
አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ ከሁሉም ክፍለ ከተማ ለተመለመሉ ለአንድ ሺህ 577 አካል ጉዳተኞችና ምንም የገቢ ምንጭ ለሌላቸው ሴቶች የተስማሚ ቴክኖሎጂ ድጋፍ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው የሴቶች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዝናሽ ከተማ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ ድጋፉ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያለመ ነው። ድጋፉ የተደረገው 15 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ከ11 ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ ለአንድ ሺህ 577 ሴቶች ሲሆን፤ ድጋፍ የተደረገላቸው ሴቶች ራሳቸውን መለወጥ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም አርዓያ መሆን አለባቸው። ድጋፍ ከተደረጉላቸው ቴክኖሎጂዎች መካከልም ዘመናዊ የእንጀራና የዳቦ መጋገሪያ፣ የችፕስ መጥበሻና ሌሎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ለአንድ ሺህ 60 ሴቶች ድጋፍ መደረጉን አውስተው፤ ይህንንም በተጨባጭ ሥራ ላይ ማዋላቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ጥናት 87 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የተሰጣቸውን ድጋፍ ተጠቅመው ውጤት ማግኘት መቻላቸውን መገንዘብ እንደተቻለ ተናግረዋል።
ከ10 በመቶ በላይ የሆኑት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ አለመግባታቸውን አንስተው፤ ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።
ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ እንዲሆኑ ቢሮው ከአጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም በተለያዩ የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የነበሩ ሴቶች ራሳቸውን ስለመቻላቸው ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂዎቹ የሴቶችን ልፋት የሚቀንሱና ወጪ ቆጣቢ ሲሆኑ፤ ሴቶች በኢኮኖሚ ሲያድጉ ጠንካራ ትውልድ የማፍራት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚችሉ የገለጹት ወይዘሮ ዝናሽ፤ ቢሮው ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የክትትል እና የቁጥጥር ሥራዎችንም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክቷል።
የሴቶች መብቃት እና መለወጥ ሀገርን የማፅናት መሠረት ነው ያሉት ምክትል ኃላፊዋ፤ ብቁ ዜጋን ለማፍራት በሚደረገው ጉዞ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነውም ብለዋል።
ቢሮው በልዩ ሁኔታ ሰው ተኮር ሥራዎች ላይ በስፋት እየሠራበት እንደሚገኝ ያነሱት ወይዘሮ ዝናሽ፤ በዚህም ድጋፉ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ብዙአየሁ ወልደጊዮርጊስ፤ ባለቤታቸው የቀን ሥራ በመሥራት እያስተዳደራቸው እንደሚገኝና እሳቸውም ልጃቸውን በመንከባከብ ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ እያሳለፉ እንደሆነ በማንሳት፤ አሁን ባገኙት ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ እንጀራ ጋግሮ በመሸጥ ባለቤታቸውን ለማገዝ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ መስከረም መንገሻ በበኩላቸው፤ በሰው ቤት ልብስ በማጠብና ተዟዙሮ የጽዳት ሥራዎችን በመሥራት ይተዳደሩ የነበረ ቢሆንም፤ በህመም ምክንያት ያንንም አቁመው እንደነበር አውስተው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም አነስተኛ የሥራ ቦታ ቢመቻችላቸው የተሻለ መሥራት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ከተስማሚ ቴክኖሎጂዎች መካከልም ዘመናዊ የእንጀራና የዳቦ መጋገሪያ፣ የችፕስ መጥበሻና ሌሎችም ይገኙበታል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም