
የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ጉዞ መነሻ እየተደረገ በታሪክ የሚነሳው የ40ዎቹ የአርመን ልጆች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እና የማርች ባንድ ማቋቋም ነው። ይሁን እንጂ ገና በአጼ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ቡድን የማቋቋም ሙከራዎች ነበሩ።
ፍራንሲስ ፋልሴቶ ስለ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ጉዞ በጻፈው ማስታወሻ ይህን ሃሳብ አስፍሯ፦ አጼ ምኒልክ ዓድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ካደረጉ በኋላ የሩሲያ ዛር (tsar) ንጉሡን እጅ ለመንሳት አምባሳደራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ።
አምባሳደሩ ለንጉሡ ይዞ ከመጣው እጅ መንሻ መካከል 40 የብራስ የሙዚቃ መሳሪያዎች ይገኙበት ነበር። የእነኚህን የሙዚቃ መሳሪያ የአጨዋወት ሞያ ለማሰልጠን ደግሞ ሚሌውስኪ (Milewski) የተባለ የሙዚቃ መምህር አብሮ ተልኮ ነበር። ሚሌውስኪም ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ሙዚቃ ለማስተማር ጥረት ያደርግ ነበር።
ከዚህ ከፋልሴቶ ማስታወሻ እንደምንረዳው የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ጉዞ በር ከፋች ጭምር ነበር። እነኚህ ከላይ የተጠቀሱት የታሪክ አጋጣሚዎች እንዳሉ ሆነው በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ እጅጉን ያበበበት እና ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዘመን ከ1947 ዓ.ም. እስከ አብዮት ፍንዳታ ድረስ ያሉት ሃያ ዓመታት ናቸው።
እኚህ 20 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዓመታት ነበሩ። ቀደም ብለው ተቋቋመው የነበሩት የተለያዩ ወታደራዊ ባንዶች ምርጥ ምርጥ ድምጻዊያንን በመመልመል አዳዲስ ሙዚቃዎችን እያጠኑ ብቅ ማለት ሲጀምሩ የአጼ ኃይለሥላሴ እና የሀገር ፍቅር ትያትር ቤቶችም መድረኩን በመቀላቀል ምርጥ ምርጥ ሙዚቃዎችን እያዘጋጁ ማቅረብ ጀመሩ።
በ1950ዎቹ መጨረሻ እና በ1960ዎቹ እንደ ራስ ባንድ ያሉ የግል ባንዶች በብዛት መቋቋም ጀመሩ። ይህ ጊዜ የተለያዩ እውቅ ሙዚቀኞች ወደ መድረክ የመጡበት እና የኢትዮጵያ ባሕላዊ ሙዚቃ ከምዕራቡ ዓለም ሙዚቃ ጋር እየተዋሃደ የራሱን ቀለም እና መስመር መያዝ የጀመረበት ጊዜ ነበር።
ዛሬ ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ማንሳታችን ያለ ምክንያት አይደለም። ከሀገራችን እውቅ ድምፃዊያን ጀርባ ሆኖ ዘመን አይሽሬ የሙዚቃ ሥራዎች ያበረከተውን አንድ የኢትዮጵያ ባለውለታ ለማመስገን በማሰብ እንጂ።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ ሲነሳ ስሙ አብሮ ይነሳል። በተለይም ከ1960ዎቹ ጀምሮ ባሉት ዘመናት ውስጥ በተሠሩ ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎች ውስጥ የዚህ ድርጅት ዐሻራ በጉልህ ታትሞ ይታያል።
እ.አ.አ በ1973 ዓ.ም. በባለሀብቱ ዓሊ ታንጎ አማካኝነት ተመሥርቶ ወደ ኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የተቀላቀለው ካይፋ ሪከርድስ (kaifa records) ከነ አምሃ ሪከርስድስ እና ፒሊፕስ ሪከርድስ ጋር በመሆን የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ምሰሶ ሆነው ታላቅ ውለታን ውለዋል።
ዓሊ ታንጎ ማነው?
ዓሊ ታንጎ ከየመኒ አባቱ እና ከኢትዮጵያዊት እናቱ ጅማ ከተማ ነው ተወልዶ ያደገው:: የመኒው የአሊ አባት የታወቁ ቡና ነጋዴ ነበሩ። አሊ ከነጋዴ አባቱ ጋር ሥራ እያገዘ ማደጉ ከአባቱ ጠንካራ የሥራ ባሕልን እንዲወርስ እንደረዳው ይናገራል።
ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በመጀመሪያ በየመኒ ማኅበረሰብ ት/ት ቤት (Yemeni community school) ቀጥሎም በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል።
ዓሊ ገና በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ እያለ ነበር አባቱ ላይመለስ ወደ የመን ያቀናው። ይህን ጊዜ የአሊ እናት ሌላ ባል አግብታ ኑሮዋን ትጀምራለች። አዲሱ የአሊ እንጀራ አባት እንደ አባት ሁሉ በቡና ንግድ ላይ የተሠማራ ሰው ነበር። አሊም የሚያውቀውን የቡና ንግድ የእንጀራ አባቱን እየረዳ ቆየ።
በአዲስ አበባ የነበረው የጦፈ የቡና ገበያ እየቀዘቀዘ ሲመጣ አሊ ሥራ መፈለግ ነበረበት። ቀጥሎ አሊ የሶፎሊኒ ጫማ ካምፓኒ (Cipollini Shoe Company) ኤጀንት በመሆን ሲሠራ ለዓመታት ከቆየ በኋላ ዘርፉን በመቀየር የሶኒ ካምፓኒ ኤጀንት ሆነ። ዓሊ የሶኒ ካምፓኒ ኤጀንት በነበረበት ጊዜ የተፈጠረ አንድ አጋጣሚ ነበር የካይፋ ሪከርድን የወለደው::
አንድ ሰው ወደ አሊ የኤሌክትሮኒክስ መደብር ይመጣና የሶኒ ሪከርደር በዱቤ እንዲሸጥለት ይጠይቀዋል። አሊም ሰውዬውን በማመን የተባለውን እቃ በዱቤ ይሸጥለታል። በኋላ ሰውዬው እንኳን እዳውን ሊከፍል ከነአካቴው የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል።
የኋላ ኋላ አሊ አንድ መረጃ ከሰዎች ይደርሰዋል። በመረጃው መሠረት ሰውዬው በፒያሳ አካባቢ ካሊፕሶ የተባለ ሙዚቃ ቤት ከፍቶ እየሠራ ነበር። ዓሊ ሰውዬው ወዳለበት ሄዶ እዳውን እንዲከፍል ቢጠይቀው ሰውዬው ብዙ እዳ እንዳለበትና ያን ማድረግ እንደማይችል ይናገራል።
ዓሊም ‹‹ካልሆነ ሱቁን ሽጥልኝ እና እዳህን ክፈል›› የሚል ሃሳብ ያመጣና በሃሳቡ ይስማማሉ። ዓሊም ሙዚቃ ቤቱን ከገዛው በኋላ ለዓመታት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ዝነኛ ሆኖ የኖረውን ታንጎ ሙዚቃ ቤት ከፈተ።
ዓሊ በመጀመሪያ በታንጎ ሙዚቃ ቤት የተለያዩ የውጭ ሙዚቃዎችን እያስመጣ በመሸጥ ሥራውን ቢጀምርም በኋላ ላይ እንደ እነ አምሃ ሪከርድስ የራሱን የሙዚቃ ሪከርድስ የማቋቋም ሃሳብ ማውጠንጠን ጀመረ። ለዚህ ሥራው የሚረዳውን መሳሪያ ካሟላ በኋላ መጀመሪያ አብሮት እንዲሠራ የጠየቀው ድምጻዊ ጌታቸው ካሳን ነበር።
ይሁንና ጌታቸው ቀድሞ ከአምሃ ሪከርድስ ጋር ውል ስለነበረው ይህ ሃሳቡ ሊሰምርለት አልቻለም። ከጌታቸው ጋር አብሮ የመሥራቱ ነገር ባይሳካም የጌታቸው ሥራ በአምሃ ሪከርድስ ፕሮድዩስ ከተደረገ በኋላ ብዙ ቅጂዎችን ገዝቶ አስመራ ድረስ በማከፋፈል አሊን የተወዳደረው አልነበረም::
ዓሊ በኬፋ ሪከርድስ አማካኝነት ሙዚቃን ፕሮዲዩስ በማድረጉ በኩል የመጀመሪያ ሥራው የነበረው የዓለማየሁ ቦሮቦር ‹‹በላያ በላያ›› የተባለ ሥራ ነበር። ምንም እንኳን ብዙም በአድማጭ ዘንድ ተቀባይነት ባያገኝም። በኋላ የነ ስዩም ገብረየስ እና አያሌው መስፍን ሥራዎች ታትመው ሲወጡ በሰፊው አየሩን ተቆጠጠሩት።
በዚህም ኬፋ ሪከርድስም በደንብ በሁለት እግሩ መቆም ቻለ። ሙሉቀን መለሰ እና አሊ በመጀመሪያ አብሮት ለመሥራት ጓግቶለት የነበረው ጌታቸው ካሳም ኬፋ ሪከርድን ተቀላቀሉ። ‹‹ዝማም ሰው ለበኔ››፣‹‹እንዲህም እንዲህም››፣‹‹አልተገናኘንም እና ቆንጆ›› የተሰኙት ድንቅ ድንቅ ሥራዎች ከኬፋ ሪከርድስ ጓዳ መውጣት ጀመሩ።
እንዲህ እንደ ዛሬው ዝናዋ ሳይናኝ በፊት በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት በሙዚቃና ውዝዋዜ ታገለግል የነበረችውን አስቴር አወቀን አሊ በአንድ አጋጣሚ ስትዘፍን ያያታል። በድምጿ በመደነቁም አብረው እንዲሠሩ ሃሳብ ያቀርብላታል። በጊዜው ከአሊ ታንጎ ጋር መሥራት እንደ አስቴር አወቀ ላለ ጀማሪ ሙዚቀኛ ትልቅ እድል ስለነበር አስቴር በደስታ ነበር ጥያቄውን የተቀበለችው::
የአስቴር አወቀ ‹‹አንተዬ ሎሚዬ››፣ ‹‹ሙሉ››፣ ‹‹እትቱ በረደኝ››፣ የተሰኙ ሥራዎች በኬፋ ሪከርድስ ታትመው ሲወጡ ግን ተቀባይነታቸው የተጠበቀውን ያህል አልነበረም። ከታተመው ከግማሽ በላይ የሚሆነውም ሳይሸጥ ነበር የቀረው። ይህ የሆነበትን ምክንያት ዓሊ ለማጣራት ሲሞክር ያገኘው መልስ የአስቴርን የድምጽ አወጣጥ አልወደድነውም የሚል ነበር።
ኬፋ ሪከርድስ ከላይ ከተጠቀሱት አርቲስቶች በተጨማሪ የታምራት ፈረንጅን፣ ጥላሁን ገሠሠን፣ ሂሩት በቀለን፣ብዙነሽ በቀለን፣ ምኒልክ ወስናቸውን፣ አያሌው መስፍንን፣ ማህሙድ አህመድን፣ አሊ ቢራን፣ፀሐይ እንዳለን፣ እና አለማየሁ እሸቴን የመሳሰሉ ሥራዎችን አሳትሟል።
የድምፃውያንና የሙዚቀኞችን ሥራ ከኅብረተሰቡ ዘንድ በማድረስ ረገድ በዘመናዊቷ አዲስ አበባ ታሪክ ከሚጠቀሱት ውስጥ የሙዚቃ ቤቶች (መደብሮች) በቀዳሚ ይወሳሉ:: በ1960ዎቹ የሙዚቃ ሥራን በቴፕ ካሴቶች ማሳተምና ማሠራጨት ከመጀመሩ በፊት ሥራዎች ይቀርቡ የነበሩት በሸክላ ነበር::
በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች ባሕር ማዶ ድረስ በመዝለቅ ስማቸው ጎልተው ከተሰሙት ሙዚቃ ቤቶች ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ‹‹ታንጎ ሙዚቃ ቤት›› ነበር:: ኮከቧ ድምፃዊት አስቴር አወቀ ስትነሳ ከመጀመሪያዋ እስከ አምስተኛዋ ካሴት ድረስ አብሯት የሚነሳው ታንጎ ነው:: እንዲሁም ዓሊ ቢራ፣ ንዋይ ደበበ፣ (የጥቅምት አበባ) ወዘተ. ከታንጎ ጋር ስማቸው ይያያዛል::
ታንጎ ሙዚቃ ቤት የቆረቆረውና ሙዚቃን የማሳተምና የመነገድ ሥራ የገባው አቶ ዓሊ አብደላ ካይፋ (በቅጽል ስሙ ዓሊ ታንጎ) ነው:: ከሸክላ ማጫወቻ፣ ወደ ቴፕ ሪኮርደር ከቴፕ ወደ ሲዲ እየተሸጋገረ በመጣው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሂደት ውስጥ በተለይ ቀደም ባለው ዘመን በ1960ዎቹ አጋማሽና በ70ዎቹ ሙዚቃን በማሳተም አቶ ዓሊ አብደላ (ታንጎ) ተጠቃሽ ስም እንዳለው ይወሳል::
ታንጎ ሙዚቃ ቤት ካይፋ ሪከርድስ በተለይም ለወጣት ድምፃውያንና ለሌሎችም ዕውቅ ድምፃውያን ከ1965 ዓ.ም. እስከ 1969 ዓ.ም. ብቻ 53 የሙዚቃ ሥራዎችን አሳትሞ ለሕዝብ አቅርቧል:: ከዓሊ ታንጎ ታላላቅ ሥራዎች ተርታ የሚሰለፈው በ1978 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ውጭ ተቀርጾ በዓለም የተሠራጨው የማህሙድ አህመድ ኧረ መላ መላ ነው::
ዓሊ ታንጎ በሸክላ ያስቀረፃቸውን ሥራዎችና የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች በመውደዱ ‹‹ኢትዮጲስ›› በሚል የዘፈን ስብሰብ በማዘጋጀት ለዓለም ያስተዋወቀው ፍራንሲስ ፋልሲቶ የዓሊን የሸክላ ኅትመቶች በኢትዮጲስ የ13ኛ ሲዲ ኅትመት ላይ ‹‹ወርቃማዎቹ 70ዎቹ›› ተብለው ተጠቅሰዋል::
በ1935 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ ዓሊ አብደላ ካይፋ፣ ባደረባቸው ሕመም በሚኖሩበት አሜሪካ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይታው መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በ78 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም ኑሯቸውን ባደረጉበት አሜሪካ በሲያትል ከተማ ተፈፅሟል።
አብደላ ካይፋ (ዓሊ ታንጎ) ባለትዳር እና የ12 ልጆች አባት ነበሩ። እኛም እኚህን ጉምቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለውለታ ነፍስ ይመር እያልን፤ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ለነበራቸው የላቀ አበርክቶ አመሰገንን:: ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም