
አዲስ አበባ፡- የፋይዳ መታወቂያ አገልግሎቶችን አጠቃሎ የያዘና ከደንበኞች ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አፋጣኝ መልስ መስጠት የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ ይፋ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮሚኒኬሽን እና ሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ አቤኔዘር ፈለቀ ትናንት መተግበሪያው ይፋ በሆነ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ መተግበሪያው መበልጸጉ የፋይዳ መታወቂያ አገልግሎቶችን በማዘመን የደንበኞችን ቅሬታ ወዲያውኑ ለመፍታት እና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተደራሽ የመሆን አቅምን ከማሻሻል አንጻር ትልቅ ምዕራፍ ነው።
መተግበሪያው በተቋሙ የውስጥ የሰው ኃይል የተገነባ መሆኑን ገልጸው፤ የመተግበሪያው ዓላማ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎቶችን በቀላሉ እና በተቀላጠፈ መንገድ በአንድ ላይ እንዲያገኙ ለማስቻል “በአንድሮይድ “እና “በአይኦኤስ” አሠራር ሥርዓቶች ለሕዝብ መቅረቡን አስረድተዋል።
አቶ አቤኔዘር እንደሚያስረዱት ፤ መተግበሪያው ደንበኞች በተለያዩ ምክንያቶች የጠፋባቸውን የፋይዳ መታወቂያ ቁጥር መልሰው እንዲያስልኩ፤ መታወቂያቸውን በዲጅታል መልኩ ለመያዝ እንዲሁም፤ ከመተግበሪያው አውርደው ለመያዝ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በምዝገባ ወቅት የተሳሳተ የሥነ ሕዝብ መረጃን ወደ መመዝገቢያ ጣቢያዎች መሄድ ሳያስፈልግ፤ ተጠቃሚዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አማካኝነት ለማረም እና የአድራሻ ለውጥ ሲኖርም ካሉበት ሆነው እንዲያድሱ ያስችላል ብለዋል።
በተጨማሪም የፋይዳ መታወቂያን በካርድ መልክ አሳትሞ ለመያዝ በመተግበሪያው አማካኝነት ለማዘዝ እንደሚያስችል እና ደንበኞች ቅሬታ ሲኖራቸው ቅሬታቸውን ለማቅረብ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ኃላፊው እንደተናሩት፤ በዲጅታል ስትራቴጂ 2025 የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን አስቻይ ከሆኑ መሠረተ ልማቶች ቁልፍና እና ወሳኝ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያን የሽግግር ግብ ለማሳካት እንደዋና አስቻይ ሆኖ እየተተገበረ ይገኛል።
እንዲሁም እስካሁን ባለው ጊዜ ለ12 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ተደራሽ በማድረግ፤ ከተቋማት ጋር አሠራሮችን በማስተሳሰር የተለያዩ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ እና በዘመናዊ መልኩ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል ሲሉ አውስተዋል።
በቀጣይም መተግበሪያውን በማሻሻል ደንበኞች ከፋይዳ በተጨማሪ ከመሬት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ዲጅታል የሆኑ መረጃዎችን መያዝ እንዲችል እና ደንበኞች ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር እንደሚሠራ ተጠቁሟል።
የፋይዳ መተግበሪያ ከአፕ ስቶር እንዲሁም፤ ከፕሌይ ስቶር ላይ በማውረድ መጠቀም እንደሚቻልም ተገልጿል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም