
ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ መንግሥት ላለፉት ስድስት ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ሀገሪቱ እንደ ሀገር ያጋጠሟትን አስቸጋሪ ፈተናዎች በመሻገር ዛሬ ላይ ዜጎችን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸረው የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ችሏል።
በአንድ በኩል የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከለውጡ ዋዜማ እና ማግስት የነበረበት ከፍ ያለ መንገጫገጭ እና መንገጫገጩ ከፈጠረው የኢኮኖሚ ስብራት ፤ በሌላ በኩል ፤ ለውጡን ተከትሎ ሀገረ መንግሥቱን የህልውና ስጋት ውስጥ ጨምሮት በነበረው የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች ፤ በሀገሪቱ በነዚህ የለውጥ ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት የማስመዝገቡ እውነታ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው።
ከፍ ያለ የውጪ የዕዳ ጫና፤ የተሟጠጠ ሀገራዊ የውጪ ምንዛሬ ፤ የተዳከመ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም፤ ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩ የሰላም እጦቶች ፤ ከዚያም አልፎ በሀገረ መንግሥቱ ላይ በግልጽ የታወጁ ጦርነቶች ፤ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነበሩ።
መንግሥት ችግሮችን ለመቀልበስ ገና ከጅምሮ ሀገር በቀ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ እና በጠንከራ ዲሲፕሊን እንዲመራ በማድረግ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከነበረበት ስጋት ወጥቶ ፤ እንደሀገር ላለፉት ስድስት ዓመታት ያጋጠሙንን ፈተናዎችን ተሸክሞ መሻገር የሚያስችል አቅም እንዲፈጥር ማድረግ ችሏል ። ከዚያም አልፎ አሁን ላይ የሕዝባችንን የመልማት እና የመበልጸግ መሻት እውን ማድረግ በሚያስችል ተስፋ ሰጪ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንዲገኝ አስችሏል።
የሀገርን ሀብት አጥንቶ ከማወቅ የሚጀምረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው ፤ ሀብቶችን በተቀናጀ መንገድ ማልማት እና ልማቶችን ጠብቆ የማስቀጠል ስትራቴጂክ እይታ የተላበሰ ነው። የተወሰኑ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አቅሞች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ፤ የመልማት ዕድሎችን አውን ማድረግ የሚያስችሉ አቅሞችን አስፍቶ መጠቀምን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ ፖሊሲው የልማት አቅሞችን ተጨባጭ በማድረግ ሂደት ውስጥ የሀገር ውስጥ እና የውጪ የሀብት ምንጫችን አሟጦ መጠቀም የሚያስችሉ፤ አዳዲስ እሳቤዎችን ፤ ሕጎች እና የአሠራር መመሪያዎችን ተግባራዊ ያደረገ ነው። ውስን ሀገራዊ ሀብትን ውጤታማ ለሆኑ የተመረጡ ፕሮጀክቶች የማዋል አዲስ ዕይታን ይዞ የመጣ እና በዚህም ውጤታማ መሆን የቻለ ነው።
ለዚህም ግብርና ተኮር የነበረውን የቀደመውን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አተያያይ በመለወጥ ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቱሪዝም ፣ በግብርና ፣ በኢንዱስትሪ ፣ በማዕድን እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ስትራቴጂክ ትኩረት እንዲያደርግ ረድቷል፤ በዘርፉ ያሉ ሀገራዊ አቅሞችን በተጨባጭ በማልማት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስችሏል።
በግብርናው ዘርፍ በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኩታ ገጠም እርሻ ፤ በሩዝ ልማት የተመዘገቡ ስኬቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው ። በቱሪዝም ዘርፍ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ፣ በኮሪዶር ልማት የተገኘው ውጤት ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዛት ያላቸውን ጎብኚዎች በመሳብ ተጠቃሽ እንድትሆን አድርጓታል ።
ሀገሪቱ በማዕድኑ ዘርፍ ያላትን አቅሞች በተሻለ መልኩ እንድትጠቅም አሰችሏል። ለዚህም በድንጋይ ከሰል ፣ በከበሩ ማዕድናት፤ በኦፓል እና በወርቅ ያላትን አቅሞች በተሻለ መልኩ በጥራት እና በብዛት ወደ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል መልካም ዕድል እየፈጠረ ነው።
በቴክኖሎጂም ቢሆን በዲጂታል ኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትን ከማዘመን ጀምሮ አገልግሎቶች አስተማማኝ በሆኑ የቴክኖሎጂ አቅሞች እንዲጎለብቱ ማድረግ ተችሏል ፤ ሀገሪቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆና የምትወጣበትን ሁኔታ መፍጠር በሚያስችል ጅማሬ ውስጥ ትገኛለች። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት በብዙ መልኩ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተጨባጭ መረጃዎች የሚያመላክቱት ነው።
ለሁለንተናዊ ልማት የሚያስፈልገውን ሀብት በማሰባሰብ ሂደትም ፤ የታክስ ሥርዓቱን ከማዘመን ባለፈ ፤ የታክስ መሠረቶችን ለማስፋት እየተደረገ ያለው ርብርብ ተስፋ ሰጪ ነው ፤ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በጥራት እና በፍጥነት በመፈጸም እንደሀገር እየተፈጠረ ያለው አዲስ ባህል ፤ መንግሥታዊ ሙስናን ከማስቀረት ባለፈ፤ ሙስናንን መከላከል የሚያስችሉ አዳዲስ ሕጎችን ተግባራዊ በማድረግ ኢኮኖሚው የሚመነጨውን ሀብት ለሀገር ዕድገት ለማዋል እየተደረገ ያለው ጥረት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ይገኛል
ባለፉት ስድስት ዓመታት መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እየሠራቸው ያሉ ስኬታማ ሥራዎች አሁን ላይ ሀገራዊ የዕዳ ጫናን ትርጉም ባለው መንገድ መቀነስ አስችሏል፤ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት ለማከናወን የተሻለ ዕድል ፈጥሯል። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለተከታታይ ዓመታት ዕድገት እንዲያስመዘግብ ረድቷል። ይህም ዓለም አቀፍ እውቅና ፤ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ተዓማኒነት እንዲኖራት አስችሏል። ለልማቷ የሚያስፈልገትን ሀብት እንድታገኝም የተሻለ እድል ፈጥሮላታል!
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም