በኦሮሚያ ክልል ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል የአቮካዶ ምርት ተሰበሰበ

– 165 ሺህ 321 አርሶ አደሮች በአቮካዶ ልማት ተሠማርተዋል

አዲስ አበባ፡– በ2017 የምርት ዘመን ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እስካሁን ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል የአቮካዶ ምርት መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ። በክልሉ 165 ሺህ 321 አርሶ አደሮች በአቮካዶ ልማት መሠማራታቸው ተጠቁሟል፡፡

በቢሮው የፍራፍሬ ልማት ዳይሬክተር አቶ ተገኝ ኢራና ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በክልሉ የአቮካዶ ማሳ ሽፋን 55 ሺህ 112 ሄክታር መሬት የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 30 ሺህ 145 ሄክታር የሚሆነው መሬት ላይ የተተከለው የአቮካዶ ዛፍ ምርት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ አምስት ኩንታል የአቮካዶ ምርት ማግኘት መቻሉን አውስተው፤ በዘንድሮው የምርት ዘመን ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁንም ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል የአቮካዶ ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በ21 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 185 ወረዳዎች በአንድ ሺህ 751 ክላስተር በማደራጀት አቮካዶ መተከሉን  የገለጹት አቶ ተገኝ፤ 165 ሺህ 321 ወንድና ሴት አርሶ አደሮች በአቮካዶ ማልማት ሥራ ተሠማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ተጠቃሚ እየሆኑ እንደመጡ ጠቁመዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮው ዓመት ወደ ጎረቤት ሀገራት እና መካከለኛው ምስራቅ የአቫካዶ ምርትን መላክ ተችሏል፡፡ ወደ አውሮፓ አንድ ሺህ ኩንታል የአቮካዶ ምርት ለመላክ ታቅዶ ከዚህም መካከል 610 ኩንታል ምርት ኤክስፖርት ተደርጓል።

ወደ ጎረቤት ሀገራት እና መካከለኛው ምስራቅ የሚላኩ የአቮካዶ ምርቶችን ጨምሮ እንደአጠቃላይ በክልሉ 12 ሺህ ኩንታል የአቮካዶ ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል ፡፡

ከባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ 20 ሚሊዮን የአቮካዶ ችግኝ ለማዘጋጀት ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እስከ ታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም ድረስ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ ማዘጋጀት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የአቮካዶ ምርታማነትን ለማሳደግ፤ አዳዲስ የአቦካዶ ዝርያዎችን ለማልማት የግብዓት ችግር ማጋጠሙን አመልክተው፤ ችግሩን ለመቅረፍ በክልሉ በሚገኙ 270 ችግኝ ጣቢያዎች በሽታን የሚቋቋሙ፣ ምርታማ እና ገበያ መር የሆኑ ዝርያዎች የማባዛት እና የአቅርቦት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአቫካዶ ልማት በስፋት ማልማት አዲስ እንደመሆኑም የልማት ሠራተኛው ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሠራቱን ገልጸው፤ አርሶ አደሮች ከ50 በላይ የአቮካዶ ችግኝ በክላስተር እንዲተክሉ እየተደረገ ነው፡፡ ምርቱ ቶሎ የሚበላሽ እንደመሆኑም አርሶ አደሮችና ላኪዎች በምን አይነት መልኩ ማስቀመጥና መላክ እንዳለባቸው ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አሁንም ክፍተቱ ሙሉ በሙሉ ስላልተቀረፈ ቀጣይ ሥራዎች እንደሚጠበቁ ጠቁመዋል፡፡

በገበያ ትስስር ረገድም አርሶ አደሮች ምርቱን ካመረቱ በኋላ ገበያ የማፈላለግ ሥራ እንደሚሠሩ አንስተው፤ ይህን ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት ዳይሬክተሩ፡፡

አርሶ አደሮች እና የአቮካዶ አልሚዎች የአቮካዶ ችግኝ ከተከሉ በኋላ በእንስሳት እንዳይበላ እንዲጠብቁ እና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 11 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You