ተርኪዬ እና ሶሪያ የመከላከያ አጋርነት ስምምነት ሊያደርጉ ነው

የሶሪያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አህመድ አል ሻራ እና የተርኪዬ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን በአንካራ የጋራ የመከላከያ አጋርነት ስምምነት ሊያደርጉ መሆኑ ተገልጿል።ስምምነቱ ቱርክ በማዕከላዊ ሶሪያ የአየር ኃይል የጦር ሰፈር እንድታቋቁም እና በምላሹ የሶሪያ ወታደሮችን ማሰልጠንን የሚያካትት ነው ተብሏል።

ስለስምምነቱ የሚያውቁ የጸጥታ እና የደህንነት ባለስልጣናት በሰጡት መረጃ መሰረት፤ የሶሪያ የሽግግር መንግሥት መሰል ወታደራዊ አጋርነት ስምምነት ሲፈጽም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።በዚህም መሠረት ተርኪዬ በሶሪያ ሁለት አዳዲስ የአየር ጦር ሰፈር እንድትመሰርት፣ የሶሪያን የአየር ክልል ለወታደራዊ አገልግሎት እንድትጠቀም እና በሶሪያ አዲስ ጦር ውስጥ ወታደሮችን በማሰልጠን ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንድትጫወት እንደሚያስችላት ምንጮቹ ጠቁመዋል።

የኔቶ አባል የሆነችው ሀገር የበሽር አላሳድን መንግሥት የጣሉትን ተዋጊዎች በፖለቲካ እና በተለያዩ መንገዶች ስትደግፍ መቆየቷ ይታወቃል።አንካራ ራሷን በአዲሷ ሶሪያ ውስጥ የአሳድ ዋና ቀጣናዊ ደጋፊ ኢራን መገፋትን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት እና በቀጣናዊ ወሳኝ ተዋናይ ስፍራ ላይ ለመቀመጥ በፍጥነት እየተንቀሳቀሰች መሆኑ ተዘግቧል።

ይህ የተርኪዬ የተጽዕኖ ፈጣሪነት ፈጣን እንቅስቃሴ ከባህረ ሰላጤው አረብ ሀገራት ጋር ፉክክር እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚችል ዘገባው አክሏል።ከአሳድ ውድቀት በኋላ የሶሪያ አዲሱ አመራር ሠራዊቱን እና የተለያዩ አማፂ ቡድኖችን በትኖ ወደ አዲስ ወታደራዊ እዝ ውስጥ ለማዋሃድ እየሠራ ነው ተብሏል።

ከአንካራ ጋር ይፈጸማል በተባለው የመከላከያ ስምምነት መሠረት ሁለቱ ሀገራት በጋራ ወታደራዊ ስምሪቶች ዙሪያ ሊተባበሩ እንደሚችል ተመላክቷል። ደማስቆ እና አንካራ በቅርበት ይሠሩበታል የተባለው ሌላኛው ጉዳይ መልሶ ግንባታን የተመለከተ ይሆናል።

የተርኪዬ ፕሬዚዳንት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ፋህረቲን አልቱን ኤርዶሀን እና አልሻራ በሶሪያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሶሪያን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት፣ መረጋጋት እና ደህንነትን ለማስፈን በሚያስችሉ የጋራ እርምጃዎች ላይ ይወያያሉ ማለታቸውን አል ዐይን ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You