
-
የእሁድ ገበያዎችን ቁጥር 137 ማድረስ ተችሏል
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ 11 ክፍለ ከተሞች በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ግብይት መፈጸም መቻሉን የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ገለጸ፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የእሁድ ገበያዎችን ቁጥር ወደ 137 ማድረስ ተችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሀብተየስ ዲሮ እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት በእሁድ ገበያ፣ በባዛሮች እና በመደበኛ ሱቆች ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ግብይት ተፈጽሟል፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽሩ ገለጻ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብይት ድርሻን በማሳደግ ፍትሐዊ የግብይት ተጠቃሚነት እንዲኖር ቁልፍ ተግባሩ አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት በተለያዩ ጊዜያት በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠሩ ቀውሶች ምክንያት በከተማዋ የሚስተዋለውን የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶች የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
ማህበራቱ ከገጠር አምራች ኅብረት ሥራ ማህበራት እና ከኢንዱስትሪ አምራቾች ጋር ቀጥተኛ የግብይት ትስስር በመፍጠር ማህበረሰቡ በፍትሐዊ ግብይት ምርትና ሸቀጥ እንዲያገኝ በማድረግ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
የእሁድ ገበያ ማዕከላትና የበዓላት ባዛሮች እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን የሚናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ማህበራቱ ለሕዝብ አማራጭ የግብይት መዳረሻ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አያይዘውም፤ በአሁኑ ጊዜ የኅብረት ሥራ ማህበራት የሚሳተፉባቸው የእሁድ ገበያ መዳረሻዎችን ወደ 137 ማስፋት በመቻሉ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችና እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶችን ጨምሮ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማህበረሰቡ በቅርበት ተደራሽ ለማድረግ እንደተቻለም ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማህበራት የሥራ ፈጠራን በማበረታታት በከተማ አስተዳደሩ የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ ያለውን ሥራ እና የማህበረሰብ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል እንደ አንድ ስትራቴጂ እያገለገሉ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም ኮሚሽኑ ያስመዘገባቸውን በጎ ጅምሮች አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ሌሎችም የኅብረት ሥራ ማህበራት ጅምሮቹን ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ዘላቂነት እንዲኖረው የተጠናከረ ሥራ እንደሚሠራም አቶ ሀብተየስ ተናግረዋል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራትን እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅና ለማጠናከር ያለመው 11ኛው ሀገር አቀፍ እና 4ኛው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም፣ ‹‹የኅብረት ሥራ ማህበራት ሚና ለኢትዮጵያ ብልፅግና›› በሚል መሪ ቃል ከጥር 28 እስከ የካቲት ሦስት ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም