ሀገራዊ ምክክሩ በሴቶች ዕይታ

ዜና ሐተታ

ወይዘሮ ኡርጂ አሊ ከመልካ አዳማ ወረዳ ሴቶችን በመወከል በኦሮሚያ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ተሳታፊ እናት ናቸው። ሠላም ከሌለ በዋነኝነት የሚጎዱት ሴቶች እና ልጆች ናቸው ይላሉ።

እንደ ሴት እና እናትም ሁሉም ሰው በሠላም ወጥቶ የሚገባባት ሃገር እመኛለሁ የሚሉት ወይዘሮ ኡርጂ ፤ ኢትዮጵያውያን ከቤታችን ጀምሮ ችግሮች ሲፈጠሩ በመመካከር የመፍታት መልካም ልምድ ስላለን አሁንም በሃገራዊ ምክክሩ ተወያይተን ችግሮችን መፍታት እንችላለን ሲሉ ይገልጻሉ።

እናት በኦሮሞ ባሕል ትልቅ ክብር እና ተሰሚነት አላት የሚሉት ወይዘሮ ኡርጂ፤ ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ ይናገራሉ።

ወይዘሮ አበራሽ ቁምቢ ደግሞ የመጣችው ከኦሮሚያ ክልል ወንጂ ወረዳ ሴቶችን በመወከል ነው። ሴቶች በሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለባቸው የምትናገረው ወይዘሮ አበራሽ፤ ሴቶች አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ሠላም ሲደፈርስ ዋነኛ ተጎጂዎች በመሆናቸው ጭምር እንደሆነም ትናገራለች።

ሴቶች በአካባቢያቸውም ችግሮች ተፈጥረው በውይይት ሲፈቱ ልጆቻቸውን እና የትዳር አጋሮቻቸውን በመምከር እና በማረጋጋት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ የምትለው ወይዘሮ አበራሽ፤ በሀገራዊ ምክክሩም በግልጽ ከመወያየት ጀምሮ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብላለች።

ከምዕራብ ሐረርጌ ሴቶችን በመወከል የመጣችው ሌላኛዋ የኦሮሚያ አጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ተሳታፊ ደግሞ ወይዘሮ የትናየት ፀጋዬ ነች። ወይዘሮ የትናየት እንደምትለው ሴቶች ግጭት ሲፈጠር ገፈት ቀማሾች ናቸው።

ሴቶች ሠላምን አብዝተው የሚፈልጉት ግጭት በሴቶች ላይ በርካታ ችግሮችን ይዞ የሚመጣ በመሆኑ እንደሆነ የምትናገረው ወይዘሮ የትናየት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሠላምን የሚያመጣ በመሆኑ በተለይ ለሴቶች እፎይታን የሚሰጥ ነው ትላለች።

እንደ ሀገር የመጣንበት መንገድ ጥሩ አልነበረም የምትለው ወይዘሮ የትናየት፤ ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ሃገር ለግጭት እየዳረጉን ያሉ ችግሮች ላይ ተወያይተን ለመግባባት ትልቅ ዕድል ነው ትላለች።

ሠላም ለመፍጠር በሚደረገው ሃገራዊ ምክክር ሴቶችን በመወከል መገኘቴ ትልቅ ዕድል ነው የምትለው ወይዘሮ የትናየት፤ በምክክሩ ንቁ ተሳታፊ በመሆን እንዲሁም ሌሎችን በማድመጥ እርቅና ሠላም ለመፍጠር ተዘጋጅቼያለሁ ትላለች። በየአካባቢው ያሉ ሴቶችም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለባቸውም ትመክራለች።

ሴቶች ሰፊ የማኅበረሰብ ክፍሎች በመሆናቸው በሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ድርሻ አላቸው የምትለው ወይዘሮ የትናየት፤ የመፍትሔ አካል በመሆን የበኩላቸውን መወጣት አለባቸውም ትላለች።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ብዙ ሰዎችን ለከፋ ችግር እና እንግልት ዳርገዋል። በግጭቶቹ በሚፈጠሩ ችግሮች ዋነኛ ገፈት ቀማሾቹ ደግሞ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው።

ሴት እናቶች ግጭት ሲኖር ሳይፈልጉ ብቻቸውን ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት ይሸከማሉ። ግጭቶች በአካባቢያቸው ሲፈጠርም ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው መሸሽ ለነሱ ቀላል አይደለም። ለዚህ ነው ሴቶች አብዝተው ሠላምን የሚናፍቁት ነው ያሉት።

ችግሮች ሲፈጠሩ ተወያይቶ መፍታት በየአካባቢው ያለ ኢትዮጵያዊ ባሕል ነው። እንደ ሀገርም መመካከር ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያመጣ ታምኖበት ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ከጀመረ 3 ዓመት ሊሞላው ነው። በዚህ ሂደትም የተወሰኑ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ውጤታማ መሆኑን ኮሚሽኑ ይገልጻል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You