‹‹ትልቁ ገንዘብ ጊዜ ነው›› – ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ

ሙዚቃ መክሊቱ መሆኑን አውቆ፤ ለሥራው በሰጠው ትኩረት ዛሬ ላይ መድረስ የሚፈልግበት የሕይወት መስመር ላይ ይገኛል:: በስሙ የተሰየመ የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበም ሥራውን ለአድማጭ ያደረሰ ሲሆን፤ በወጣትነቱ በብዙዎች ዘንድ እውቅናንና ተወዳጅነትን አትርፏል:: በታዳጊነቱ አርአያ ያደረጋቸው ታላላቅ የሀገሪቱ ድምጻውያን የደረሱበት ደረጃ መድረስ ህልሙ ነው::

ዛሬ ላይ ይህንን ወጣት ድምጻዊ አርአያ የሚያደርጉ ታዳጊዎች እየተፈጠሩ ናቸው:: በተለያዩ መድረኮች ላይ በመጋበዝ ስለ ሙያዊ ሕይወቱ ለታዳጊ ወጣቶች ልምዱን ያካፍላል:: ወጣት እና ዝነኛ ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ የዛሬው እንግዳችን ነው::

ተወልዶ ያደገው ኮልፌ ቀራኒዮ አካባቢ ሲሆን፤ ለወላጆቹ ሁለተኛ ልጅ ነው:: በአቅራቢያው የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ በመኖሩ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ አባላት በእጅጉ ይስቡት እንደነበር ያስታውሳል:: እናቱ የሙዚቃ አድናቂ በመሆናቸው ቤት ውስጥ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ላይ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ያዳምጣሉ:: ከእናቱ ጋር የተለያዩ ሙዚቃዎች የሚሰማው ልዑል፤ እናቱ በራሱ እንዲያንጎራጉር አድርገውታል:: በቤት ውስጥ፣ በጎረቤት እንዲሁም በትምህርት ቤት ሲያንጎራጉር ከሰሙት ሰዎች ቀጥልበት የሚል ማበረታቻዎችን አግኝቷል::

በ11 ዓመቱ የሜሪጆይ ክበብን በመቀላቀል ተሰጥኦውን ማዳበር ተያያዘ:: የልዑል አስተዳደግ እና የቤተሰቦቹ አቋም ልጆች በተሳካላቸው እና ጎበዝ በሆኑበት ሙያ ላይ ክህሎት እና ችሎታ ላይ ድጋፍ በማድረግ ስኬታማ እንዲሆኑ ማገዝ በመሆኑ አትዝፈን ብሎ የከለከለው አልነበረም:: ‹‹እናቴ በሥራዬ በጣም ታበረታታኛለች፤ ከልምምድ እንድቀርም አትፈልግም ነበር::›› የሚለው ልዑል፤ እናቱ የድምጻዊ ነዋይ ደበበ አድናቂ ከመሆናቸውም በላይ የተለያዩ ድምጻዊያንን ሥራ እንዲሠራ ይጠቁሙት እንደነበር ያስታውሳል::

በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን በማስተማር በማሳደግ የሙያውን መንገድ በማሳየት እና እድል በመስጠት የሚታወቁት ተስፋዬ አበበ፤ በብዙዎች አጠራር ፋዘር ቤት የኪነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የልዑል አንዱ ራሱን ያበቃበት ሥፍራ ነበር:: የሙዚቃ ሙያውን ለማሳደግ አንድ ርምጃ ያራመደው የኢትዮጵያን አይድል ኮካኮላ ሱፐር ስታር የድምጻውያን ውድድር ደግሞ ሌላኛው ነው:: ልዑል በዚህ ውድድር ውስጥ ሲሳተፍ ገና 15 ዓመቱ ነበር::

በመጀመሪያው ዙር ውድድር ላይ ከዳኞች የተሰጠው መልካም አስተያየት ከአንደኛው ውድድር ወደ ሌላኛው ከማለፍ በላይ ይበልጥ ራሱን እያሻሻለ ለአሸናፊነት እንዲወዳደር አድርጎታል:: በውድድሩ ላይም በርካታ ባለሙያዎችን ለማግኘት ችሏል::

በውድድሩ በርካታ ደጋፊዎች እንደነበሩት የሚያስታውሰው ልዑል፤ በየዙሩ ላይ በነበረው የድምጽ አሰጣጥ ብልጫም ነበረው:: ልዑል በውድደሩ ላይ በነበረው ብቃት በሁለተኛ ደረጃ ሊያጠናቅቅ ችሏል:: የሙዚቃ ሥራን ሙያው አድርጎ መቀጠል እና ትልቅ ድምጻዊ የመሆን ዓላማን የያዘው ልዑል፤ ውድድሩ በርካታ እድሎችን ፈጥሮለታል::

ከውድድሩ ባገኘው የገንዘብ ሽልማት የመጀመሪያ ሥራውን ግጥምና ዜማው የዶክተር ተስፋዬ አበበ የሆነውን ዓይነ በጎ የተሰኘ በድምጻዊ ታደለ በቀለ እና ሂሩት በቀለ የተሠራ ቆየት ያለ ሙዚቃ ከድምጻዊ እቴነሽ ደመቀ ጋር በድጋሚ በመሥራት ከአድማጮች ጋር ሊተዋወቅ ችሏል::

‹‹ሙዚቃን መክሊቴ ነው ብዬ ከያዝኩት ጀምሮ፤ ምኞቴ በማደንቃቸው ድምጻውያን ልክ የሆነ ብዙ አልበም ያለው ድምጻዊ መሆን ነበር::›› የሚለው ድምፃዊ ልዑል፤ አንጋፋ ባለሙያዎችን በሚያገኛቸው ጊዜ የመጡበትን መንገድ የመጠየቅ ልምድ እንዳለውም ይገልጻል:: አንድ በጅምር ላይ ያለ አርቲስት ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር ማወቅ ለዓላማው ጠንክሮ መሥራት ይገባዋል የሚል እምነት አለው::

በዚህ ሙያ ውስጥ የፊልም ደራሲ እና ፕሮዲውሰር የሆነው ታላቅ ወንድሙ፤ በሙያው ላይ ይበልጥ እንዲያተኩርና ስኬታማ እንዲሆን እንዳገዘው ገልጿል:: ‹‹በጣም የምወዳቸው ድምጻውያን እና ረጅም ዓመት የቆዩ ባለሙያዎች የሄዱበትን መንገድ መጓዜ አሁን ላይ የደረስኩበት ደረጃ ላይ እንድደርስ አድርጎኛል::›› ይላል::

ብዙም ሳይቆይ በሚሠራበት የኤክስፕረስ ባንድ ውስጥ ‹‹ቀረሁ እንጂ›› የተሰኘ ነጠላ ዜማንም ለአድማጭ አስተዋውቋል:: ልዑል ሁለቱን የሙዚቃ ሥራዎቹን ሲያቀርብ በርካታ ድምጻውያንን ያፈራው 30 ዓመት ያስቆጠረው ኤክስፕረስ ባንድ ውስጥም የመሥራት እድል ነበረው::

ድምጻዊ ልዑል በተለያየ ወቅት ኮከብ እና በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አሁንም ድረስ ተወዳጅ የሆኑ የሁለት ድምጻውያን አድናቂ ነው:: ድምጻዊ ቴዎድሮስ ታደሰ እና ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ በሙዚቃ ሥራዎቻቸው ባላቸው ተቀባይነት እና የሕይወት ልምዳቸው አርአያ የሚያደርጋቸው ናቸው::

በተለያየ ጊዜ በሥራ አጋጣሚ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያገኛቸው አንጋፋ ድምጻውያን እና ባለሙያዎች ያላቸውን ልምድ እና አስተያየታቸውን እንደሚያካፍሉት የሚያስታውሰው ልዑል፤ የማይረሳው ትልቅ ምክር እንዳለው ይገልጻል:: ‹‹ ነገር ባጠረ ቁጥር ያምራል ይባላል:: ሁልጊዜም የማስታውሰው ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ጋር በአንድ መድረክ ላይ ተገናኝተን ሥራዎቼን ሳቀርብ ካየኝ በኋላ፤ ‹አሁን የያዝከውን መንገድ ይዘህ ብቻ ወደፊት ሂድ ይታየኛል› ያለኝን መቼም አልረሳውም::›› ይላል::

በሙዚቃ ሥራው ውስጥ ያሉ በርካታ ድምጻውያን በተለይም በአሁን ሰዓት የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበማቸውን ከማውጣታቸው በፊት የተወሰኑ ነጠላ ዜማዎችን አስቀድመው ወደ ሕዝብ ያደርሳሉ:: ይህም አልበሙ ከመውጣቱ በፊት የራሳቸውን አድማጭ ለመገንባት እና ለመተዋወቅ ሲሆን፤ የአልበም ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልገውን የገንዘብ ዝግጅት እና ከብዙ ባለሙያዎች ጋር ለመተዋወቅ የሚረዳቸው ነው:: ታዲያ የአልበም ሥራቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው በተለያዩ ክለቦች ላይ በመሥራት፣ ነጠላ ዜማዎችን በማውጣት ከሀገር ውጭም በተለያዩ መድረኮች ላይ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ በመሥራት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ::

መዳረሻው ብዙ አልበም ያለው ትልቅ አርቲስት መሆን እንደሆነ የሚናገረው ድምጻዊ ልዑል፤ የመጀመሪያ የአልበም ሥራውን አስቀድሞ ጀምሮት እንደነበር ይናገራል:: ‹‹ አንድ ድምጻዊ ነጠላ ዜማ ካወጣ በኋላ፤ አረብ ሀገራት ላይ ሌሎች ቦታዎች ላይ የመሥራት እድሉ ሰፊ ነው:: ይህ የሥራ ሂደት ገንዘብ ለማግኘት ቢጠቅምም አልበም ለመሥራት ግን አይመችም::›› የሚለው ድምፃዊ ልዑል፤ ማንኛውንም የሕይወት ዓላማ ለማሳካት አንዱን መንገድ ለመምረጥ ትርፍ እና ኪሳራውን ማጥናት የተለመደ ነው ይላል::

ነገር ግን አንዳንድ ወጣቶች ምናልባትም የአጭር ጊዜ የተሻለ የገንዘብ ክፍያ በመጓጓት ዓላማቸውን እና ህልማቸውን ለማዘግየት ሲወስኑ ይታያል:: ላመኑበት ላስቀመጡት ግብ ትኩረት አድርጎ መሥራትን እንጂ ጊዜያዊ ነገሮች እምብዛም የማያጓጉት ልዑል ግን፤ ትልቁ ገንዘብ ጊዜ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለው:: በመሆኑም ፍላጎቱ አልበም መሥራት በመሆኑ ለጊዜው በውጭ ሀገር ሥራዎቹን ለማቅረብ የሚደረጉለትን ጥሪዎች በማዘግየት የአልበም ሥራዎቹ ላይ ትኩረቱን እንዳደረገም ይናገራል::

የሙዚቃ አልበም ሥራ ከነጠላ ዜማ ለየት ባለ ትኩረት የሚሠራ እና ድምጻዊው የራሱን አቅም አውጥቶ የሚያሳይበት ዘመንን የሚሻገር ነው:: ይህ የመጀመሪያ የአልበም ሥራ በመሆኑ የሚኖረው ትኩረት ለየት ያለ ይሆናል:: ለዚህም ይመስላል የልዑል የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሙ ዝግጅት ስድስት ዓመት ያህል ጊዜን ወስዶበታል::

ለታዳጊ ድምጻውያን የሚለው እንዳለው የሚናገረው ድምፃዊ ልዑል፤ ‹‹አልበም በሚሠሩበት ወቅት የራሳቸውን ስሜት እና የሙዚቃ ምርጫ በደንብ ቢያጠኑ፤ ሰዎች የወደዱትን ሳይሆን ራሳቸው የወደዱትን ቢመርጡ፤ ጊዜ ወስደው ራሳቸውን የሚገልጽ፤ አቅማቸውን የሚመጥን ሥራ ለመሥራት መጣር እንጂ መቸኮል አይጠበቅባቸውም ባይ ነኝ::›› የሚለው ልዑል፤ የሙዚቃ ምርጫው እና ፍላጎቱን የሚረዱ ባለሙያዎችን ለማግኘት በርካታ ጊዜያት እንደወሰደበት ያስረዳል::

የሙዚቃ ሥራዎቹን ከመረጠ በኋላ እና ድምጹን ወደ መቅዳት ከገባ በኋላ የሠራቸውን የሙዚቃ ስብስቦች መጨረሻቸው ሕዝብ ጋር ነውና የሙዚቃ አድማጭ የሆኑ በተለያየ ጊዜ የሚያገኛቸውን የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች በማሰማት ምላሻቸውን ይጠይቅ ነበር::

ከስድስት ዓመት ቆይታ በኋላ ልዑል የተሰኘ መጠሪያ ተሰጥቶት ይፋ የተደረገው የመጀመሪያ አልበም፤ ከአንጋፋ እስከ ወጣት ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል:: 14 የሙዚቃ ሥራዎችን በያዘው አልበም በግጥምና በዜማው ድምጻዊ ሞገስ ተካ፣ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ፣ ወንደሰን ይሁብ ፣ ምህረተአብ ደስታ ፣ እሱባለሁ ይታየው (የሺ)፣ ደጎል መኮንን ተሳትፈውበታል:: በሙዚቃ ቅንብሩ እንዲሁ ኪሩቤል ተስፋዬ፣ ኤክስፕረስ ባንድ፣ አቤል ጳውሎስ ይገኙበታል::

የቀድሞው ዘመን ድምጻውያን ሥራዎቻቸውን በካሴት፣ በሲዲ ጊዜው በፈጠራቸው ቴክኖሎጂዎች ለአድማጭ ያደርሳሉ:: አሁን ባለንበት ጊዜ ደግሞ ድምጻውያን የአልበም ሥራዎቻቸውን ለአሳታሚ መሸጥ ሳይጠበቅባቸው የዩቱዩብ ማህበራዊ ገጽ መተግበሪያ በራሳቸው ገጽ ላይ ሥራቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተላለፍ ያስችላቸዋል:: ይህ ገጽ ሙዚቃውን የተመለከተውን ሰው ብዛት ፣ የሰዎችን ግልጽ አስተያየት በየጊዜው የሚያሳይ በመሆኑ ውጤቱ በቶሎ የሚታይ ነው:: ‹‹ስድስት ዓመት የተለፋበት አልበም ቢሆንም፤ ይፋ የሚደረግበት ሰዓት ላይ ምላሹ ምን ይሆናል የሚለው ላይ ፍርሃት ነበር::›› የሚለው ልዑል አልበም ሥራው በገጹ ላይ ከተለቀቀ በኋላ ሙዚቃው በአጭር ጊዜ ተቀባይነትን ያገኘ ሲሆን በወቅቱ ከፍተኛ የእይታ መጠንም ነበረው::

ቴክኖሎጂው የፈጠረው የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ራሳቸው መቆጣጠር በሚችሉት ገጽ ላይ ማጋራት የሚችሉት መሆኑ በረጅም ጊዜ ጥረትም ቢሆን መፍትሔ ሊገኝለት ያልቻለውን የኮፒራይት መብት ለማስከበር የተሻለ መንገድ መሆኑንም ልዑል ጠቁሟል:: ‹‹የኪነ-ጥበብ ሥራ ባለሙያው በገንዘብ ፣ በጊዜ፣ የፈጠራ አቅሙን በመጠቀም የሚሠራው ነው:: ስለዚህ ነገ ለትውልድ ለልጅ ልጆቹ የሚያስተላልፈው በመሆኑ የኮፒራይት መብቱን በተቻለ መጠን ማስጠበቅ አለበት::›› ይላል::

ልዑል በዚህ አጋጣሚም ጊዜው የሚፈጥራቸውን ቴክኖሎጂዎች ወቅቱ የሚጠይቃቸውን ክህሎቶች በማዳበር ባለሙያዎች ራሳቸውን በተሻለ መልኩ ማሳየት እና የሚገባቸውን ጥቅም ማግኘት እንደሚችሉ ይገልጻል:: ልዑል ሲሳይ በተሰኘው የዩቱዩብ ገጹ ከ165 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፤ የሙዚቃ ሥራዎቹም እስካሁን ድረስ ከ36 ሚሊዮን በላይ እይታን አግኝተዋል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የሙዚቃ ሥራዎች ማሰራጫዎች ላይ በራሱ ስም ማስተላለፍ ችሏል::

በመጀመሪያ ለአድማጭ ባደረሰው የሙዚቃ አልበም ሥራው ጥሩ ተቀባይነትን ያገኘው ልዑል፤ የኮንሰርት ሥራውን ያቀረበ ሲሆን፤ ከሀገር ውጭ ሥራውን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ይገኛል:: የሁለተኛ የሙዚቃ አልበም ሥራውንም ጀምሯል::

‹‹ዝና በራሱ የሚሰጠው ጥሩ እድል እንዳለ ሁሉ መጥፎ ጎንም አለው:: በመሆኑም ይህንን ማመጣጠን የአርቲስቱ ሥራ ነው:: ለዚህ ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር ዓላማን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል::›› ብሏል::

ልዑል ራሱን በሙያው ለማሳደግ ልምምድ በማድረግ ተሰጥኦውን ሊያሳድግለት በሚችሉ ተግባራት ላይ በርካታ ጊዜውን ያሳልፋል:: ከድምጻዊነት ባሻገርም የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት የሚያስደስተው ልዑል፤ ፒያኖ እና ጊታር የመጫወት ልምድ አለው::

ልዑል ሙዚቃን በጀመረበት ወቅት የተለያዩ አንጋፋ ድምጻውያን የሙዚቃ ሥራቸውን በማዜም የራሱን መንገድ መፍጠር ችሏል:: የአልበም ሥራውን ይፋ ካደረገ በኋላ የድምጽ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች የእርሱን የሙዚቃ ሥራዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይጫወታሉ:: ይህ ለልዑል ልዩ ስሜት የሚፈጥር ብቻም ሳይሆን ይበልጥ ለመሥራት የሚያበረታታው እንደሆነ ገልጿል:: የተለያዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊ ድምጻውያን የሙዚቃ ሥራዎች ፕሮዲውስ ማድረግ የራሱን ሪከርዲንግ ኩባንያ መክፈት ከወደፊት እቅዶቹ ውስጥ ነው::

ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ ዛሬ ላይ የደረሰበት ደረጃ ከጥንካሬው ለዓላማው ከሰጠው ትኩረት ባሻገር፤ በዙሪያው ያገዙትን ቤተሰቦቹንና ባለሙያዎችን አመስግኗል:: ሁልጊዜም የሚያበረታቱትን እናቱን ወይዘሮ አበበች በሥራዎቹ በማማከር በቅርቡ ሆኖ የሚደግፈውን ታላቅ ወንድሙን መላኩ ሲሳይ ያመሰግናል:: በአልበም ሥራ ውስጥ የተሳተፉ ባለሙያዎችን፣ ጥሩ ምላሽ በመስጠት ለደገፉት አድማጮቹ ጭምር ምስጋናውን አቅርቧል::

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You