
ሰላሙ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው በምንጃር ነው፡፡ የተለያዩ እቃዎችን ለመሸጥ ወደ አዲስ አበባ በተደጋጋሚ በሚመጣበት ወቅት በተዋወቃቸው ሰዎች አማካኝነት አዲስ አበባ ለመቅረት ልቡ ቢሸፍትም ባለመወሰኑ ምክንያት ተመልሶ ወደ ምንጃር ይሄድ ነበር፡፡ ታዲያ በአንድ አብሮ አደግ ጓደኛው አማካኝነት የተለያዩ ሥራዎችን ለመሞከር በማሰብ ኑሮውን በአዲስ አበባ ለማድረግ ወሰነ፡፡
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከጓደኛው ታደሰ ጋር በመሆን ኑሮውን በአዲስ አበባ ጀመረ፡፡ ሰላሙ ቀኑን በሥራ ማሳለፍ የሚፈልግ የነገ ሕይወቱ ከዛሬ የተሻለ ማድረግ እና መጣር መገለጫ ባሕሪው ነው፡፡ በመሆኑም የተለያዩ እቃዎችን ከመርካቶ እየወሰደ በሚኖርበት አካባቢ በመሸጥ ደንበኞችን አፍርቷል፤ በዚህም ሰላሙን የሚውቁት ሰዎች የሚፈልጓቸውን የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች ከእሱ ይገዛሉ፡፡
ሰላሙ በሙሉ ጊዜ ሥራው ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በግንበኝነት ሥራ ይተዳደራል፡፡ በመሆኑም የሚሰራበት ቦታ ከጊዜ ጊዜ ይለያያል፡፡ አንዱ የሕንጻ ሥራ ሲያልቅ ሌሎች ሥራዎችን በመፈለግ ብቻ በሥራ ላይ የሚያሳልፍበትን ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ለአንድ ዓመት ያክል ጊዜ በቆየባት አዲስ አበባ ብዙ ሰዎችን ተዋውቋል፡፡ ኑሮውን ያደረገው በሽሮሜዳ ሲሆን አሁን ላይ የሚሰራበት ቦታ በመገናኛ አካባቢ በእድሳት ላይ የሚገኝ የሕንጻ ሥራ ላይ ተቀጥሮ ይሰራል፡፡ ይህ ሥራው ከጠዋት ጀምሮ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ ሥራውን አጠናቆ ወደቤቱ ያመራል፡፡ በሥራው ላይ ከሰዎች ጋር በቶሎ ለመግባባት የማይቸገር ሲሆን ሥራውም አብረውት ከሚሰሩ ወጣቶች ጋር በጋራ እንዲውል ያደርገዋል፡፡
ጌታመሳይ በዚህ ሕንጻ ስር በጥበቃ ሥራ ይተዳደራል፡፡ በጥበቃ ሥራ ከስድስት ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጌታመሳይ ሥራውን በአንድ ቦታ ብቻ ተወስኖ ሳይሆን በተለያዩ በታዎች ላይ በፈረቃ የጥበቃ ሥራውን ይሰራል፡፡ አሁን ላይ የሚሰራበት ይህ ሕንጻ በዚያው መገናኛ አካባቢ ከሚገኘው የሥራ ቦታው ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ ቀኑን ከዚህ በፊት የሚሰራበት የሥራ ቦታ ላይ ሲያሳልፍ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ደግሞ ይህንን ሰላሙ የሚሰራበትን ሕንጻ በሌሊት ፈረቃ የጥበቃ ሥራ ላይ ይሰማራል፡፡ የመጀመሪያ የጥበቃ ሥራውን ሲጨርስም ወደዚያ በመሄድ ከእለቱ የጥበቃ ተረኛ ተረክቦ ምሽቱን ሕንጻውን ሲጠብቅ ያድራል፡፡
ሰናይት ሰላሙ ከሚሰራበት ሕንጻ ጎን የራሷን የሻይ ቡና ንግድ የምትሰራ ሲሆን በአቅራቢያዋ ባሉ ቢሮዎች፣ ሕንጻዎች ላይ እየተዘዋወረች የተለያዩ ትኩስ ነገሮችን ታቀርባለች፡፡ ሰናይት ከሰዎች ጋር ሁሉ በቶሎ የምትግባባ ናት፤ ሥራዋም ከብዙ ሰዎች ጋር የሚያገናኛት በመሆኑ ሁሉም ሰዎች ስሟን ያውቁታል እሷም ታውቃቸዋለች፡፡ ሰዎች ጠዋት ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት፣ ቀን ምሳ ሰዓት ላይ በቀን ውስጥ በአብዛኛው የትኩስ ነገር ተጠቃሚዎች ናቸው ፡፡
አዲስ ትውውቅ
ሰላሙ ለዚህ ሥራ አዲስ ባይሆንም ፤ ለቦታው ግን አዲስ ነው ፡፡ ሥራውን ሲቀላቀል ከአሰሪዎቹ ጋርም ሆነ ከሰዎች ጋር ለመግባባት ብዙም አልተቸገረም ፡፡ ሰላሙ ብቻውን የሚኖር በመሆኑ በቀኑ ውስጥ የምሳ ሰዓቱን የሚያሳልፈው በሥራ አካባቢው የሚገኝ ምግብ ቤት ከተመገበ በኋላ ሰናይት ጋር ጎራ በማለት ቡና ይጠጣል፡፡ ሰናይት ለቦታው አዲስ መሆኑን ስለተረዳች አዲስ የሆኑ ሰዎችን በፍጥነት ቦታውን እንዲላመዱት ታደርጋለች ፡፡
ሰላሙ ሥራውን ከጀመረ በኋላ በየዕለቱ ቡናም ሆነ ሻይ በሚጠጣበት ወቅት ከሰናይት ጋር በቀላሉ ሊግባባ ችሏል፡፡ ሰላሙ ሰናይት ያላትን ሥራ ጥንካሬና ከሰዎች ጋር ያላትን በቶሎ መግባባት በመመልከት በተለየ ዐይን እንዲመለከታት አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ሰናይት የምታቀርበው ሻይ ጠትቶ ከምሳ በኋላም ቡናውን እሷ ጋር ጠጥቶ እና ተጨዋውቶ ወደ ሥራው ይመለሳል፡፡
ጌታመሳይ በዚህ ሥራ ረጅም ጊዜ የቆየ በመሆኑ፤ ሰናይትን አስቀድሞ ያውቃታል ፡፡ ጌታመሳይ የብዙዎች ዐይን ውስጥ የገባችውን ሰናይትን አስቀድሞ ቢከጅላትም ሰናይት ግን አይኗ ውስጥ ባለመግባቱ ብዙውን ጊዜ በሥራ ቦታዋ የማትግባባው ሰው ቢኖር ጌታመሳይ ነው፡፡ ጌታመሳይ በባሕሪው ቁጡ እና በቶሎ የሚናደድ በመሆኑ አብረውት ካሉ ሰዎች ጋር ከሰላምታ የዘለለ ሰዓት የወሰደ ጨዋታ አይኖረውም ፡፡ ነገር ግን የሰናይት እና የሰላሙ አዲስ ግንኙነት ከሥራ በኋላ ያላቸው አብሮ መሆን በፍጹም ምቾት ነስቶታል ፡፡ ነገር ግን በዐይኑ ከመከታተል የዘለለ እና አልፎ አልፎ ከሰናይት ጋር የነበረውን የቀድሞ ግንኙነት ለመመለስ ሙከራ ያደርግ ነበር፡፡ ሰናይት ደግሞ ከአዲሱ የሕንጻው ሰራተኛ ሰላሙ ጋር ያላት ግንኙነት እየጠነከረ ይበልጥ እየተግባቡ መጡ ፡፡
የሕንጻው ሥራ ለማከናወን ጠዋት ከሁለት ሰዓት በፊት ሥራ ቦታው ላይ ይገኛል ፡፡ የጠዋት የመጀመሪያ ሥራው ሰናይት ጋር ቡና መጠጣት አብሯት ደቂቃዎችን ካሳለፈ በኋላ ሥራውን ይጀምራል ፡፡ ጌታ መሳይ ሰናይት እና ሰላሙ ተግባብተው የፍቅር ግንኙነት መጀመራቸውን ከሰማ ቆይቷል ፡፡ ጉዳዩን ለማረጋገጥ ከሰው መጠየቅም ባይጠበቅበትም የሚያየው ነገር ሁሉንም ነገር ግልጽ አድርጎለት ነበር ፡፡ ታዲያ ይህንን ንዴቱን ለመወጣት ሰላሙ ሥራውን ጨርሶ ከወጣ በኋላ እቃዎችን ይዘህ ትወጣለህ በሚል ተደጋጋሚ ፍተሻ፣ ማድረግ የጥበቃ ተረኛውን ከተቀበለ በኋላ ሥራውን ሳይጨርስ በፍጥነት እንዲወጣ ማድረግ እና የግጭት መንስኤዎችን መፍጠር ሙከራ ያደርግ ነበር ፡፡
አዳዲስ ባሕሪዎችን የሚያስተውለው ሰላሙ ጉዳዩ ሌላ እንደሆነ ባለመረዳት ለማስረዳት ጥረት ያደርጋል፡፡ ሥራውን ሲጨርስ ከአዲስ ወዳጁ ሰናይት ጋር በመሆን ስለሚመሰርቱት አዲስ ጎጆ ይመካከራሉ፡፡ 2015 ዓ.ም ሲጠናቀቅ በአዲስ ዓመት ሕይወት እንደሚጀምሩ ተነጋግረው ወስነዋል፡፡ የሁለቱን ወዳጅነትም በአካባቢው ያሉ ሰዎች አውቀዋል፡፡
ሰላሙ የሚሰራበት የሕንጻ ሥራ እየተጠናቀቀ በመሆኑ እንደሌላው ጊዜ ቀኑን ሙሉ በሥራ አያሳልፉም፡፡ ወቅቱም ክረምት ያለቀቀበት የ2015 ዓ.ም መገባደጃ ነው፡፡ በመሆኑም ሰላሙ ሌሎች ሥራዎች በመፈለግ ላይ ነው ፡፡
የከረረ ቀን
እለቱ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ቀን ነው ፡፡ 2015 አሮጌው ዓመት ሊባል 2016 ደግሞ አዲስ ዓመት ተብሎ ሊቀበል በዝግጅት ላይ ነው ፡፡ የሕንጻ ሥራው እየተገባደደ በመምጣቱ የሕንጻው ሰራተኞች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በፈረቃ ነው ፡፡ ሰላሙ ከሰዓት በኋላ በመግባት ሌሎች ሥራውን እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ ይቆያል ፡፡ ጌታመሳይ ደግሞ የማታ ፈረቃ የጥበቃ ሰራተኛ በመሆኑ ቀን ሰራተኞች ሥራቸውን ሲጨርሱ ከተረኛው የጥበቃ ሰራተኛ ሥራውን ተረክቦ ይሰራል ፡፡ ታዲያ ሰላሙ እና እሱ በመጥፎ ዐይን መተያየት ከጀመሩ ቆይተዋል ፡፡ ሰላሙን ከሰናይት ጋር
ጌታመሳይ ግርማ የተባለው ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ መገናኛ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ሟችን በቢላዋ በመውጋት ሕይወቱ እንዲያልፍ በማድረጉ ክስ ቀርቦበት በፍርድቤት ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ ተከሳሽ ለፈጸመው የሰው መግደል ወንጀል በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም