ሰዎች ለመዝናናት ምርጫቸው የተለያየ ነው። አንዳንዶች ተመሳሳይ የመዝናኛ ቦታን በተመሳሳይ ሰዓት እና ጊዜ ያደርጋሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አዕምሯቸውን ከውጥረት ነጻ ለማድረግ የሚያሳልፉት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቢሆን ይመርጣሉ፡፡ የመዝናኛ ስፍራዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ በርከት ብለው በየደረጃው ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶች ከረጅም ሥራ ቀን በኋላ በፍጥነት ወደቤታቸው መግባት ምርጫቸው ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ከአድካሚ የሥራ ቀን በኋላ ወደቤታቸው ከመግባታቸው በፊት ከጓደኞቻቸው ፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ራሳቸውን ዘና አድርገው ወደ ቤታቸው ይገባሉ፡፡
የጨርቆስ ሰፈር የተለያዩ የባህል አልባሳት በብዛት የሚገኝበት ነው፡፡ ታዲያ ማንኛውም የባህል አልባሳት ለማሰራት የፈለጉ ሰዎች ወደዚህ ስፍራ በመሄድ በወደዱት አማራጭ ማሰራት ይችላሉ። አካባቢው የሥራ ቦታ እንደመሆኑ እዚህም እዚያም የሚንቀሳቀሰው ወደ ገበያ ማዕከል የሚገቡ እና የሚወጡ ሰዎች ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ ሥራ የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲሁ ገበያውን ተከትለው የሚፈጠሩ አገልግሎት ሰጪዎች በቦታው ይገኛሉ፡፡
ታደሰ አድነው ባህል አልባሳት የማዘጋጀት ሥራ ከገባ አብረው ካሉ ጓደኞቹ ቀዳሚው ነው፡፡ በዚህ ሥራ ብዙ ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን፤ በጨርቆስ የገበያ ማዕከል ይታወቃል፡፡ የራሱን ቤተሰብ መስርቶ የሚኖር ሲሆን የሁለት ልጆች አባትም ጭምር ነው። ውበቱ በቀለ የታደሰ አድነው የሥራ ባልደረባ ሲሆን፤ የተለያዩ የሽመና ውጤት የሆኑ ልብሶችን በትእዛዝ የሚሰራ ሲሆን፤ በጨርቆስ የገበያ ማዕከል እንደ ታደሰ ያሉ ሌሎች ደንበኛ ነጋዴዎች አሉት፡፡
ሰውነት ታመነ እና ተሰማ ሳሬ በዚህ ሥራ ውስጥ ከአምስት ዓመት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ የራሳቸው የሆነ የተለያዩ የባህል አልባሳትን የሚሰሩት የራሳቸው የንግድ ሱቅ አላቸው፡፡ በስራቸው በገንዘብም ሆነ ብዙ ትእዛዝ ያላቸው እንደሆነ እርስ በእርስ መተጋገዝ በጓደኛሞቹ መካከልም ሆነ በገበያው ማዕከል የተለመደ ተግባር ነው።
እነዚህ የሥራ ባልደረቦች ውሏቸው በጋራ ነው። የታዘዟቸውን የደንበኞቻቸውን ልብሶች ለማድረስ እንደ የሥራቸው አብረው ውለው አብረው ያመሻሉ። ይህ ነው የሚባል የሥራ ሰዓት የሌላቸው ሲሆን፤ አንዳንዴም አምሽተው በሥራ ሊያሳልፉ ይችላሉ። ታዲያ ከሥራ በኋላ ያላቸውን ጊዜ ወደ ቤታቸው ከመግባታቸው በፊት አብረው የማምሸት ልማድ አላቸው፡፡
ከሥራ በኋላ
ልክ እንደ ሁልጊዜው በሥራ ያለፈ ቀን ነበር። ሥራቸውን በእለቱ ደንበኞቻቸውን በመቀበል ፣ የተቀበሏቸውን ትእዛዞች በመሥራት ፣ ሠርተው የጨረሱትን ደግሞ በማስረከብ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።
በዛሬው ቀን የነበሯቸውን ሥራዎች አምሽተው ነበር ያጠናቀቁት፤ ሥራቸውን እንዳጠናቀቁ ሁልጊዜ ወደሚያመሹበት 6ኪሎ አካባቢ የሚገኝ ሰላም ስጋ ቤት እና ግሮሰሪ ያቀናሉ፡፡ በረከት በዚህ ግሮሰሪ ውስጥ ምሽቱን ያሳልፋል፡፡ በሌላ የስራ ዘርፍ ላይ የተሰማራው በረከት ከታደሰ እና ጓደኞቹ ጋር ይተዋወቃል፡፡ የሚያመሹበት ቦታ እና ጊዜ ተመሳሳይ በመሆኑ በዓይንም ቢሆን ትውውቅ ይኖራቸዋል፡፡ ታሪኩ እንግዳሰው በድለላ ሥራ ላይ የተሰማራ ነው። ታዲያ በዚህ የድለላ ሥራው ከበርካታ ሰዎች ጋር የመተዋወቅ እድል አለው፡፡ በሥራው ባህሪ ምክንያት ይህ የሥራ ሰዓቴ ነው፤ ይህ ከሥራ ውጪ የምሆንበት ሰዓት ነው የሚለው ሰዓት የለውም፡፡ ታዲያ በየትኛው አካባቢ ለሥራ ቆይቶ ማምሻውን ግን በዚህ ግሮሰሪ ያደርጋል፡፡
በመሆኑም በግሮሰሪው በየእለቱ ተጠቃሚ በመሆኑ በዓይን የሚያውቃቸው ሰዎች የድለላ ሥራ ተግባቢነቱን በመጠቀም ሊግባባቸው ችሏል፡፡ ነገር ግን ታሪኩ በባህሪው ይህ ነው የሚባል የቅርብ ጓደኛ የለውም፡፡ ከሁሉም ሰው ጋር ተግባቦት ያለው ሲሆን በቃሉ የማይገኝ በመሆኑም በከፊልም እሱ ላይ ቅሬታ ላይ ያላቸው ሰዎች በዙሪያው አሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ችግር ለመፍታት የሚጠቀመው መንገድ ሌላ ቃል መግባት ነበር፡፡
እላፊ ሰዓት
ሰኔ 17ቀን 2015 ዓ.ም ተሰማ ሳሬ ፣ ታደሰ አድነው ፣ ውበቱ በቀለ እና ሰውነት ታመነ ሁልጊዜ ከሚሠሩበት የጨርቆስ የገበያ ማዕከል ወጥተው ወደ ቤት ከማምራታቸው በፊት ወደ ሰላም ስጋ ቤት እና ግሮሰሪ አመሩ፡፡ በረከት ረጅም የሆነ ጊዜውን በዚህ ግሮሰሪ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ከታሪኩ ጋር የማምሸት ልምድ አለው፡፡ እንደ ወትሮውም ቀድሞ በመገኘት እየጠበቀው ነው፡፡ በመሀልም በግሮሰሪው ካሉ ሰዎች ጋር አንዳንድ ጨዋታዎችን እየተቀባበሉ ያደርጋሉ፡፡ ተሰማ እና ጓደኞቹ የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ በረከት ሁልጊዜ የጨዋታ መነሻ ነው፡፡ ይህ ቀልድ አዘል ትችት ሁሌም ቢሆን ተሰማን ምቾት የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
ታዲያ ሰዓቱ ከምሽቱ ወደ አራት ሰዓት ሆኗል፡፡ ታሪኩ በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን ስራዎች ከደንበኞቹ ጋር የማሳመን ሥራ ሰርቶ ወደሁልጊዜው መዝናኛ እና የውሎ ማሳረጊያው ግሮሰሪ ይመጣል፡፡ ልክ ከውጭ ሲገባም ከመግቢያው አንስቶ ያሉ ተጠቃሚዎችን ሰላም እያለ ጓደኛውን በረከትን በመፈለግ ላይ ነው፡፡
ታሪኩ አንድ በመርካቶ የሚገኝን ሱቅ እንዲከራየው በጨርቆስ የገቢ ማዕከል የሚሰራው ተሰማ ጠይቆት ነበር። ነገር ግን የድለላ ሥራው በእጁ ያለውን በፍጥነት ለሚስማማ ደንበኛ መሸጥ ነውና ለሌላ ቦታ ፈላጊ በመስጠቱ ተሰማ እና ታሪኩ በመሀከላቸው ያለው ግንኙነት ሻክሯል፡፡
ታዲያ የታሪኩን መምጣት የተመለከተው ተሰማ “እንዴት አመሸህ አንተ ቀጣፊ ደላላ” በሚል ትችት ያዘለ ሰላምታ አቀረበለት፡፡ ታሪኩ ይህንን ትችት ከብዙዎች የለመደው በመሆኑ መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ ባይሆንም ደላላ ነውና ለሚያሰላስል ሰው ጊዜ መስጠት ባህሪው አለመሆኑን በቀልድ መልክ በመናገር ጓደኛው በረከት ወደ ተቀመጠበት ጠረጴዛ አመራ፡፡
በረከት ተሰማ እና ጓደኞቹ የሚሰሩትን የአልባሳት ሥራ በመናቅ ለጓደኛው ተደርቦ የሰጠው መልስ ለተሰማ እንዲሁ የሚታለፍ ባለመሆኑ ከቦታው በመነሳት እጅ ለእጅ ተያያዙ፡፡ በዚህ መሀል የተፈጠረው የቃላት ልውውጥ ይጠቀሙት የነበረው መጠጥ ጋር ተደማምሮ በመሀከላቸው ግጭት ተፈጠረ፡፡
በቦታው ለነበሩ ሰዎች ከቁጥጥር ውጪ የሆነው ግጭት ከበረከት እና ተሰማ አልፎ ሊገላግል የገባውን ታሪኩ ጋር ሆነ፤ ግሮሰሪው ድብልቅልቅ ባለ ጩኸት ተሞላ፡፡ የግል ቁርሾ ይመስል የነበረው ጸብም ወደ ቡድን ተሻግሮ አራቱ ጓደኛማቾች እና በረከት እና ታሪኩ እርስ በእርሳቸው ጥል ጀመሩ፡፡
በሰዓቱም መጠጥ ይጠጡበት በነበረው የቢራ ጠርሙስ በመወርወር የታሪኩ የተለያዩ ክፍሎች ላይ ጉዳት አደረሱበት፡፡ በግሮሰሪው ውስጥ ለሎሚ መቁረጫነት የሚያገለግለውን ቢላ ከባንኮኒው ላይ በመውሰድ ታሪኩ ላይ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ በመውጋት ጉዳት አደረሱበት፡፡ በጉዳቱ አራቱ ጓደኛማቾች መጠነኛ ጉዳት ሲደርስባቸው በድለላ ሥራ የተሰማራው ታሪኩ እንግዳሰው በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ቢያመራም ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
የወንጀሉ ዝርዝር
ወንጀሉ በተፈጸመበት እለት ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ጉዳዩ በተፈጸመበት በሰኔ ወር በቀን 17/2015 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ አራት ሰዓት ሰላም ስጋ ቤት እና ግሮሰሪ አንደኛ ምስክር በረከት ግሮሰሪ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የሟች ታሪኩ እንግዳ ሰው ህይወት መጥፋት ጥፋተኛ ናቸው ያላቸውን ተጠርጣሪዎችን እና በቦታው የነበሩ ምስክሮችን በመያዝ ወንጀሉን ማጣራት ጀመረ፡፡
አንደኛ ተከሳሽ በመሆን የቀረበው ተሰማ ሳሬ ለምን ሱቁን ለእኔ አላከራየኸኝም በሚል ሟች ታሪኩ ጋር በፈጠረው ጸብ ሟች እና ተከሳሽ ሲያያዙ ከ2ተኛ ተከሳሽ ጋር አብረው በግሪሰሪ ውስጥ ይጠጡ የነበሩ 1ኛ እና 3ተኛ ተከሳሽ እና 4ተኛ ተከሳሽ ጠረጴዛቸው ላይ ባለ የቢራ ጠርሙስ ፣ ብርጭቆ በመርወር ሟችን በመምታት፤ 4ተኛ እና 5ተኛ የዐ/ሕግ ምስክሮች 1ኛ ተከሳሽ በግሮሰሪው ውስጥ ለሎሚ መቁረጫነት አገልግሎት ላይ ይውል የነበረውን ቢላ የግሮሰሪው ባንኮኒ ውስጥ ዘሎ በመግባት በመውሰዱ ደጋግሞ በስለት በመውጋት ህይወቱን በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ ታስቦ የሚፈጸም ከባድ ግድያ ወንጀል በመፈጸም ተከሷል፡፡
በስለት የቀኝ ደረቱን ፣ በስተጀርባ ፣ የቀኝ ሆዱን ፣ በግራ በኩል አንገቱን እንዲሁም የግራ ጭኑን በመውጋት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረጉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የአምባጓሮ ወንጀል ተከሰዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 (1) (ሀ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ክስ ተመስርቷል፡፡
ዐቃቤ ሕግ በወንጀሉ ላይ አራተኛ ተጠርጣሪ ያደረገው ታደሰ አድነው ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ወደ አርባምንጭ ጋሞ ዞን ከተማ ለአንድ ወር ያክል ተሰውሯል፡፡ በጋሞ ዞን መሰወሩ መረጃው የደረሰው ፖሊስ ጋሞ ጎፋ ዞን ዛራ ወረዳ ገና ኬራ ቀበሌ ወሌ ቆሬ ጎጥ ተሰውሮ የሚገኘውን ተጠርጣሪ ከዞኑ ፖሊስ መምሪያ ጋር ባደረገው ግንኙነት ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡
ማስረጃዎች
ዐቃቤ ሕግ በመሠረተው የክስ ወንጀል ያስረዱልኛል ያላቸውን ሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች አጠናክሮ አቅርቧል፡፡
በሰው ማስረጃዎች ወንጀሉን የፈጸሙት ተከሳሾችን ይለዩልኛል ያላቸውን በቦታው የነበሩ ሰዎች በመሰብሰብ ወንጀለኞችን የመለየት እና የማረጋገጥ 11 የሰው ማስረጃዎችን ተጠቅሟል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ባሰናዳው የሰነድ ማስረጃ ሟች የመጀመሪያ ሕክምና ካደረገበት የካቲት 12 ሆስፒታል የሕክምና ማስረጃ ከነትርጉሙ የሞት የምስክር ወረቀት ማረጋገጫ ፣ የሟች ማንነት ጉዳት የደረሰበትን የሟች የሰውነት ክፍል ፣ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ቦታ ለማሳየት የተነሱ 31 የፎቶግራፍ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ እንዲሁም 11 ምስክሮች ተከሳሾችን ሲመርጡ ለማሳየት የተነሳ 54 ፎቶ ቀርቧል፡፡
እንዲሁም የሟች አስክሬን ምርመራ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የተላከ የአስክሬን ምርመራ በውጫዊ እና ውስጣዊ ክፍል ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን አስቀምጧል፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በላከው እና ዐቃቤ ሕግ ካስቀመጠው ትርጉም ጋር ውጫዊ አካል ሟች ጉዳት በደረሰበት የሰውነት ክፍሉ ላይ የደረሰበት መጠን የሞቱ መንስኤ ከደረት ጀርባ በስለት በደረሰበት የጉዳት መጠን መሆኑን አብራርቶ ለፍርድ ቤቱ ልኳል ፡፡
ውሳኔ
በዚህ የክስ መዝገብ አራት ተከሳሾችን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ህዳር 4 ቀን 2017ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ክስና ማስረጃዎችን ከሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ አንደኛ ተከሳሽ ተሰማ ሳሬ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ውበቱ በቀለ በ10 ዓመት በፅኑ እስራት ፣ ሶስተኛ ተከሳሽ ሰውነት ታመነ በ10 ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት የቀጡ ሲሆን፤ አራተኛ ተከሳሽ ታደሰ አድነው ተከራክሮ ባቀረበው መረጃ በነጻ ይሰናበት በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም