስጥ የሉም። በክርስትናም ሆነ በእስልምና እምነት የኢትዮጵያ ስም በተደጋጋሚ የሚነሳ ነው። አንዱ ዋነኛውና ጥንታዊው ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ መዝሙረ ዳዊትንና መጽሐፈ ኤርምያስን መመልከት ይበቃል። በእስልምና ኃይማኖትም ወደ እውነተኛዋ ምድር ሂዱ የሚለው የነብዩ መሀመድ ትዕዛዝ የሚጠቀስ ነው፡፡

የነጻነት ታጋይ አፍሪካውያን የሚያደርጉት ትግል “ያለምግብ መጋቢ፣ ያለውሃ ዋናተኛ” እንዳይሆንባቸው በማሰብ የነጻነት ትግላቸውን ለማሳለጥ የሚረዷቸውን የተለያዩ ድርጅቶችን እና ንቅናቄዎችን መሠረቱ። በድርጅቶቻቸው ጥላ ስር ሆነው ለነጻነታቸው መታገል ጀመሩ።

ከንቅናቄዎች መካከል “ኢትዮጵያኒዝም” (ETHIOPI­ANISM) አንዱ እና የመጀመሪያው ነው። ኢትዮጵያኒዝም በዘመናዊው የቅኝ ግዛት ዘመን ለኃይማኖት እና ለፖለቲካዊ ነፃነት የተነሱትን ቅስቀሳዎች ያቀፈ፤ ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካውያን የተደረገ የሃይማኖት እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴው የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1880ዎቹ ሲሆን የጀመሩትም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ “የሚሽነሪ” ሠራተኞች ናቸው።

ዋና ዓላማውም ከአውሮፓውያን ተጽዕኖ ነፃ የሆኑ የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናትን ለማቋቋም የታለመ መሆኑን የታሪክ ድርሳነት ያስረዳሉ። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያኒዝም “በኃይማኖት ብቻ ሊገለጽ የማይችል መሆኑን ፖለቲከኞች እና የታሪክ ጸሐፊዎች ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያኒዝም (Ethiopianism) የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው በደቡብ አፍሪካ የቀድሞው «የዌስሊያ» ቤተክርስቲያን አገልጋይ ማንጌና ሞኮን እኤአ በ1892 የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን (Ethiopian Church) ሲመሠርት ነው።

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን ንቅናቄ ተከትሎ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የንቅናቄውን ዓላማ የሚያስቀጥሉ አብያተ ክርስትያናትን ከፈቱ። ከእነዚህ መካከል በናይጄሪያ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ተብለው የሚጠሩት-የኔቲቭ ባፕቲስት ቸርች እ.ኤ.አ 1888፣ የቀድሞዋ የአንግሊካን ዩናይትድ ቤተኛ አፍሪካ ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ1891 እና የተባበሩት አፍሪካ የሜቶዲስት ቸርች እ.ኤ.አ 1917 ተጠቃሽ ናቸው።

በካሜሩን ተወላጅ ባፕቲስት ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ 1887፣ በጋና በናቲቭ ባፕቲስት ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ 1898፣ የአሜሪካ ኔግሮ ቤተ እምነት በሮዴዥያ ቅርንጫፍ እ.ኤ.አ 1906 ፣ በኬንያ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ 1957 እና ሌሎችም የኢትዮጵያንዝም ንቅናቄን ተከትሎ የተከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

በንቅናቄው “Africa for the Africans” “አፍሪካ ለአፍሪካውያን” የሚለው መፈክር በሰፊው የተቀነቀነ ሲሆን የአፍሪካውያን የዕምነት ነጻነት እንዲረጋገጥ እና በፖለቲካው ዘርፍም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዲረጋገጥ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል።

የኢትዮጵያኒዝም ንቅንናቄ መሪዎች እና ተከታዮቻቸው የአፍሪካውያን ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያ “አፍሪካዊት ጽዮን” “African Zion” እያሉ ይጠሯት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ንቅናቄያቸውን ኢትዮጵያኒዝም ብለው እንዲሰይሙ ያደረጋቸው አንደኛው ምክንያት ይኸው ስለመሆኑ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። የኢትዮጵያኒዝም አጥብቆ ተሟጋች የነበረው ጆርጅ ሊሌ በ1884 የኢትዮጵያ ባብቲስት ቸርች በሚል መጠሪያ በጃማይካ ቤተክርስቲያን መሥርቷል። “ኢትዮጵያኒዝም ወደ አሜሪካ ከመድረሱ አስቀድሞ ሥነ ቃሉ ጃማይካ ውስጥ ሥራ ላይ መዋል ጀምሮ የነበረውም በጆርጅ ሊሌ እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ሌላው የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ ብርቱ አራማጅ ማርቆስ ጋርቤ ነበር። ንቅናቄው እንዲያንሰራራም ብዙ ጥሯል። ስለእምነቱም መርህ ሲናገር፣ እኛ /ጥቁሮች/ ኔግሮዎች ዘለአለማዊው እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ የዘመናት ሁሉ አንድ እግዚአብሔር በሆነው በኢትዮጵያ አምላክ እናምናለን። ይህ ነው የምናመልክው አምላክ የምናመልከው ግን በኢትዮጵያ መነጥርነት ወይም በኢትዮጵያ በኩል ነው ብሏል፡፡ ጋርቢ እንዲሁ ተራ ሰው አልነበረም። አልፎ አልፎ ተፈጥሮ ካበቀለቻቸው ለየት ለየት ያሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ እንደነበረ የተጻፈለት ሰው ነው። ወደተስፋይቱ ምድር ኢትዮጵያ የመመለስን ንቅናቄ ነፍስ የዘራበት እርሱ ነበር፡፡ “የኢትዮጵያኒዝም ርእዮተዓለምን ከክርስትና ጋር በማዛመድ ይበልጥ ጐልቶ እንደወጣበት ያደረገው ማርቆስ ጋርቢ ነው። በተለያየ ወቅት ባደረጋቸው ንግግሮቹ ፍቅር፣ መረዳዳት እና ለጋስነት የመጣው ከጥቁር አፍሪካ፣ ከግብጽና ኢትዮጵያ ሲሆን ነጮች ግን ስግብግቦች፣ ፍቅር የለሾችና ንፉጎች ናቸው ብሏል። ስለሆነም በማርቆስ ጋርቢ አማካይነት “ኢትዮጵያኒዝም በርእዮተዓለምነት በንድፈሃሳብ ብቻ ሳይወሰን ወደ ንቅናቄነትና ትግል ስልትነት ተቀየረ፡፡

እ.ኤ.አ በ1896 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በአጼ ምኒልክ እየተመሩ ወራሪውን የአውሮፓ ኢፔሪያሊስት ጣልያን በዓድዋ ጦርነት ድል መንሳታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ በከፍተኛ ደረጃ ጎመራ። የኢትዮጵያኒዝም የተሰኘውን ቃል የሚጠቀሙ አፍሪካውያን ቁጥር በእጅጉ ጨመረ።

እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር ያለ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያኒዝም እና በኢትዮጵያ ያለው ቁርኝት ምን እንደሚመስል ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ ኢትዮጵያን “አፍሪካዊነት ጽዮን” “African Zion” እያሉ የጀመሩት ስለመሆኑ እና የዓድዋን ድል ተከትሎ ኢትዮጵያኒዝም (Ethiopianism) ከኃይማኖታዊነት ትግል ባለፈ ለጥቁሮች ፖለቲካዊ ነጻነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ብዙዎች የሚናፍቋት የመጨረሻ ቤታቸው ነች። ኋላ ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሊቴሪ ሥልጠና እንደተሰጣቸው ይታወቃል። እሳቸውም ‹‹A Long Walk to Freedom ››በተባለው መጽሃፋቸው ውስጥ ‹‹አሜሪካንን፤ እንግሊዝንና ፈረንሳይን በአንድ ላይ ከምጎበኝ ኢትዮጵያን ማየት እመርጣለሁ›› ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You