
አዲስ አበባ፡- “የቤት ልማት ፋይናንስ እጥረትን በማቃለል የመኖሪያ ቤት ችግርን ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታት በትኩረት ይሠራል” ሲሉ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሔለን ደበበ አስታወቁ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሔለን ደበበ የቤት ፋይናንስ ሥርዓት ዝርጋታ የጥናት ማጎልበቻ መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ያለው የቤት ብዛት ዝቅተኛ እንደሆነ እና ያሉትም ቢሆኑ ያረጁ፣ የተጠባበቁና ከደረጃ በታች የሆኑ ናቸው። ለዚህ ችግር በርካታ መንስኤዎችን መጥቀስ ቢቻልም ዋናው ግን የቤት ፋይናንስ እጥረት ነው ብለዋል።
የቤት ልማት ፋይናንስ እጥረትን በማቃለል የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ትርጉም ባለው መልኩ እንዲሻሻል ይደረጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ራሱን የቻለ የቤት ፋይናንስ ምንጭና የአቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ሀገር አቀፍ የቤት ፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ጥናት በማከናወን ራሱን የቻለ የሕግ ማሕቀፍ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቤት ለሰው ልጅ መጠለያ ብቻ ሳይሆን እሴት፣ የሥራ ቦታ፣ የመዝናኛ ሥፍራ፣ የማህበረሰብ ማንነት ደረጃ መገለጫ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ይህንን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ላይ በተደነገገው መሠረት የሀገሪቷ አቅም በፈቀደ መጠን ለዜጎች የመኖሪያ ቤቶችን ለማቅረብ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በቤት ልማት ዘርፍ በተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ መሠረት አበረታች ውጤቶች ተገኝቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በአጠቃላይ በከተሞች ከሚጠበቀው የቤት ፍላጎት አንጻር አሁንም ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሀገር አቀፍ የቤቶች ልማት ፋይናንስ ሥርዓት ወደ ትግበራ ሲገባ ለአዳዲስ ቤቶች ግንባታ፣ ለቤቶች ጥገናና ማሻሻያ እንዲሁም ለተያያዥ የቤት ልማት ፕሮግራሞች የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ በማገልገል እንደ ሀገር የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እንዲሻሻል የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል።
የፋይናንስ ሥርዓቱ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ እድገትን በማጎልበት እና ድህነትን በመቀነስ ዜጎች የቋሚ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚረዳ ፣ የኑሮ ሁኔታን የሚያሻሽል ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ሁኔታቸውን እንዲያጎለብቱ እድል የሚፈጥር እንደሆነ አስረድተዋል።
የቤት ልማት ሥራው በፍጥነት እየጨመረ የሚሄደውን የከተማ ሕዝብ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ሲንከባለል የመጣውን የቤት ችግር ለመቅረፍ የሚጠቅም ነው ብለዋል።
ከቤት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ከቤት አልሚዎች፣ ከመሬት ልማትና አቅርቦት ተቋማት፣ ከከተማ ፕላን፣ ከዘርፉ ሙያተኞችና ከመሰል ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሄለን ደበበ ተናግረዋል ።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም