
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ሥጋቶችን በመለየት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማድረግ፤ መምራት፤ ምላሽ መስጠት በአዋጅ ከተሰጡት ተግባራት መካከል ናቸው:: የዝግጅት ክፍላችን ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመለየት አደጋዎች ሳይከሰቱ ቀድሞ የመዘጋጀትና የመከላከል ሥራውን እንዴት እያከናወነ ነው፤ የጤና የቅኝት ሥራዎችን በመሥራት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ የምላሽ አሰጣጡና ዝግጁነቱ እና መሰል ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ጋር ቆይታ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት በተገቢው መንገድ እየተወጣ ነው ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር መሳይ፡- እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፍሪካ አንጋፋ ከሚባሉት የጤና ኢንስቲትዩቶች አንዱ ነው:: የዓለም አቀፉ የጤና ኢንስቲትዩቶች ማህበር አባል እና የቦርድ ሥራ አስፈጻሚ ነን:: በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተስሚነት ያለው ትልቅ ሥራ የሚሠራ ተቋም ነው:: በተለያየ ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች ፌዴራል ላይ ሆነው በማቀድ ስትራቴጂካዊ ድጋፎችን ለክልሎች ይሰጣሉ::
ከክልሎች አቅም በላይ በሚሆንበት ጊዜ በተለይም ደግሞ ያልተለመዱ ወይም አዲስ የሚከሰቱና እንደገና የሚከሰቱ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል የመተላለፍ ዕድላቸው ከፍተኛ የሆኑ ለኅብረተሰብ ጤና ሥጋት የሆኑ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲኖሩ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ቡድን ተደራጅቶ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ሥልጠና ተሰጥቶ እየሠሩ ይገኛሉ:: እነዚህ ባለሙያዎች በየጊዜው የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እየወሰዱ ዝግጁ ሆነው የሚጠብቁ ናቸው::
አልፎ አልፎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው የሃይማኖት በዓላት ሲኖሩ ቀድሞ በማቀድ ለድንገተኛ የጤና ችግር ፈቺ የሕክምና ቡድን በቦታው ይሰማራል:: ስለሆነም ትልልቅ የአደባባይ ሁነቶች ላይ የመከላከል ዝግጁነት፤ የቅኝት ሥራ እና አስፈላጊ ቅድመ ዝግጀት ይደረጋል::
የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ከአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በጋራ በማቀድ እና በመሥራት ምላሽ የሚሰጥባቸው ሥራዎች ይሠራሉ:: ለአብነት በቅርቡ በጎፋ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥፍራው በማቅናት የጤና አደጋ እንዳይከሰት የሕክምና ድጋፍ ተሰጥቷል:: መሠረታዊ የሆኑ የጤና አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ ተሠርቷል::
በየትኛውም የዓለም ክፍል በሽታዎች ሲከሰቱ በሽታዎች የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ወይም ሥጋት ይሆናሉ ተብለው የተለዩ፤ ያልተለዩ በባህሪያቸው ተላላፊ የሆኑ በሀገሪቱ ብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና እቅድ ላይ በተቀመጠው መሠረት በቋሚነት የልየታ ሥራዎች ይከናወናሉ:: ስለሆነም በሀገሪቱ ድንበር አካባቢዎች በተለይ በየብስ መውጫና መግቢያ ኬላዎች ያሉ ሲሆን የተላላፊ በሽታዎች የቁጥጥር ሥራዎችና የክትባት አገልግሎቶች ይሰጣሉ::
ወደ ሀገር በሚገቡና በሚወጡ አውሮፕላኖች ላይ የቅኝትና የርጭት ሥራዎች ይከናወናሉ:: በተጨማሪም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ አስከሬኖች ላይ የሰርቲፊኬሽንና የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ይካሄዳል:: ይህም በድንበር ጤና ቡድን የሚሠራ ነው:: እንዲሁም በተላላፊ በሽታ ልየታ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የልየታ ሥራ ይከናወናል::
በቅርቡ በሩዋንዳ ላይ ተከስቶ በነበረው የቫይረስ ወረርሽኝ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ላይ በተከሰተው የ‹‹ኢምፖት›› በሽታን በተመለከተ የዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ሥጋቱን በመለየት በሀገራቱ በሚመጡ መንገደኞች ላይ በቋሚነት የመለየት ሥራ ይሠራል:: ባለፉት ወራት በአየር የሚጓዙ ከ500 ሺ በላይ መንደኞች ተለይተዋል:: እንደመተማ፤ ኩምሩክ፤ ጋላፊ፤ ቶጎ ጫሌ፤ ሞያሌ፤ ኬላዎች ላይ በቋሚነት የልየታ ሥራዎችን ተሠርተዋል:: እነዚህ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን መከላከል ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው::
በቅኝት ሥራ ወደ 36 የሚሆኑ የተለያዩ በባህሪያቸው ተላላፊ የሆኑ፤ ቢከሰቱ ከፍተኛ የሆነ የኅብረተሰብ የጤና ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብለው በተለዩ በሽታዎች ላይ በቋሚነት ቅኝት ይደረጋል:: ማንኛውም የጤና አደጋ ቀበሌ ላይ ተከስቷል የሚባል ሃሳብ ሲሰማ በ30 ደቂቃ ውስጥ ወረዳው ወደ ዞን፤ ዞኑ ወደ ክልል ሪፖርት በማድረግ የማረጋገጥ ሥራ የሚሠራ ሲሆን በብሔራዊ ደረጃ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መረጃው ደርሶ ይለያል::
በየሳምንቱ የጤና መረጃዎች እየተሰበሰቡ ይተነተናሉ:: የበሽታ የሥርጭት ሁኔታ በቋሚነት ክትትል ስለሚደርግ ርምጃ ይወሰዳል:: ለምሳሌ የምላሽ ሥራ ሳይዘገይ እንዲጀመር፤ ኅብረተሰቡን የማንቃት፤ የማስተባበር እና የጤና ሥርዓቱ ቶሎ ምላሽ እንዲሰጥ የማድረግ ሥራ ይሠራል:: የማንቃት ሥራዎችን እንሠራለን:: ሌሎችም በየወሩ ሪፖርት የሚደረግባቸው በሽታዎች ያሉ ሲሆን እንደ ኤች. አይ. ቪ ኤድስ ያሉ በሽታዎች ከመቶ በላይ የጤና ተቋማት ላይ በቋሚነት የሥርጭት ሁኔታው ላይ ክትትል ይደረጋል::
መረጃዎችን ሰብስቦ በመተንተን ለጤና ሚኒስቴርና ለገጠር ጤና ተቋማት በመስጠት የጤና ምላሽ ሥርዓት እንዲጠናከር በአውትና በመረጃ ላይ የተደገፈ የትንተናና የምላሽ ሥራዎች ሪፖርት ይቀርባል:: በሁሉም ተዋህሲያን ላይ የቅኝት ሥራዎችን ማለትም የተዋህሲያን መድኃኒት መላመድ ላይ ከ30 በላይ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እና ክስተቶች ላይ የሚሠሩ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ይሠራሉ::
በሽታዎች ሲከሰቱ መንስኤዎቻቸው ምንድን ነው፤ የበሽታው ጫና ምን ይመስላል፤ የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል የበለጠ ይጎዳል፤ በሀገሪቱ በየትኞቹ አካባቢዎች ይከሰታሉ፤ የሚለው የጉዳት መጠናቸው ከተለየ በኋላ ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል አሠራር በመንደፍ የመከላከልና የቁጥጥር ሥራ ይከናወናል::
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ ከተመሠረተ 100 ዓመት ሊሞላው ነው እንደ ዕድሜው በልኩ ሠርቷል ብለው ያምናሉ? ከሆነስ ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?
ዶ/ር መሳይ፡- እንደ ዕድሜው ስንል ለምሳሌ ሥራ ሲጀምር በጣም ትንሽ በሆኑ ላብራቶሪዎች ሲሰጥ ከነበረበት ክልሎችን በመደገፍ በመላው ሀገሪቱ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ቅርንጫፎች ተቋቁመው የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች የቁጥጥር ሥራ እንዲሠሩ ተደርጓል:: በተለያዩ የዓለም ክፍል እየተነሱ ያሉ የተላላፊ በሽታዎች አሉ:: የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ምላሽ ላይ ሰው ሠራሽና ድንገተኛ አደጋዎች የተለዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ያልተጠበቁ ድንገት የሚከሰቱ ናቸው:: ሥርዓት በመገንባቱ ማንኛውም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ተገንብቷል:: ይህ ብቻ ሳይሆን በአሠራር እና በአደረጃጀት ስታንዳረድ ተዘጋጅቶ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የተናበበ ሥርዓት ተፈጥሯል:: በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የተለየ የጤና አደጋ ወረርሽኝ ጭምጭምታ ከተሰማ ወዲያውኑ ምላሽ የሚሰጥበት አቅም ተገንብቷል::
የምላሽ አሰጣጥ ሥርዓቱ ከማዕከል ብቻ ተወርውሮ የሚሠራ ሳይሆን በየክልሉ የተገነቡ አቅሞችን የመደገፍ ሥራ ይሠራል:: ለዚህም አንዱ ማሳያው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው ኮቪደ- 19 በተከሰተበት ወቅት ከዓለም ሀገራት በአንጻራዊነት በተሻለ ሁኔታ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ሳይቋረጥ በሽታውን መከላከልና መቆጣጠር ተችሏል:: ይህ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች ሳይቋረጡ እየሰጡ እንዲቀጥሉ የተደረገበት ሂደት ነበር:: በሌላ በኩል የሞት ምጣኔ እንዲቀንስ ሰፊ ሥራ የተሠራበት ሂደት አለ::
የኢንስቲትዩቱ የምርምር አቅም ዘመናዊ ላብራቶሪዎችን የያዘ ሲሆን በፊት ከነበረበት በከፍተኛ ደረጃ የተሻሻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: አቅሙ ከዚህ በፊት ከነበረበት በተሻለ ደረጃ የተሻሻለበት እና የጤና ችግሮች ሲከሰቱ ለሚሰጠው ምላሽ ትልቅ አቅም ሆኗል:: በየሳምንቱ እና በየወሩ ሪፖርት የሚደረግባቸውን ሪፖርት በማድረግ እና በማደራጀት ተተንትኖ በልኩ ምላሽ ይሰጣል:: ስለዚህ አልፎ አልፎ ወጣ ያሉ በሽታዎች ስለሚሰሙ እንጂ በየቀኑ 24 ሰዓት ሰባት ቀን ያለ ማቋረጥ መረጃ ይሰበሰባል፤ ምላሽ ይሰጣል::
በአገልግሎት ተደራሽነት በኩል ብዙ ወረዳዎች ላይ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ የሚሰጥበት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ በየቀኑ በርካታ የሰው ኃይል በጤና ሲስተሙ እየሠራ ይገኛል:: ኢትዮጵያ ጠንካራ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝት ካላቸው ሀገራት ተርታ የተሰለፈች ሀገር ናት:: ሁሉን አቀፍ የሆነ የኅብረተሰብ ጤና አቀፍ ሥራዎች እንዲሠሩ ማድረግ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል::
አዲስ ዘመን፡- አቅም ስለመፈጠሩ ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?
ዶ/ር መሳይ፡- ማሳያዎቹ የኮሌራ ወረርሽኝ፤ ከድርቅ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በሽታዎችን፤ የወባ እና የኩፍኝ ወረርሽኝ ፤ ደንጊ የሚባል በሽታ ተከስቶ የነበረ ሲሆን አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ማኅበራዊ ቀውስ ሳይከሰት፤ ትምህርት ቤቶች ሳይዘጉ፤ የልማት ሥራዎች ሳይቋረጡ ኅብረተሰቡም ሳይሸበር ወረርሽኞቹን በሚገባ መቆጣጠር ተችሏል:: በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሽታው ተለይቶ ተረጋግጦ ሕክምና አግኝተው ድነው እንዲወጡ ተደርጓል:: ይህን አንድ ሁለት ብሎ እንደ ማሳያ ብቻ ከሚሆን የጤና ሥጋት ናቸው ተብለው በተለዩት ላይ ቀድሞ የዝግጁነት ሥራ ስለሚሠራ ሲከሰት ወዲያውኑ ምላሽ ይሰጣል:: ምላሽ በሚሰጥበት ጊዜ ሊደርስ የሚችለውን ሞት ወይም ቀውስ ኅብረተሰቡ ቶሎ ሕክምና አግኝቶ እንዲድን ለማድረግ ነው:: በተጨማሪም የማኅበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል የሥርጭት አድማሱን ከመግታት አንጻር በርካታ የመቆጣጠር ሥራዎች ተሠርተዋል::
በሀገሪቱ 80 ዓመት ያስቆጠሩ የመጀመሪያ ላብራቶሪዎች አሉ:: ከዝቅተኛ ተነስቶ አሁን ላይ ‹‹ሰቴት ኦፍ ዘአርት›› የሚባሉ በቴክኖሎጂ የዳበሩ ላብራቶሪዎች አሉ:: አቅማቸው በሽታዎች ሲከሰቱ ቶሎ ምርመራ ተካሂዶ ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት እና በሽታዎችን በቶሎ መለየት የሚያስችል አቅም ተገንብቷል:: የተህዋሲያን የዘረመል ትንተና ጭምር እየተሠራ ይለያል:: ላብራቶሪዎቹ ለምርምርም ለኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጭምር የሚረዱ ሥራዎች ናቸው::
ወባ በምታስተላልፈው የትንኝ ባሕሪ ላይ የትንኝ ዝርያዎች ላይ የሚሠሩ ጥናቶች አሉ:: የማስተላለፍ አቅማቸውን የመለየት አዳዲስ የሚፈጠሩ ከሆነም የትኞቹ ትንኞች የበለጠ በሽታውን ያስተላልፋሉ የሚለው ይገኝበታል:: ባሕሪያቸውና የአመጋገብ ሁኔታቸውን መለየት ያስችላል:: ይህም ሰው ሠራሽ ሰህተቶችን ያስቀራል:: ይህ ሲባል አዳዲስ ለሚከሰቱ በሽታዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል:: ለምሳሌ የብሔራዊ ኢንፍሎይዛ ላብራቶሪ አቅሙ በአፍሪካ ካሉት 16ቱ ውስጥ አንደኛ ነው:: ማንኛውም ጉንፋን ነክና ኢንፍሉዌንዛ በሽታዎች በቋሚነት ቅኝት ይሠራባቸዋል::
ኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ የመረጃ ማመንጨት አቅም የጤና መረጃ አስተዳደርና ትንተና ማዕከል ያለ ሲሆን በሀገሪቱ የተሠሩ በርካታ የጤና መረጃዎች ይሰበሰባሉ:: እነዚህ መረጃዎች በሳይንሳዊ ሥነ ዘዴ ይተነተናሉ:: መረጃዎቹ ለፖሊሲ ግብዓትነትና ለሥራ የእቅድ መነሻ ግብዓት ይውላሉ:: ስለዚህ በሳይንስ ላይ መሠረት ያደረገ ዓለም አቀፍ የመረጃ ሳይንስ ሥርዓቶችን በመከተል መረጃዎች ይመነጫሉ:: እነዚህን ጠቅለል አድርገን በምናይበት ጊዜ በመቶ ዓመት ውስጥ የተለያየ ስያሜ አደረጃጀትና ተግባራት ሲሰጠው ከነበረበት መንገድ አሁን ላይ በሙሉ አቅሙ ዋና ዋና የኅብረተሰብ ጤና ተግባራት የሚባሉትን በአዋጅ ተለይተው እየሠራ ነው::
ማንኛውም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቢከሰት ቀድሞ መዘጋጀት፤ መከላከል ከተገኘ ደግሞ መቆጣጠርና ምላሽ መስጠት ላይ በተለይም አቅም የሚሆነው የቅኝት ሥርዓቱ መሻሻል ነው::
አዲስ ዘመን፡- አንዱ የተቋሙ መለኪያ የጤና ሥጋቶችን ብሎም ከተከሰቱ ታካሚዎችን ማዳንና የሞት ምጣኔ መቀነስ ነው:: እናም በተሠራው ሥራ የሞት ምጣኔን ከነበረበት በዚህ መልኩ ቀንሰናል ብሎ ለመግለጽ የሚያስችሉ ማሳያዎች አሉ?
ዶ/ር መሳይ፡- የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ከዓለም ጋር ማነጻጸር ይቻላል:: የእኛ ሀገር ዝቅተኛ ነው:: የኮሌራም ሲታይ ከአንድ ፐርሰንት በታች ነው:: የኩፍኝም በመቶ ሺዎች፤ በ10 እና 20 ሺዎች ታመው የሞት ምጣኔው ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድ በታች ነው:: ስለዚህ የሞት ምጣኔን ከመቀነስ አንጻር በወባ፤ ኩፍኝ፤ ኮሌራ እና መሰል በሽታዎችን ከመከላከልና የሞት ምጣኔን ዝቅ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል::
ተላላፊ በሽታዎችን ቀድሞ መለየት ምላሽ መስጠትና የ‹‹ሰርቪላንስ›› አቅሞች ላይ መሻሻሎች አሉ:: ብሔራዊ የጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሞ እንደየክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ ድንገተኛ የጤና ማስተባበሪያ ማዕከልን በመምራት ምላሽ እየተሰጠ እና እየተገመገመ እየተሠራ ነው:: በክልሎች ላይ ኩፍኝ፤ ኮሌራ አንድ ላይ በተከሰተበት ወቅት በማቻቻል ተሠርቷል:: ለምሳሌ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ለወረርሽኙ ምላሽ እየተሰጠ በተጓዳኝ የእናቶችና ሕፃናት የጤና አገልግሎቶች ሳይቆራረጡ እየተሰጡ ባለው ሥርዓት ሀብትን አቅምን በመጠቀም እየተሠራ ነው:: በዚህና መሰል ጉዳዮች የሚገለጹ በጣም በርካታ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- የወባ በሽታ በተለይ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከሶስት ዓመት በላይ በወረርሽኝ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል:: በዚህም ኅብረተሰቡ ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ ስላለው እርስዎ በሚናገሩት ልክ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም ካደራጀ ለምን በወረርሽኝ ውስጥ ሊቆይ ቻለ? መከላከልስ ስለምን አልተቻለም?
ዶ/ር መሳይ፡- ደቡብ ምዕራብ ላይ ለምሳሌ ኩፍኝ በሽታ ነበር:: በክልል ያለውን ወረርሽኝ መቆጣጠር ተችሏል:: 75 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ መልክዓ- ምድር ለወባ ምቹ ነው:: ወደ 69 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ለወባ ተጋላጭ ነው:: ያ ማለት ወባ ሙሉ በሙሉ የሌለ በሽታ አይደለም:: አሁን ላይ ያለው የጤና ፖሊሲ መከላከልን መሠረት ያደረገ ነው:: ጤና ኬላ ላይ የወባ መድኃኒት አቅርቦት ብንመለከት የጤና ኤክስቴንሽን ተግባራዊ በሆነባቸው ወባማ በሆኑ አካባቢዎች ወረርሽኙ ተነስቷል::
የፌዴራል መንግሥት መድኃኒቶችን በነፃ እየሰጠ ነው:: ባልተማከለ የጤና ሥርዓት አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ላይ የመከላከሉን ሥራ በቂ ስላልሆነ የወባ የመከላከል ሥራ በባህሪው የኅብረተሰብ ተሳትፎን ይጠይቃል:: የትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማስወገድን፤ ያቆሩ ውሃዎችን ማፋሰስ ያስፈልጋል:: በተጨማሪም የአልጋ አጎበሮችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል:: አጠቃቀሙን በየጊዜው የጤና አጠባበቅ ትምህርትንም በመስጠት በጤና ኬላ ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው:: በሌላ በኩል በሽታውን ከመከላከል አንጻር የመድኃኒት መላመድ ይኑር አይኑር የሚለውን የመከላከልና የቁጥጥር ሥራዎች ውጤታማ ናቸው? አይደሉም የሚለውን እየሠራን ስለሆነ በዚህ ረገድ ምንም ችግር አልነበረም::
የወባ ወረርሽኝ ከፍ ብሎ በታየባቸው ቦታዎች ላይ ሥራ ያቆሙ ጤና ኬላዎችን በመለየት ምላሽ እየተሰጠ ነው:: አንድም ሞት ቢኖር ስኬት እስካልሆነ ድረስ ስኬት ነው ተብሎ አይወራም:: ነገር ግን የሞት ምጣኔው ዝቅ ብሏል:: ስለሆነም የወባ ወረርሽኝ ቢኖር የሞት ምጣኔው ዝቅተኛ ነው:: ነገር ግን ወባ ተላምዶ የቆየበት ምክንያት ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑባቸው ቦታዎች በሀገሪቱ ባሉ ወረዳዎች ላይ ትኩረት ያደረገ በፌዴራል ደረጃ እየተመራ ክልሎችንም በማቀናጀት በመሠራቱ በየሳምንቱ እየቀነሰ ነው::
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ ትርጉም ባለው መንገድ ወባ ቀንሷል:: ክልሉ ወባማ አካባቢ ነው:: እስከ ሰሜን ምዕራብ ማለትም ጋምቤላ፤ ቤኒሻንጉል፤ እስከ ትግራይ እና አማራ ክልል ምዕራቡ ክፍል አካባቢ አሁንም ከፍተኛ የወባ ጫና ያለባቸው አካባቢዎች ናቸው:: አንዳንድ ቦታዎች ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ግጭቶች ያሉባቸው አካባቢዎች አሉ:: ነገር ግን ወባን ለመከላከል በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ተመድቦ የመከላከሉ ሥራ እየተሠራ ነው:: ለረጅም ጊዜ ወባ ተቆጣጥረናል:: ነገር ግን መዘናጋት ነበር:: ወባ ትንኟ፤ ተዋህስያኑ አሉ:: የመከላከሉ ሥራ በሚገባ ሲቀንስ እና ወደ ሌሎች በሽታዎች መከላከል ላይ ትኩረት ሲደረግ መነሳቱ አይቀርም::
አዲስ ዘመን፡- በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል የሰው ኃይልና አደረጃጀት ተገንብቷል?
ዶ/ር መሳይ፡- በሽታዎችን በተቀናጀ መንገድ መከላከል እንዲቻል በየደረጃው ላሉ ሠራተኞች በየጊዜው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሠጥቷል:: ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ጋር በቅንጅት ስለምንሠራ በብሔራዊ ደረጃ የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በከፍተኛ አመራሩ እየተመራ በውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ መድኃኒቶች ገብተው እየተሠራጩ ናቸው:: መድኃኒቱ ከተሠራጨ በኋላ ወረዳና ጤና ኬላዎች ከደረሰ በኋላ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ የክልሎች ነው:: የመመርመሪያ መሳሪያዎች ግን በነፃ ይቀርባሉ:: ወባ አዲስ በሽታ ሳይሆን ነባር በሽታ ነው:: እየጨመረ ያለው የቁጥጥር ሥራው እየተሠራ ባለበት ነው:: ስለዚህ አሁንም በብሔራዊ ደረጃ እየተመራ የወባ ሥርጭት በጨመረባቸው አካባቢዎች እየተሠራ ነው:: ሥራው ግን በቋሚነት የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው::
በመደበኛ የመከላከል ሥራ ሲሠራ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀር በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል:: አሁን ላይ የወባ ሥርጭት ያለባቸው 222 ወረዳዎች ተለይተው የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው:: 76 በመቶ ጫና ሲያስከትሉ ከነበረው ተጽዕኖ ከ50 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል:: ጠንካራ የአመራር ቁርጠኝነት ታይቶባቸው ሕዝብ በተሳተፈባቸው ካቀድነው ቀድመናል:: ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ወባ በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምርበት ወቅት ነው:: አሁን ላይ ከመስከረም ጀምሮ እየቀነሰ ነው:: በፊት ወባ የሚከሰተው በሁለት ወቅቶች ላይ ነበር:: አሁን ላይ ግን ዓመቱን በሙሉ አለ:: የወባ የመከላከል ሥራ ከመሠረተ ልማቶች ጋር አስተሳስሮ መሥራት ያስፈልጋል:: ስለሆነም ዓመቱን በሙሉ የመቆጣጠር ሥራ መሥራት አለብን:: በተለይ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ነገሮችን በመለየት በየጊዜው ማጽዳት ይገባል::
የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራር በየክልሉ ተመድበው በሚኒስትር ዴኤታዎች እየተመራ የመከላከሉ ሥራ እየተሠራ ነው:: ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ከፍተኛ የወባ ሥርጭት የሚከሰትበት ወቅት ነው:: በሚቀጥሉት ወራትም በተቀናጀ መንገድ መሥራት ከተቻለ ወባ እየቀነሰ የሚሄድበት ሁኔታ ይፈጠራል::
ይህ ችግር የጤና ሥርዓቱ ላይ ብቻ ያለ ሳይሆን የአየር ንብረት ሁኔታው ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል:: ከዚህ ቀደም ወባ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ አድርሰን ነበር:: ነገር ግን በኅብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት በመፈጠሩ እና ለወባ መራቢያ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ እንደገና ሊያንሠራራ ችሏል::
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ ወባን ለመከላከል እያደረገ ባለው ጥረት አሁን ላይ ከወረርሽኝነት ወጥቷል?
ዶ/ር መሳይ፡- አልወጣም:: ለምሳሌ ወላይታ ሶዶ አካባቢ ሄድን ስናረጋግጥ መጀመሪያ ከነበረበት 80 በመቶ ቀንሷል:: ይህም የድንገተኛ ጤና አደጋዎች ምላሽ ነው:: ይህ የሚጨምርበት አንዱ ምክንያት ኅብረተሰቡ የተሰጠው አጎበር በአግባቡ ባለመጠቀሙ እንደ አንድ ምክንያት ይነሳል:: የአቆሩ ውሃዎችን አለማፋሰስ፤ መዘናጋት ለመባባሱ እንደ ምክንያትነት ይወሰዳል::
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየተስፋፉ ነው ይባላል:: ከዚህ አንጻር በሽታዎች ለመከላከል ኢንስቲትዩቱ ምን ሠርቷል?
ዶ/ር መሳይ፡- ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መስፋፋት ከባህሪ ጋር የሚያያዙ ናቸው:: ለምሳሌ የስኳር፤ ከልብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የግፊት እና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭቱ አለ:: የዓለም የበሽታ ሥርጭት ሲታይ ብዙ ጊዜ የሚበዛው በበለፀጉ ሀገራት ነው:: ይህ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የሚያይዝ ነው:: ለምሳሌ ቁጥጥር ያልተደረገበት ውፍረት፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፤ የአመጋገብ ሥርዓትን አለማስተካከል ጋር የሚያያዙ ናቸው:: ለዚህ ችግር የጤና አጠባበቅ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል:: በጤና ሚኒስቴር በኩል ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በፕሮግራም ዘርፍ የሚሠሩ የምላሽ ሥራዎች አሉ::
የደም ግፊት የልየታ ሥራ፤ የጡት ካንሰር፤ የማህጸን ካንሰርና መሰል የሕመም ዓይነቶች የመከላከል ሥራ ይሠራል:: ሀገራዊ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት ሁኔታ ለማወቅ ወካይ የሆነ ጥናት እየተሠራ ነው:: ተላላፊ ያልሆኑ የሚባሉትን በሽታዎች በሁለት መልኩ የሚታይ ሲሆን የሥርዓተ ምግብ መዛባት እና እጥረት ነው:: እነዚህን በሽታዎች መርምሮ የመለየት አቅም ጨምሯል:: ስለዚህ ይህን መከላከል የሚያስችል ፖሊሲ ስላለ ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሠራ ነው:: ከልብና የደም ስር የተያያዙ በሽታዎች ሲታይ የመጨመር ሁኔታ ይስተዋላል:: ጠቅለል ባለ ሁኔታ ሀገራዊ ሁኔታው ያለው ሥርጭት ለማወቅ ወካይ የሆነ የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ ነው:: ጥናቱም በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል::
አዲስ ዘመን፡- ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ማዳን እንደሚቻል አልፎ አልፎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ሲነገር ይደመጣልና ይህ ምን ያህል እውነት ነው? የትኞቹስ በሽታዎችስ የመዳን ዕድል አላቸው?
ዶ/ር መሳይ፡- የበሽታዎች ጫና በሀገር አቀፍ ደረጃና ዓለም ደረጃ ይታወቃል:: በየጊዜው የጥናት ውጤቶች ይወጣሉ:: የበሽታዎች መንስኤ ይታወቃል:: ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የስብ የደም ስር ክፍል ላይ በመጋገር የደም ስርን በማጥበብ ለደም ግፊት መጨመር ምክንያት በመሆን ሌሎች ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ሊያመጡ ይችላሉ:: የእነዚህ በሽታዎች ትልቁ መፍትሔ መከላከል ሲሆን ውጤታማ ነው::
በሽታው ከተከሰተ በኋላ ክብደትን መቀነስና ሌሎች የሕክምና የምክር አገልግሎቶችን መከታተል የሚችሉ ሰዎች ሊደኑ የሚችሉበት እድል አለ:: ይህ ደግሞ የሚወሰነው በሽታው እስከሚታወቅ ድረስ በራሱ ለረጅም ጊዜ ቆይቶ ከሆነ የጎንዮሽ ተጨማሪ ጉዳቶች ስለሚኖሩ ሰዎች ያለ ምንም አካል ጉዳት ለረጅም ጊዜ ሊኖሩ ይችላሉ:: ይሁን እንጂ በሽታው ለረጅም ጊዜ ቆይቶ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከተለ ከሆነ የሆነ ወቅት ድንገት ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል በቋሚነት ክትትል ያስፈልጋል::
ለበሽታዎች አጋላጭ የሆኑ አካባቢያዊ የሆኑ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ:: ብዙ ጊዜ በዘር የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው:: በአጠቃላይ ግን ውፍረት መቀነስ፤ እንቅስቃሴ ማድረግ፤ አመጋገብ ላይ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ያስፈልጋል:: ስለዚህ መድኃኒት ላያስፈልግ ይችላል:: ነገር ግን ሁልጊዜ ክትትል ያስፈልጋል:: አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ለራሳቸው ቢዝነስ ለማግኘት የሚለቁትን መረጃ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል:: የሕክምና ባለሙያዎችን መረጃ መጠየቅና መረዳት ተገቢ ነው:: ከባለሙያና ከታማኝ ምንጮች መረጃን መውሰድና መጠቀም ተገቢ ነው:: በባህሪያቸው መከላከል የምንችላቸው ናቸው::
የማዳን ጉዳይ እንደየጉዳት መጠኑ የሚወሰን ነው:: ተላላፊ በሽታ ሲሆን ተዋህሲያኑን ገድለን ስንጨርስ ይሆናል:: ነገር ግን አንዳንድ በሽታዎች ብዙዎቹ መንስኤዎቹን ካስወገድናቸው ወደ ሙሉ ጤንነት ይመለሳሉ:: ነገር ግን እንደገና ሊከሰቱበት የሚችሉበት እድል ስለሚኖር በፕሮግራም ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- የሕክምናው ዘርፍ በየጊዜው ጥናትና ምርምርን የሚፈልግ ነውና በዓመት ምን ያህል ጥናቶች በተቋሙ ይጠናሉ? ጥናቶችስ ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ ኢንስቲትዩቱ ምን ሠርቷል?
ዶ/ር መሳይ፡- በአጠቃላይ በዓመት በኢንስቲትዩቱ ተጠናቀው የሚቀርቡ ጥናቶች ከ70 እስከ 80 የጥናትና የምርምር ሥራዎች ናቸው:: ሌሎችም ትልልቅ ጥናቶች አሉ:: ባለፈው ዓመት ኤች. አይ. ቪ ሥርጭት ላይ ጥናቶች ተጠንተዋል:: የባሕሪ፤ ሥርጭት ላይ ወካይ የሆኑ ጥናቶች በተለይ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አምስት የሚሆኑ ጥናቶች ተጠንተዋል:: ወባ ላይም በተመሳሳይ የወባ መድኃኒት መላመድ ላይ እና የመከላከልና የቁጥጥር ሥራዎች፤ በትንኝ ባሕሪ እና የመተላለፍ አቅማቸው ላይ የተሠሩ ወካይ የሆኑ ሀገራዊ ጥናቶች አሉ::
በመድኃኒት መላመድ ላይ ቋሚ የጥናትና ምርምር አካል የሆኑ የቅኝት ሥራዎች ይሠራሉ:: ወባ ከመደበኛ የቅኝት ሥርዓት በተጨማሪ ጥናቶች ይሠራሉ:: ወባ ላይ መድኃኒቱ እያሻለን አይደለም የሚል ቅሬታ ይነሳ ነበርና መድኃኒቱ ትክክለኛ መሆኑን በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት የተመዘገቡ ናቸው:: በመድኃኒቶች ላይ ከሥርጭት እስከ መድኃኒቱን መጠቀም ላይ ሊደረግ የሚገባው የጥንቃቄ ሂደት አለ:: ጥንቃቄ ያልተከተሉ ከሆነ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ:: የኅብረተሰብ የጤና ችግር ናቸው ተብለው በተለዩት ጉዳዮች ላይ ጥናት ይከናወናል:: የጤና ችግሮችን ለመለየት የሚደረገውን ሥራ በትክክል ለመለየት የሚያስችል ነው:: ጥናቶች ተግባራዊ ምርምሮች ስለሆኑ ኢንስቲትዩቱ እና ጤና ሚኒስቴር የሚጠቀምባቸው ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር የጤና ሥጋት ናቸው ተብለው የተለዩ በሽታዎች አሉ? በእናቶችና ሕፃናት ሞት ቅነሳ ላይ በተጨባጭ የተሠራው ሥራ ምንድን ነው?
ዶ/ር መሳይ፡- እንደ ሀገር የጤና ሥጋት የሚባሉት ተላላፊ በሽታዎች ናቸው:: እንደየሁኔታው ይለዋወጣል:: በየትኛውም ዓለም ክፍል የጤና ሥጋት የሆነ በሽታ ሁልጊዜም እንደ አደጋ ይቆጠራል:: የጤና አደጋዎች ሲከሰቱ ሁልጊዜ የአደጋዎች የቁጥጥር ሥርዓት በተጠንቀቅ ሆኖ ክትትል ይደረጋል:: የመከላከልና ዝግጁነት ሥራ ይሠራል:: አንድ ተላላፊ በሽታ ከአንደኛው የዓለም ጫፍ ወደ ሌላኛው ዓለም ጫፍ በ36 ሰዓታት ውስጥ የመድረስ ዕድል አላቸው:: ምክንያቱም በከፍተኛ ደረጃ የአየር ትራንስፖርት አለ:: ስለዚህ የጤና ደህንነት ሥራችን ሁልጊዜም የመጠበቅ ሥራ እንሠራለን:: የሚሠራው ከዓለም የጤና ድርጅት በሚሰጠው መመሪያ እና ከዓለም አቀፍ የጤና ደንብ ፈራሚ ሀገራት ጋር ከሚወጡ መረጃዎች ጋር እያቀናጀን የሚሠራ ነው::
ዓለም አቀፍ የጤና ሥጋቶች ሲኖሩ በሁሉም መንገድ ዝግጁ ሆኖ የሚጠባበቅና ቢከሰት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ ይሠራል:: የእናቶችና ሕፃናት ሞት ላይ የቅኝት ሥርዓት አለ:: የእናቶች ሞት ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ከወሊድ ጋር በተያያዘ ነው:: ስለዚህ በወሊድ ጊዜ ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች ማንኛውም እናት በጤና ተቋም እንዲወልዱ ማድረግ ነው::
የድህረ ወሊድ ክትትል ማድረግ፤ የሥርዓተ ምግብ እጥረት ካለ የልየታ ሥራ ይሠራሉ:: ስለዚህ የእናቶችና ሕፃናት ጤና በፕሮግራም ዘርፍ የሰባት 24 ሥራ በጤና ሚኒስቴር ሲሆን የእኛ ድርሻ የቅኝት ሥራ መሥራት ነው:: የእናቶች ሞት ምጣኔ ትርጉም ባለው መልኩ ቀንሷል:: ከዓለም ሀገራት ጋር ሲነጻጸር መድረስ ካለበት አንጻር ሲታይ መከላከል በሚቻል የጤና ችግር ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሁኔታ እናት መሞት የለባትም በሚል እየተሠራበት ነው:: ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ቶሎ ሕክምና ፈልጎ ወደ ጤና ተቋም አለመምጣት፤ ትራንስፖርት ማጣት፤ ጤና ተቋም ከደረሱ በኋላ ፈጣን የሆነ ርምጃ ካልተወሰደ ሊጎዱ ይችላሉ:: በተለይ በወሊድ ምክንያት ደም እየፈሰሳት ያለች እናት በአጭር ጊዜ ተገቢው እንክብካቤና የጤና አገልግሎት ካላገኙ ሊጎዱ ስለሚችሉ እነዚህን መሠረት ያደረገ ሥራ ይሠራል::
አዲስ ዘመን፡-ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን::
ዶ/ር መሳይ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ::
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም