
እንደ ሀገር ከፍ ብሎ የሚታየውን ዘርፈ ብዙ ፍላጎት ለመመለስ እንዲቻል፤ ይህንን ታላቅ ተግባር የሚያሳኩ አቅጣጫዎችን ነድፎ መንቀሳቀስ ይገባል:: በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለዘመናት ታሰበው ያልተተገበሩ እንደ ዓባይ ግድብ ዓይነት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርጋ እነሆ ዛሬ ከፍጻሜው ፍጻሜ ላይ ደርሷል::
ይሄ ግድብ እንደ ሀገር የዘመናት ጥያቄን የመለሰ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን አንድነትና የማድረግ አቅም የገለጠ ነበር:: በተለይ በዲፕሎማሲው መስክ የተከናወኑ ሥራዎች፤ በየአቅጣጫው ይደርስ የነበረውን ክስና ጫና ተቋቁሞና አሸንፎ ከማለፍ አኳያ የነበረው ድርሻ ከፍ ያለ ነው::
በዚህ የተነሳም ታሪካዊ ጠላቶቻችንና የኢትዮጵያ ብልፅግና የማይዋጥላቸው ሀገራት በየአቅጣጫው ጫጫታና ክስ ጀመሩ:: አጋሮቻቸው ሀገራትና ተቋማትም ዘርፈ ብዙ ጫና ማስደረግ ሥራቸው አደረጉ:: ሌላው ቀርቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሳይቀር በውሃ ላይ በተከናወነ የልማት ጉዳይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከስሳ ጉዳዩዋን ለማስረዳት የቀረበችበት አጋጣሚ ተፈጥሯል::
ይሄ ሁሉ ጫና፣ ክስና ወቀሳ ታዲያ አንድም እንደ መንግሥት በተሠራው ከፍ ያለ ሥራ፤ ሁለተኛም በየቦታው ባሉ ኢትዮጵያውያን ጥረት፤ ሦስተኛም፣ በሕዝቡ የውስጥ ትብብርና የነቃ ተሳትፎ ታግዞ እና ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ሴራው ተሸንፎ ሂደቱ በስኬት ቀጠለ:: እናም ዓባይ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረና ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ሥራ እውን ሆኖ ሕዝቡ የፍጻሜውን ብሥራት እየተጠባበቀ ይገኛል::
በዚህ መልኩ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ጥያቄን እና የሕዝቦች ፍላጎትን ለመመለስ የሚደረገው ጥረት፤ ዛሬ ደግሞ በመልክዓ ምድራዊ ተፈጥሮም፣ በታሪክም፣ በሕግም ፊት ቅቡልነትን በሚያስገኘው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታጅቦ ጉዞ ጀምሯል:: ምክንያቱም፣ ትናንት የቀይ ባሕር ቀጣናን በበላይነት ትዘውር የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ለቀይ ባሕር ባይተዋር ሆናለችና::
ይሄ ባይተዋርነቷ ብቻም ሳይሆን፣ እንደ ሀገር በሕዝብ ቁጥሯ እያደገች፤ በኢኮኖሚዋም እየተመነደገች፤ የወጪና ገቢ ምርቷም እያሻቀበ፤ ሀገራዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳይዋም ከፍ ያለ ፍላጎትን እየወለደ ያለችበት ወቅት ነው:: በዚህ ምክንያትም፣ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ፣ የማህበራዊም፣ የፖለቲካዊም፣ የኢኮኖሚያዊም በጥቅሉ የልማትና ደኅንነቷ ጉዳይ ሆኗል:: ከዚህ አለፍ ብሎም የህልውናዋ ጉዳይ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል::
ይሄን መነሻ በማድረግም ነው ኢትዮጵያ ከፍ ያለ መሻቷን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ የሕግም፣ የታሪክም፣ የመልክዓ ምድራዊ እውነታንም አጣቅሳ የባሕር በር ባለቤት የምትሆንበትን አማራጮች ሁሉ አስቀምጣ በሰላማዊ መንገድ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ይህንን ወሳኝ ጉዳይ እውን ለማድረግ ለጎረቤቶቿ ሁሉ ጥያቄዋን ያቀረበችው::
ይሄ ጥያቄ ታዲያ መንገዱ ሰላማዊ፣ መርሁ የጋራ ሀብትን በጋራ አልምቶ አብሮ የመበልጸግ፤ ግቡ ደግሞ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ልዕልናን ብሎም ብልፅግናን እውን ማድረግ ነው:: ይሄ ደግሞ በዓባይ ግድብ ላይ የታየ፤ የኢትዮጵያን የጋራ ሀብትን አብሮ የማልማትና የእድገት አቅም የማድረግ እሳቤን በተግባር የሚገልጥ ነው::
በዚህ ጥያቄ መነሻነትም፣ እሳቤ፣ መንገድና ግቡን የተረዱ ምላሽ አጥተዋል:: ለጊዜው የተደናገሩም በሂደት ጉዳዩ ሲገባቸው አዎንታዊ መንገድን ጀምረዋል:: ያልገባቸውና ቀድሞውንም የኢትዮጵያ ከፍ ማለት የሚያምማቸው ኃይሎች ደግሞ ዛሬም በወቀሳና ክስ ተግባራቸው ቀጥለዋል::
ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያ ጥያቄዋ በመልካም መንገድ እየተጓዘ፤ በጅምር ውጤቶችም እየታጀበ መቀጠሉ ነው:: ምክንያቱም ጥያቄዋ ቀደም ሲል በሶማሊ ላንድ በመግባቢያ ስምምነት ጭምር በታገዘ መልኩ፤ አሁን ደግሞ በሶማሊያ አዎንታዊ ምላሽ ታግዟልና::
ይሄ እንዲሆን ደግሞ ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሠርቷል:: የሀገራት ድጋፍና አጋርነትም ተገልጿል:: ለምሳሌ፣ ሶማሊያ በዚህ ላይ አዎንታዊ ምልከታ እና ምላሽ እንዲኖራት በማስቻል በኩል በቱርክ መንግሥት የነበረው የማወያየት ሚና ጉልህ ነበር:: ይሄው ሚና ዛሬም ድረስ የዘለቀ ነው::
ከዚህ በተጓዳኝ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች ይሄንኑ የኢትዮጵያን ጥያቄ በአዎንታዊ መልኩ ተቀብለውታል:: ለምሳሌ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎችም የምዕራቡ ዓለም ሀገራት፤ ብሎም የምሥራቅ እና የሩቅ ምስራቅ ሀገራት የኢትዮጵያን በሰላማዊ አማራጭ ላይ ያተኮረ የባሕር በር ጥያቄ እንደሚደግፉት አረጋግጠዋል::
ከሰሞኑም ስዊድን ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አረጋግጣለች:: ስዊድን ይሄን የገለጸችው፤ በፓርላማ አባሏና የመከላከያ ኮሚቴ ምክትል ኃላፊዋ ያስሚን ኤሪክሰ በኩል ነው:: ኃላፊዋ እንዳረጋገጡትም፤ ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ስ ዊድን ትደግፋለች።
ይሄን መሰል የሀገራት ድጋፍና አጋርነት ታዲያ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም:: ይልቁንም፣ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ሠርታ እየተለወጠች ያለችበት መንገድን በመገንዘብ ነው:: በሌላ በኩል የሕዝቦች አብሮነትና መተባበር የፈጠረው ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የማጽናት ግስጋሴ ነው:: ከዚህ ሁሉ ጀርባ ደግሞ ቀጣናው ትብብርና ብልፅግናን እውን ከማድረግ አኳያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተሳስሮና ተባብሮ የመሥራት መንገዷን በመገንዘብ ነው::
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም