በዛሬው ርእሰ ጉዳያችን ላይ ስለ ገንዘብ ያለንን አመለካከት የሚቃኝ አጭር ቆይታ ለማድረግ ወድጃለሁ። በተለይ ገንዘብ እና ገንዘብ ይዞት ስለሚመጣው ነፃነት (financial freedoms) ትኩረት አድርጌ ጥቂት ለማለት ፈቅጃለሁ። ዛሬ የማነሳቸው እነዚህ ነጥቦች በተለይ በገንዘብ ዙሪያ ሊኖረን ስለሚገባ አመለካከትና አስተሳሰብ (financial mindset) የሚሉን ነገር ይኖራል። ቀደም ሲል የነበረንን አስተሳሰብ በማረቅና ትክክለኛው ምልከታ ምን መሆን እንደሚኖርበት ከማመላከት አኳያ ጠቃሚ መልእክቶችን እንደሚከተለው ያጋሩናል።
አስተሳሰብ እና የገንዘብ ነፃነት
በሕይወታቸው ላይ ጠንካራ የሥራ ባሕልን በመፍጠር እና ስኬታማ ሕይወት በመምራት የሚታወቁ ግለሰቦች በገንዘብ፣ በአጠቃቀምና በጥቅሉ ስለገንዘብ ባላቸው መልካም እሳቤ ውጤታማ ናቸው። በዚህ ምክንያት ግባቸውን ለማሳካትና የሚፈልጉትን ሕይወት ለመምራት ችለዋል። ከእነዚህ ስኬታማ ሰዎች በገንዘብ ላይ ያለህን አመለካከት መቀየር እንዴት በቀጣይ ለሚኖርህ ንግድም ሆነ ሀብትህን የመምራት ብቃት ብዙ መማር ትችላለህ። የዛሬው የተስተካከለ እሳቤም ለወደፊቱ ሕይወትህና ግብህ ስኬት ላይ መድረስ ጉልህ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ወጣቶች የተሻለ የገንዘብ ነፃነት እና የአጠቃቀም ብልህነት (financial freedoms) እንዲኖራቸው ያልማሉ። ሕይወታቸውን ማሻሻል፣ ቤተሰባቸውን መደገፍ እና ነገን የበለጠ ብሩህ አድርገው መገንባት ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ የፋይናንስ ነፃነትን ማግኘታቸው ብቻ በቂ አይደለም። ገንዘብ ከማግኘት ጎን ለጎን በጣም አስፈላጊ ጉዳይ አለ። እርሱም በገንዘብ ዙሪያ ያለን አመለካከትና እሳቤ ማስተካከልን ይጠይቃል።
ለገንዘብ እና ከእርሱ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ሀብር የሚኖረን አስተሳሰብ በጥቅሉ ቀጣይነት ወዳለው ስኬትና ወደ ሕይወት ግባችን የሚያደርሰን ነው። ይህ ማለት ገንዘብን ከማግኘት፣ በአግባቡ ለትክክለኛው ጉዳይና ጊዜ መጠቀምን እንዲሁም የገንዘብ አወጣጥና አስተዳደራችንን፣ ለገንዘብ ያለንን እምነት፣ አመለካከት እና ልማዶች ያካትታል።
ለምሳሌ ገንዘብ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው ብለህ ታምናለህ? ወይስ ገንዘብን የማግኘት እድሎች በሁሉም ቦታዎች አሉ ብለህ ታስባለህ? እነዚህ እሳቤዎችህ በገንዘብ ዙሪያ ያለህን አመለካከት ይቀርፃሉ። ብዙ ሰዎች ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሀብት ለጥቂት እድለኞች ብቻ ነው›› ብለው ያምናሉ። ብዙ ወጣቶች ዝቅተኛ ደመወዝ በሚከፈልባቸው ሥራዎች ውስጥ እንደተቀረቀሩ ወይም ሥራ አጥ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ነገር ግን ስለ ገንዘብ ያለህን አስተሳሰብ (አመለካከት) በመቀየር ብቻ አዳዲስ እድሎችን ማማተር እንድትችል በር መክፈት ትችላለህ።
አስተሳሰብ እና ድርጊት
አስተሳሰብህ በድርጊትህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ‹‹ገንዘብ ለማግኘት ከባድ ነው›› ብለህ ካሰብክ ድፍረት የሚጠይቁ ርምጃዎችና ውሳኔዎችን ከማድረግ፤ አዳዲስ ክህሎቶችን ከመማር ትቆጠባለህ። በሌላ በኩል ተቃራኒ የሆነ አመለካከት ይዘህ ገንዘብ ለማግኘት ቀላል እንደሆነ ካመንክ አሊያም በቀላሉ ሰርተህ እንደምታገኝ ካሰብክ እራስህን በየጊዜው ለማሻሻል፣ ክህሎቶችህን ለማዳበር፣ እንዲሁም ሁሌም ጠንካራ የሥራ ባሕል እንዲኖርህ ትሠራለህ። ይህ እርምጃህ ደግሞ የአንተን የፋይናንስ ሁኔታ እንዲሻሻል በር ይከፍታል። በቀላሉ እድሎችን አታባክንም አጋጣሚዎችን ወደራስህ በመውሰድ የምትፈልገውን የፋይናንስ ነፃነት ማግኘት ትጀምራለህ።
ለምሳሌ ዛሬ ላነሳነው ርዕሰ ጉዳይ የሚሆን አንድ ታሪክ ላጫውትህ። እነዚህ ባለታሪኮች ሁለት በተለያየ አቅጣጫና እሳቤ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ናቸው። መቅደስ ሥራዋ በጣም ትንሽ ስለሆነ ገንዘብ መቆጠብ እንደማትችል ታምናለች። የምታገኘውን ሁሉ ታጠፋለች፤ ብዙ ጊዜም ገንዘብ ከቤተሰቦቿና ጓደኞቿ ትበደራለች። ዮናስ ገቢው ልክ እንደ መቅደስ ነው። ነገር ግን ትንሽ ገንዘብ መቆጠብ ለውጥ እንደሚያመጣ ያምናል። በቀን 10 ብር መቆጠብ ይጀምራል። በተጨማሪም ስለ ኢንቨስትመንትና ንግድን እንዴት በቀላሉ መጀመር እንደሚቻል ይማራል። በጊዜ ሂደት የዮናስ አስተሳሰብ ወደስኬት ይመራው ጀመር። የቆጠበው ገንዘብ በንግድ ሥራ ሃሳብ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ይረዳዋል። በቀላሉም የስኬት በሮች ይከፈቱለት ይጀምራሉ። በተቃራኒው መቅደስ በእዳ አዙሪት ውስጥ እንደተቀረቀረች ትቀራለች።
የሁለቱ በባለታሪኮቻችን አስተሳሰብ ድርጊቶችን እና ውጤቶች እንዴት እንደሚቀርፁን እና የመጨረሻ ግባችን ምን እንደሚመስል በቀላሉ ያሳየናል። በመሆኑም በሕይወታችን ላይ ስኬታማ ለመሆን፣ በቀላሉ ገንዘብ አግኝተን ኑሯችንን ቀና ለማድረግ አስተሳሰባችን ቀና መሆን እንዳለበት ያመላክተናል። በመሆኑም አንተም በሕይወትህ ላይ ገንዘብን ማግኘትና በቀላሉ ማስተዳደር እንድትችል በቅድሚያ እሳቤህን ማስተካከል ይኖርብሀል።
በጎ ጎንን መመልከት
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ወጣቶች ስለሌላቸው ነገር በማሰላሰል ብዙ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ፤ በተለይ ከፍተኛ የሆነ የእጥረት አስተሳሰብ አላቸው። ይህ ማለት በሌለው ነገር ላይ ማተኮር ማለት ነው። ለምሳሌ “ማጠራቀም ለመጀመር በቂ ገንዘብ የለኝም” “በአካባቢዬ ጥሩ ሥራዎች የሉም” ወይም “ሀብታሞች ብቻ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት” ብለው በተደጋጋሚ በዚህ እሳቤ ውስጥ ይቆያሉ። ይህ አስተሳሰብ አዳዲስ ነገሮችን ከመሞከር ወይም ሁኔታዎን ለማሻሻል ርምጃዎችን ከመውሰድ ያግዳቸዋል፤ በውስጣቸው ፍርሃትንም ይፈጥራል፣ አቅማቸውም የተገደበ ይሆናል።
በተቃራኒው በጎ በጎውን የሚያሰላስሉና ሁሌም እድሎችን ወደ ራሳቸው የሚስቡ ሰዎች ከላይ ያነሳናቸው አሉታዊ ጉዳዮች ላይ አብዝተው አይጨነቁም። መልካም አስተሳሰብ እና እድሎች ላይ ያተኩራሉ። ምንም እንኳን ከትንሽ ቢጀምሩም ሀብትን መፍጠር እንደሚችሉ በመተማመን ጠንክረው ይሠራሉ። የተትረፈረፈ አስተሳሰብ በመያዝ “በየሳምንቱ ትንሽ መጠን እንኳን መቆጠብ እችላለሁ” “አዲስ ክህሎቶችን ከተማርኩ የተሻሉ የሥራ እድሎችን አገኛለሁ” ወይም “የወደፊቴን ለማሳደግ ጊዜዬን እና ጥረቴን ኢንቨስት ማድረግ እችላለሁ” በሚል አዎንታዊ እሳቤ የተሞሉ ናቸው። የተትረፈረፈና አዎንታዊ አስተሳሰብ ማለት ተግዳሮቶችን ችላ ማለት አይደለም። በምትኩ መፍትሔዎች ላይ በይበልጥ ማተኮርና ደፋር ርምጃ ለመውሰድ የሚረዳ አስተሳሰብን በውስጥህ መቅረፅ ማለት ነው። በመሆኑም አንተ የእነዚህ ዓይነት ስኬታማ ሰዎች አስተሳሳብ እንዲኖርህና የገንዘብ ነፃነት አግኝተህ አላማህን ከግብ እንድታደርስ በቅድሚያ አዎንታዊ አስተሳሰብ መገንባት እንዳትረሳ።
አመለካከትን እንዴት እንቀይር
ስለ ገንዘብ ያለዎትን አስተሳሰብ (አመለካከት) መቀየር አሉታዊ እምነቶችን በማወቅ እና በመቃወም ይጀምራል። በመሆኑም አንተም የዚህ እሳቤ ባለቤት ለመሆን ስለ ገንዘብ ያለህን ሃሳብ በመለየት መጀመር ይኖርብሃል። ለመሆኑ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ እሳቤ የምንላቸው እሳቤዎች የትኞቹ ናቸው? ለምሳሌ “በፍፁም በቂ ገንዘብ አይኖረኝም” ብለህ ካሰብክ ይህ እምነት አሉታዊ መሆኑን እወቅ አሊያም በርግጥም እሳቤህ እውነት እንደሆነ እራስህን ደጋግመህ መጠየቅና ማረጋገጥ አትዘንጋ። አዎንታዊ እሳቤ የዚህ ተቀራኒ ነው። በመሆኑም አሉታዊ እሳቤ በውስጥህ ሲዳብር “ገንዘብ በቀላሉ ሰርቼ ማግኘትና በተሻለ ሁኔታ ማስተዳደርን መማር እችላለሁ” በሚል አወንታዊ እሳቤዎች ቀይር። በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ካለህ ገንዘብ መቆጠብ የማይቻል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ነገር ግን በቀን አንድ ብር እንኳን መቆጠብ ለውጥ እንደሚያመጣ ማወቅ ይኖርብሃል። ዛሬ ላይ ውጤት እንደማያመጡ የገመትኳቸው ርምጃዎችና ትናንሽ ቁጠባዎች ያድጋሉ። በመሆኑም የመቆጠብ ልምድ ይኑርህ፤ ገንዘብህን በየጊዜው ማሳደግ ጀምር። በኢትዮጵያ እንደ “እቁብ” ዓይነት ባሕላዊ የቁጠባ ማህበራዊ አደረጃጀቶች አሉ። በቀላሉ ወደ ስኬት ለመሄድ እቁብ መጀመር ጥሩ መንገድ ነው።
እውቀትና የገንዘብ አስተሳሰብ
እውቀት ሌላው የስኬት መሳሪያ ነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን ገንዘብን እንዴት ማስተዳደር እንደሚችሉ አያውቁም። ምክንያቱም ማንም አላስተማራቸውም። ስለ በጀት ማውጣት፣ ቁጠባ እና ኢንቨስት ስለማድረግ ሲያስቡና ርምጃ ሲወስዱ አይታይም። ወጣቶች አሁን ላይ በቀላሉ ገንዘብ ስለመቆጠብ፣ ስለአስተዳደር፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ከማህበራዊ ሚዲያ መማር እንዲችሉ እድሉ ተፈጥሮላቸዋል። ወይም በማህበረሰብ ወርክሾፖች ላይ መገኘት ይችላሉ። በመሆኑም ይህንን እድል ሊጠቀሙ እና የእውቀት አድማሳቸውን ሊያሰፉ ይገባል።
ገንዘብን ከማግኘት በትክክል ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ ግልጽ ግቦችን ማውጣትም አስፈላጊ ነው። ለወደፊትህ የፋይናንስ ራዕይ መኖሩ ተነሳሽ እንድትሆን ያደርግሃል። ለምሳሌ በስድስት ወራት ውስጥ 10 ሺ ብር ለመቆጠብ፣ በዓመት ውስጥ አነስተኛ ንግድ ለመጀመር ወይም ዕዳውን በተወሰነ ቀን ለመክፈል ዓላማ አድርግ። እነዚህን ትልልቅ ግቦች ወደ ትናንሽና ሊተገበሩ ወደሚችሉ ደረጃዎች ከፋፍላቸው። በሂደቱ በምታገኘው ውጤት አዎንታዊ እሳቤን አዳብር።
ሌላው መልካም ከባቢን መፍጠር እውቀትና አዎንታዊ አስተሳሰብን ለማዳበር ይረዳሀል። አንተ ሁሌም ለተሻለ ለውጥና እውቀት ከሚያነሳሱ፤ በምታሳየው እድገትና የለውጥ ሂደት በጎ ምልከታ ካላቸውና ከሚያምኑህ ሰዎች ጋር ጊዜህን ማሳለፍ ይኖርብሃል። ከተሳካላቸው ሰዎች እንድትማር ውሎህም ከእነዚህ ሰዎች ጋር መሆን ይኖርበታል። በመሆኑም ጥረትህን የሚያደናቅፉ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ማስወገድ እንዳትዘነጋ።
የፋይናንስ ነፃነት ማለት ሀብታም መሆን ማለት አይደለም። ገንዘብዎን መቆጣጠር እና ፍላጎቶችዎን ማሟላት መቻል ማለት ነው። ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች የፋይናንስ ነፃነት ማግኘታቸው ውጥረትን ይቀንሳል፣ የአዕምሮ ጤናን ያሻሽላል፣ ቤተሰብን እና ማህበረሰቦችን ለመደገፍ፣ የትምህርት እና የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም ሌሎች ገንዘባቸውን እንዲቆጣጠሩ ሊያነሳሳ ይችላል። ወጣቶች የገንዘብ ነፃነት ሲያገኙ ለሌሎች አርአያ ይሆናሉ። ይህም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳይ ነው። በመሆኑም አንተም የፋይናንስ ነፃነት እንዲኖርህ ከላይ በዝርዝር የተቀመጡ ርምጃዎችን በድፍረት ውሰድ።
ስለ ገንዘብ ያለህን አስተሳሰብ መቀየር የፋይናንስ ነፃነት ለማግኘት የመጀመሪያው ርምጃ ነው። ይህንን ለማሳካት ጥረት ይጠይቃል። ነገር ግን መጨረሻው ያማረና ዋጋ ያለው ሽልማት ታገኝበታለህ። የኢትዮጵያ ወጣቶች አቅማቸውን በማመን፣ ትናንሽ የለውጥ ርምጃዎች በመውሰድ እንዲሁም ግባቸው ላይ በማተኮር የተሻለ ወደፊት ለመፍጠር የሚያስችል ኃይል መገንባት መጀመር አለባቸው።
በመጨረሻም አንድ ነገር አስታውስ የፋይናንስ ነፃነት ‹‹ምን ያህል ገንዘብ አለህ›› ማለት አይደለም። የፋይናንስ ነፃነት አሉታዊ የሆነውን እምነትህን በመቃወም፣ የምትችለውን በመቆጠብ ወይም በማስቀመጥ እንዲሁም ስለ ገንዘብ አያያዝ በመማር የምታገኘው ጠንካራ እሳቤ ነው። በመሆኑም ወደዚህ የነፃነት ጉዞ ለመድረስ የምትጀምረው በአንድ ርምጃ እና በትክክለኛው አስተሳሰብ መሆኑን ጠንቅቀህ እወቅ። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም