«ወጥ የሆነ ፓርቲ በሌለበት ሁኔታ የወል ትርክት መገንባት አይቻልም»  ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ

ሀገራችን የተለያዩ ሕዝቦች፣ ባሕሎች፣ እምነቶች እና ቋንቋዎች ያሏት ሀገር ናት፡፡ እነዚህ ሀገራዊ ጸጋዎች እንደ ሀገር ትልቅ የጥንካሬ ምንጭ ሊሆን እንደሚችሉ ይታመናል። በቀደሙት ጊዜያት እነዚህን ጸጋዎች በአግባቡ አውቀን እንዳንጠቀምባቸው የነጠላ ትርክት እሳቤ ሳንካ ሆኖብን ቆይቷልከዚህ ሀገራዊ ችግር ለመውጣት የብልፅግና ፓርቲ በወል ትርክቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ለዘለቄታው ከችግሩ ለመውጣት በመሰረታዊነት አስተሳሰብ ላይ በስፋት እየሰራም ይገኛል።

በዛሬው ወቅታዊ ጉዳያችን በሀገሪቱ ያሉ ልዩ ልዩ ባሕሎች፣ ታሪኮች እና ማንነቶች ያቀፈ የጋራ ኢትዮጵያዊ ትርክት ለመመስረት ምን እየተሰራ ነው ለሚለው ጥያቄ፤ ከብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (/) ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል

አዲስ ዘመን፡የነጠላ ትረካ እና የወል ትርክት ጽንሰሀሳቦችን በኢትዮ ጵያ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

ሰማ (/) ነጠላ ትርክት እሳቤው የሌሎችን ወደ ጎን በመተው፤ አንዳንድ ጊዜም የሌሎችን በማጠልሸት ስለ ራስ ብቻ ማሰብ፤ የራስን ብሔር ወይም የራስን ሀይማኖት ብቻ በማቀንቀን ላይ የተመሰረተ ትርክት ነው፡፡ ይህ በጎሳ፤ በዘር፤ በአካባቢ፤ በሀይማኖት ላይ የሚያጠነጥን ትርክት የመገንባት ፍላጎት ነው፡፡ የሌሎችን መብት የሚጋፋና ሌሎችን የማያቅፍ አካሄድን የሚከተል ነው፡፡

በአጭሩ፣ በሌላ አነጋገር፤ ራስን የመውደድ፣ ለራስ የመቆም ሁኔታ ነው፡፡ እዚህ ላይ ራስን መውደድ ችግር አይደለም፡፡ ችግሩ ራስህን ስትወድ ሌላን በመጥላት፣ ሌላን በማንቋሸሽ፣ ለራስ ያልተገባ ክብር መሥጠት ላይ የተገነባ ሲሆን ነው። ይህ እሳቤ አሁን ኢትዮጵያን አንድ ከማድረግ፤ ኢትዮጵያን ከማጠናከር፤ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ከመገንባት አኳያ ችግር አለበት ብለን እንነሳለን፡፡

የወል ትርክት ጋር ስንመጣ፤ የወል ትርክት አሰባሳቢ ነው፡፡ እኔ ወይም የእኔ ብሎ አይነሳም። እኛ በሚል፣ ሁሉንም የሚያቅፍ፣ ሁሉን የጋራ የሚያደርግ፣ ሁሉን የሚያስተሳስር ትርክት ነው፡፡

አጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች የጋራ የሆነ ታሪክ አላቸው፡፡ የጋራ የሆነ አሻራ አላቸው። የጋራ የሆነ እሴት አላቸው ብሎ ያምናል። እነዚህ በጋራ የገነባናቸውን እሴቶችና ታሪኮች ሁሉንም በሚያግባባ፣ በሚያስተሳስርና በሚያቅፍ መንገድ ለኢትዮጵያ ብልጽግና መጠቀም ይገባናል ብለን ነው የምናስበው፡፡

እኔ በሚለውና እኛ በሚለው መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ እኔ የሚለው ሌሎችን ያገላል፡፡ አግላይነት አለው፡፡ እኛ የሚለው የወል ትርክት አቃፊነት አለው፡፡ ሌሎችን የሚያቅፍ ነው፡፡ ሁሉን የሚያቅፍ ነው፡፡ “ከኔ በላይ ላሳር” የሚል አይደለም። ከኔ በላይ ማን አለ? የሚል አይደለም። ወይም ለራስ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ሌላውን የሚያንኳስስ የትረካ ስልት አይደለም፡፡

የወል ትርክት ሁሉን እኩል የሚመለክት፤ ሁሉን የሚያሰባስብ ነው፡፡ ሁሉም የራሱ የሆነ ጸጋ አለው፡፡ በኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ ሁሉም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብሎ የሚያምን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የሁሉም ነች፡፡ ሁላችንም በጋራ ያቆየናት፣ የጠበቅናት፣ ሁላችንም መስዋዕት የከፈልንላት ሀገር ናት፡፡ አንዱ የበለጠ የተለየ ነገር ያደረገ ሌላኛው ባይተዋር የሚሆንባት ኢትዮጵያ አይደለችም ያለችን፡፡ አጠቃላይ እይታችን ሰላማዊ የወል ትርክት የሚለው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡በጽንሰ ሀሳብ ረገድ እኔ የነበረው የነጠላ ትርክት ከአሁን ቀደም በሰፊው ሲቀነቀን ነበር፤ ይህ እንደ ሀገር ምን ዋጋ አስከፍሎን ነው ወደ አሰባሳቢ ወይም የወል ትርክት መምጣት የታሰበው?

ሰማ (/) እኔ የሚለው ነጠላ ትርክት ራሱ በሁለት ጫፎች የተከፈለ ነው፡፡ ግቡም አጠቃላይ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሀገር ግንባታም አይበጅም፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናጋ፣ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንቅፋት የሚሆን የተቃርኖ ትርክት አካሄድ ነው፡፡ ሁለት ጫፍ አለው፡፡ ሁለቱም ግባቸው አንድ ነው፡፡

አንደኛው ፍጹማዊ አንድነትን የሚከተል ኢትዮጵያን አንድና አንድ አድርጎ የሚያይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሀሳብ ልዩነቶችን፣ የሀይማኖት ልዩነትን፣ የብዝኃ ብሕር ማንነትን ሁሉ አይቀበልም፡፡ ኢትዮጵያን ፍጹም አንድ አድርጎ የሚመለከት፤ በሁሉም ነገር አንድ መልክ ብቻ ያላት ኢትዮጵያ የመመልከት አባዜና ዝንባሌ ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚቃረን ትርክት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ትርክት በሀይል፣ በጉልበት፣ አነዚህን ሁሉ በአንድ ሀምሳልና አስተሳሰብ ማሕቀፍ ማየት የሚፈልግ ነው፡፡

ራሱን የሚጠላ ሰው የለም፡፡ አሁን እኔ እኔነቴን ትቼ አንተነትህን ልቀበል አልችልም፡፡ አንተና እኔ አንድ መሆን የምንችለው የእኔም ያንተም እኩል የሚታይበት ሜዳ ሲኖርና እኩል መተሳሰብ የሚቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው፡፡ አንድ አድርጎ የመመልከት ፍላጎት ያለው፤ በአንድ አይነት መነጽር ሁሉንም በማየት በተጨባጭ መሬት ላይ ያሉ ልዩነቶችን ግምት ውስጥ አለማስገባት ነጠላ ትርክት ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ፍጹም ልዩነትን የሚሰብክ ነው፡፡ በአንዱ ወቅት ወይም ደግሞ በተለያየ ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ጉዳዮችን ሰማይ አድርሶ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጋራ ተጋምደው የኖሩበትን ሁኔታ የማይቀበል ፍጹም ልዩነትን የሚፈልግ፤ እኔ ራሴን እችላለሁ ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መስታጋብርና ትስስር ለማቋረጥ የሚፈልግ ትርክት ነው፡፡

ሁለቱም ነጠላ ትርክቶች ናቸው፡፡ ፍጹማዊ አንድነትን የሚቀበለውም፣ ፍጹማዊ ልዩነትንም የሚያቀነቅን ሀይል ሁለቱም ነጠላ ትርክቶች ናቸው። የሚመለከቱት የየራሳቸውን ብቻ ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ችግር አይመለከትም፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር በጋራ፣ በእኩልነትና በመተሳሰብ የጋራ እሴት ፈጥሮ፤ የጋራ ራዕይ ቀርጾ፤ የጋራ ሕልም ይዞ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድ አድርጎ የነበረውን እሴት ለማስቀጠል ፍላጎት የላቸውም፡፡

በአጭሩ በሌላ አገላለጽ፤ ነጠላ ትርክት የራስን ብቻ ከፍ አድርጎ መውደድ፣ የሀገር ፍቅር ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ነው፡፡ የወል ትርክት የራስንም የሌላውንም እኩል መውደድ ነው፡፡ ሌሎችንም እንደራስህ የምትመለከትበትና የምታከብርበት መንገድ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡የኢትዮጵያ ታሪካዊና ባሕላዊ የጋራ ጉዳዮች የወል ትርክቶቿን ከመቅረጽ አኳያ ምን ሚና አላቸው?

ሰማ (/) በነገራችን ላይ ሶስት ትልልቅ ጉዳዮችን ማንሳት እንችላለን፡፡ አንዱ ድሮ አያቶቻችንና አባቶቻችን የሰሩት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የዓድዋ ጉዳይ ነው፡፡ ነጮችም የሚያምኑት ጥቁር ነጭን አያሸንፍም፤ አሸንፎም አያውቅም የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ በዚህ ፕሮፖጋንዳ ሁሉም አፍሪካዊ ነጭ ጥይት በተኮሰ ቁጥር ምንም ሳያቅማሙ ቀኝ የተገዙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

እነዚህ ሀገራት አፍሪካን እንደ ቅርጫ በተከፋፈሉበት ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ይሆናል ብለው ነጮች በጣሊያን አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፤ ኢትዮጵያዊ ጥቁርም ሰው ነው ነጭም ሰው ነው፤ ሀገሬን እገዛለሁ ብሎ የሚመጣ ኃይል፤ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ ቢሆንም በምንም መልኩ እኔን ሊገዛኝ አይችልም የሚል የጸና እሳቤ አጋጥሟቸዋል፡፡

ሀገሬን አሳልፌ አልሰጥም በማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ የዳግማዊ አጼ ምኒሊክን አዋጅ ከጫፍ እስከ ጫፍ፤ እኔ የእከሌ ብሔር ነኝ፤ የታያዘው ቦታ የኔ አይደለም፣ ነጭ ዳር ድንበር ጥሶ በገባበት አካባቢ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሆ ብሎ መስዋዕትነት ከፍሏል። በታሪክም ጥቁር ነጭን እንደሚያሸንፍ፤ ነጭም በጥቁር እንደሚሸነፍ፤ ድሉ ሪከርድ ተደርጎ ተቀምጧል፤ ሀገሪቱም ሉዋላዊነቷን አስከብራለች፡፡

ይህ የሁሉም ኢትዮጵያ የታሪክ ቅርስ ነው። ዓድዋ በሰሜን አካባቢ ትግራይ ክልል የተካሄደ ሁነት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተሳተፉበት እንጂ የትግራይ ተወላጆች ብቻ ወይም ደግሞ የአማራ ተወላጆች ብቻ የተሳተፉበት አይደለም፡፡ ከመሀል ሀገር የሄዱ አሉ። በስንቅ፣ በሎጀስቲክስ፣ በሰው ኃይል ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሳተፈበት የጋራ የወል ትርክት ነው። ኢትዮጵያውያን አሸነፉ ነው የሚባለው። በዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይኮራል፡፡ ዛሬ የምንኮ ራበት የአያቶቻችን ታሪክ ነው፡፡

ሌላውና ሁለተኛው ጉዳይ አፍሪካውያን በተለይም ጥቁሮች ስልጣኔ የማይገባቸው ናቸው፤ ወደ ኋላ የቀሩ ናቸው፤ በልመና የሚኖሩ ናቸው የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካውያን፤ በአድዋ ላይ ድል የተቀዳጀናቸው ኃይሎችን ሳይቀሩ እጃችንን ዘርግተን ስንዴ የምንለምበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡

 

ጸጋ አለ:: ሸበሌ፣ ጎዴ፣ አፍዴር፣ ዋርዴር ላይም ጸጋ አለ:: ደቡብ ኢትዮጵያ ኦሞ፣ ጌዲዮ፣ ቤኒሻንጉል ላይም ጸጋ አለ:: አፋር፣ አማራም፣ ኦሮሚያም ሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ጸጋ አለ:: ይህን ጸጋ ተጠቅመው ሁሉንም ከድህነት የማውጣት አጀንዳ የጋራ አጀንደ የወል ትርክት ነው:: ይህም የኢትዮጵያን ክብር ከፍ የማድረግ ጉዳይ ነው። ሁሉም በጋራ ተረባርቦ ኢትዮጵያን ከልመናና ከተረጂነት የማውጣት ጉዳይ ሌላ ሁለተኛ የታሪክ እጥፋት ነው::

በዚህ ረገድ የብልፅግና መንግሥት ሁለተኛ እጥፋት ለመስራት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው። እንዲሚታወቀው ስንዴ በሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመረትና ከልመና ለመውጣት ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ አዎንታዊና የላቀ ውጤት ተመዝግቦ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ እውቅና የሰጡበት ጉዳይ ነው:: ይህ የወል ትርክታችን ነው:: የእኔ ነው፣ የእኔ ነው የሚል ጉዳይ አይደለም:: ሁሉም የተረባረቡበት ሁለተኛው የወል ትርክታችን ነው::

ሦስተኛ ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን ያካተተ፣ የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባይተዋር ያላደረገ፣ አንዱ ከሌላው የሰለጠነና የተለየ መወሰን የሚችልበት፤ አንዱ ደግሞ የተወሰነውን ውሳኔ ይተግብር ከሚለው አስተሳሰብ በመውጣት ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ ዘር፣ ሀይማኖት፣ ቋንቋ፣ ጂኦግራፊ ሳይወስናቸው፤ በሀገሪቱ ግዛታዊ ክልል ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሉ ሕዝቦች በፕሮግራም ውስጥ ተካተው መሳተፍ የሚችሉበት አንድ ወጥ ፓርቲ እንዲመሰረት ተደርጓል:: ይህ ሌላኛው ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው::

ከፊውዳሉ ሥርዓት መውደቅ በኋላ በፓርቲ ስም የተንቀሳቀሰው ኢሰፓ ነው:: እሱም ቢሆን ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ያደረገ አልነበረም:: ከአባልነት የሚገድባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ነበሩ:: ከኮለኔል በላይ ያሉ የሰራዊቱ አባላት በፓርቲው ውስጥ እንዲሳተፉ አልፈቀደም:: የፊውዳል ሥርአት አካል የነበሩትንም፤ ርዝራዥና የፊውዳል ዘር በማለት የፓርቲው አባል እንዳይሆኑ ከልክሏል:: የፓርቲው አባል ለመሆን ያስቀመጣቸው መስፈርቶች ነበሩ።

በኢሕአዴግ ደግሞ አጋርና ዋና በሚል የሀገሪቱን ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ አካል የተለየ የሕብረተሰብ ክፍል ኤሊት ወይም ምሁር የሚደራጅበት፤ እንደገና ደግሞ በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ያሉ ሕዝቦች ደግሞ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚወስነውን ውሳኔ እንዲተገብሩ እንጂ በውሳኔው እንዳይሳተፉ ያደረገ ነው:: ሀገሪቱን የሚመራ መሪ እንኳን የመምረጥ ዕድል የማያገኙበት የፖለቲካ ሥርዓት ነበር::

ኢሕአዴግ ሀብታም የፓርቲ አባል አይሆንም የሚል ገደብ አስቀምጦ ነበር:: በኢሰፓ ውስጥ የፓርቲ አባል የሆነ እንደማይቀበል፤ በአጋር ድርጅቶች ውስጥም ሆነ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ አባል የሆነን እንደማያካትት ገደብ አስቀምጦ ነበር::

አሁን ሁሉም በሀገሩ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ መብት አለው:: ኢሰፓ የነበረ ሰው፣ ኢሕአዴግ የነበረ ሰው አንልም:: በኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ መበልጸግ የሚችል ሰው፤ በራሱና በሥራው የሚተማመን፤ በተልዕኮ ዙሪያ የራሱን ተልዕኮ ይዞ ሀገርን ለማበልጸግ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ኃይል ፕሮግራሙን አምኖ የተቀበለ ሰው ያለ ገደብ አባል መሆን ይችላል::

በዚህ ብቻ ሳይሆን የትኛውም ዘርና ኃይማኖት ሳይከልከልና ገደብ ሳይቀመጥ ከሀገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ ያሉ ሕዝቦች አባል የሚሆኑበትና በአንድ ፓርቲ ማሕቀፍ ውስጥ የሚደራጁበት አንድ ትልቅ የኢትዮጵያ ፓርቲ መስርተናል::

ፓርቲዎች ከዚህ በፊት በመደብ ተቃርኖ የተለየ የሕብረተሰብ ጥቅም እናስከብራለን ብለው ነው የሚንቀሳቀሱት:: ብልጽግና በተለየ ሁኔታ ጥቅም አስከብርለታለሁ የሚል የሕብረተሰብ ክፍል የለውም:: አርሶአደርን በተለየ ሁኔታ ከአርብቶአደሩ ለይቶ ጥቅም አያስከብርም። አርብቶአደሩን ከከተማው ነዋሪ በተለየ ሁኔታ ጥቅም አያስከብርም። ሁሉም የራሳቸው ጥቅም ሊከበርላቸው ይገባል የሚል ነው::

ብልፅግና ሁሉም በየራሳቸው ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብሎ ነው የሚያስበው። ስለዚህ ከዚህ አኳያ የተለየ ሀሳብም ያላቸው ኃይሎች እንደ ጠላት መፈረጅ የለባቸውም:: ለሀገሬ እጠቅማለሁ ብለው እስከመጡ ድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሀሳባቸውን ይዘው ይቀርባሉ፤ ፈራጁ ዳኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው እንጂ፤ እኛን ጠላታቸው ብለን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልንነግረው አይገባም:: የሚጠቅም ነገር ይዛችሁ አልመጣችሁም የሚለውን ፍርድና ዳኝነቱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንስጥ ብሎ የሚያምን ነው::

ከዚህ አኳያ ለዴሞክራሲ መሠረት የሚሆን፤ ሀገርን የሚያሻግር አሰባሳቢ ትርክት የሚመች ነው:: አሁን ሁሉም የእኔ ነው ብሎ የሚያስበው ነጠላ ትርክት ሊኖር አይችልም:: እኔ ለጎጃም፣ እኔ ለወላይታ፣ እኔ ለጌዲዮ፣ እኔ ለጋሞ፣ እኔ ለጉራጌ፣ እኔ ለሲዳማ ብቻ ሊል አይችልም:: ሁሉም ለብልጽግና ነው:: ብልፅግና ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ በሁሉም ቦታ አለ:: ከዚህ አኳያ በጋራ ይወስናል:: ከየአካባቢዎች ተጨባጭ ሁኔታ አንጻርም ታይቶ እንዲወሰን አቅጣጫ ይወርዳል:: ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሄ መፈለግ የሁላችንም የጋራ ሥራ አድርጎ የሚሄድበትን የወል ትርክትን ለመገንባት ምቹ ሁኔታ ያስፈልጋል::

ወጥ የሆነ ፓርቲ በሌለበት ሁኔታ የወል ትርክት መገንባት አይቻልም:: አማራ በራሱ ተደራጅቶ፣ ኦሮሞ በራሱ ተደራጅቶ፣ ሱማሌ በራሱ ተደራጅቶ የወል ትርክት መገንባት አይቻልም:: ሁሉም የየራሱ ነጠላ ትርክት የሚገነባበትን ሁኔታ የሚያስቀር የወል ትርክት ግንባታ መሰረት የሚሆን መሠረት ያለውና ሁሉን የሚያካትት፤ የሚያስተሳስር ፓርቲ መመስረት ያስፈልግ ነበር:: ይሄ ተደርጓል:: ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች ሚናቸው የጎላ ናቸው::

ከልማት ሥራዎች አኳያም የሕዳሴ ግድብ አለ:: የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነው:: ከአርሶአደር እስከ አርብቶ አደር፣ ከአዛውንት እስከ ሕጻናት፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የኛ ነው ብለው የቆሙለት፤ የኛ ነው ብለው መስዋዕትነት የከፈሉለት፤ ትልቅ የልማት አሻራ ነው። በኢትዮጵያውያን ሀብት የመጣ ነው:: ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት የመጠቀም መብቷን ያጎናጸፈ ታሪክ የተሰራበት ነው:: ይሄ የወል ትርክታችን ውጤት ነው:: የአንድ አካባቢ፣ የአንድ ጾታ ወይም ደግሞ የአንድ ብሔር፣ ወይም የአንድ ሀይማኖት ውጤት አይደለም::

ከዚህ አኳያ በየአካባቢው ያሉ ነጠላ ትርክቶች ለኢትዮጵያ አይበጁም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የተዋለደ የተጋመደ፣ ብዙ አብሮ የኖረ፣ ብዙ ሂደቶችን ያሳለፈ፣ ብዙ እሴት ያለው ስለሆነ ከነጠላ ትርክት ይልቅ የወል ትርክት ያስፈልገዋል:: የወል ትርክቱ ደግሞ የሚያስተሳስር፤ የበለጠ የሚያጋምድ አንድነታችንን የሚያጠናክር ሊሆን ይገባል ብሎ በማመን ላይ የተመሰረተ ነው::

አዲስ ዘመን፡ከወል ትርክት አኳያ የወደፊት የኢትዮጵያ ራዕይ ምንድነው?

ሰማ (/) – እኛ ይዘን የመጣነው ሕልም ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው:: እነዚህም ሦስት ነገሮች ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው:: አንዱ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የተረጋገጠባት የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ጉዳይ ነው:: ልዕለ ሀያል ሀገር የመገንባት ጉዳይ ነው:: ኢትዮጵያ ልዕለ ሀያል እንድትሆን ነው:: ለብቻው ልዕለ ሀያል የሚሆን ብሔር፣ ሀይማኖት፣ ዘርና ጾታ የለም:: ልዕለ ሀያል ኢትዮጵያን እንገባ ስንል ለሁላችንም የሆነች ኢትዮጵያን እንገነባለን ማለታችን ነው::

ሁለተኛው ሰብዓዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው። ሕልማችን ሰብዓዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው ስንል ዝም ብሎ በቁስ ሀብታም መሆን ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብ የበለጸገ ማድረግ ነው::

ነጠላ ትርክት ያፋጀንና ቀውስን የጨመረ ነው:: በአንዳንድ ሀገሮች ላይ እንደሚታየው ለብቻ ማደግ የሚቻልበት ሁኔታ የለም:: አይደለም በአንድ ሀገር ውስጥ ሆነን ከጎረቤት ጋር እንኳን ካልተስማማንና ካልተደማመጥን በጋራ ካልተደጋገፍን መበልፀግ የሚባል ነገር የለም:: ስለዚህ ሰብዓዊ ብልፅግና ያስፈልጋል::

በነጠላ ትርክት አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው ጦርነትና ግጭት እየጠመቁ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ለማጫረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ታቅበው፤ በሰላማዊ መንገድ እየተናገርን ሕዝቡ ደግሞ በወሳኝነት ሚና ገብቶ ጫና ፈጥሮ እነዚህን ኃይሎች አደብ ገዝተው ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ ለማድረግ እየሰራን ነው::

ሰብዓዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ መጀመሪያ ነጠላ ትርክት ይዘው እየተዋጉ ያሉት ግጭት ውስጥ የገቡ ኃይሎች ጭምር በአስተሳሰብ ተቀይረው እንዲመጡ ነው:: አሁን አንዳንዶች ይህንን አስተሳሰብ እየተቀበሉ በሰላማዊ ድርድር ውስጥ ወደ ውይይት ገብተዋል:: ውይይቱ ላይ እያደረግን ያለነው ዋናው ነጥብ ሰብዓዊ ብልጽግናን ለመገንባት በሰው አስተሳሰብና አዕምሮ ውስጥ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መሆን አለባት የሚለውን እንዲገነዘብ የማድረግ፣ በአዕምሮና በአስተሳሰብ እንዲበለፅግ ማድረግ ነው:: ብልፅግና በአስተሳሰብ የበለፀገ በቁስ መበልፀግ ይችላል ብሎ የሚያምን ነው::

ሦሥተኛ ልዕለ ኃያል አፍሪካዊት የሆነች ሀገር መገንባት ነው:: ኢትዮጵያ የዚህ መሠረት አላት። የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረት ትልቅ ሚና የተጫወተች ናት:: እግር ኳስ ላይ ትልቅ ሚና ነበራት። በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የአፍሪካ ድምጽ የነበረች ናት:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወቅቱ ሊግ ኦፍ ኔሽን ሲመሰረት ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት:: ከዚህ አኳያ በአፍሪካ ልዕለ ኃያል ሆኖ ብዙ ሀገራት ሲጣሉ ስታስታርቅ የነበረች ናት:: ብዙ ሀገራት ብሔራዊ ቀውስ ውስጥ ሲገቡ ወታደር ልካ የታደገች ሀገር ናት:: ብዙ መሠረት ያላት ስለሆነ በአፍሪካ በኢኮኖሚውም በዲፕሎማሲውም በሁሉም መስክ ልዕለ ኃያል ሆና እንድትቀጥል የማድረግ ሕልም አለ:: ይህ ሁሉንም የሚያኮራ ነው::

አዲስ ዘመን፡የወል ትርክት ግንባታን መነሻ በማድረግ ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ::

ሰማ (/) እኔም እጅግ አመሰግናለሁ።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You