
ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሀገራችን ከተሞችና መንደሮች የቆሻሻ ሁነኛ ምንጭ የነበረውን በተለምዶ ፌስታል የምንለውን የፕላስቲክ ከረጢት የሚያግድ ረቂቅ አዋጅ ቀርቦ ነበር። በረቂቅ አዋጁ መሠረት የፕላስቲክ ከረጢት የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከአምስት እስከ አስር ሺህ ብር ይቀጣል።
በተመሳሳይ የፌስታል አምራቾችና አስመጪዎች ማምረትና ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ መሸጥ ወይም ለንግድ ዓላማ ማከማቸት ከ50-100 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣና በተጨማሪም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እንደሚያስቀጣ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። እነዚህን ‹‹የወንጀል ድርጊቶች›› የፈጸመው ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ ሦስት እጥፍ እንደሚሆን ረቂቁ ያትታል።
ረቂቅ አዋጁ በፕላስቲክና ፌስታል ምክንያት ለዛቸውንና መዓዛቸውን ያጡትን እንደ አዲስ አበባ የመሳሰሉ ከተሞችን የሚታደግ በመሆኑ የሚኖረው ፋይዳ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ለከተሞችና ለገጠሪቱ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጥበቃ ወሳኝ የሆነ ከራስ በላይ ንፋስ የሆነ ረቂቅ አዋጅ ነው።
ረቂቅ አዋጁን ስናየው ከወዲሁ አፋችንን ሞልተን ፕላስቲክ ከረጢት ስቅላት (ይሸጥ ሳይሆን ይሙት) ታወጀበት ብለን ሐሴት የምናደርግበት ነው። እንደ አዲስ አበባ የመሳሰሉ ከተሞች አነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ፣ ጫት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የተለያየ ቁሳቁስ፣ ልብስ፣ እህል ምግብ ወዘተ ሲሸምቱ የሚገዙትን ዕቃ የሚይዙት በፌስታል ነው።
ቀድሞ ይሄ እኩይ ፌስታል ሳይመጣ ጫት በኮባ (እንሰት) ቅጠል ተጠቅልሎ ይሸጥ እንደነበር አስታውሳለሁ። አሁን ግን ጫት የሚሸጡ ነጋዴዎች ፌስታልን ይጠቀማሉ። ጫትን እንደለመለመ ማቆያ (ከፈለጋችሁ ማቀዝቀዣ በሉት) የጫት ዕድሜ ማራዘሚያ እንበለው ይሆን? ለሚቅሙ እንደመስታወት በጠሩ ላስቲኮች እያሳዩ ማማለያ፣ ገበያ መሳቢያ ጭምር ነው።
ፌስታልና የመሳሰሉ ነገሮች ክፋታቸው ከአገልግሎት በኋላ የሕዝብና የሀገር ችግርና ቆሻሻ ሆነው መቅረታቸው ነው። በመቶ ዓመት ዕድሜ አይበሰብሱም። ለመሬት መከላት ምክንያት ይሆናሉ። በተለይ በገጠር አካባቢዎች ፌስታል ከተጣሉ ለእርሻው ተግዳሮት ይሆናሉ ።
ፌስታሎቹ በወደቁበት አካባቢ የሚገኙ ሣሮች ቅጠላ ቅጠሎች እንዳያድጉና እንዳይለመልሙ፤ እህል ሲዘራም ፌስታሎች ላይ ከወደቁ አፈርና ውሃ ስለማያገኙ በቀላሉ ይመክናሉ፣ ይባክናሉ። አልያም የተዘራው ዘር ሁሉ የአዕዋፋት ሲሳይ ይሆናል።
ቀደም ሲል በከተሞቻችን ፌስታል የሚባል ነገር አይታወቅም ነበር። ሰው ዕቃውን ገዝቶ በካኪ/ኪስ ወረቀት ተሰጥቶት ይሔዳል። ከልኳንዳ ሥጋ መግዛት ቢያሻችሁ ኪሎውን ነግራችሁ ተመዝኖላችሁ በጋዜጣ ተጠቅልሎ ይሰጣችሁ ነበር። አልያም በካኪ ወረቀት ነገር።
መርካቶ ዱባይ ተራና ሚሊታሪ ተራ ጨርቃ ጨርቅ ብትገበዩ፤ ሸራ ተራም ሆነ አመዴ ገበያ ጫማ ብትገዙ በጋዜጣ ተጠቅልሎላችሁ አልያም የባንክ ሳጥን በሚመስል ጠንከር ያለ ካርቶን ጫማችሁ ይደረግላችሁና ይዛችሁ ትሄዳላችሁ።
በወቅቱ ጋዜጦችን አብዛኛው ነጋዴ እየገዛው ዜናውንና መረጃውን ካነበበ በኋላ የሚሸጠውን ቁሳቁስ የሚሰጠው በጋዜጣው እየጠቀለለ ነበር። ነጋዴዎቹ ከጋዜጦች መረጃና ዕውቀት እየገበዩ ገበያተኞቻቸውንም ሲያስተናግዱ ዕቃውን በጋዜጣ ሸክፈው ሲሸጡ አስታውሳለሁ።
እናቶች ለሳምንት በሉት ለወር የሚሆን አስቤዛ ሲገዙ ከሰሌን የተሠራ ዘንቢል አልያም በስስ ጨርቅ የተሠራች አነስተኛ ዕቃዎች የምትይዝ የኪስ ጨርቅ ነገር ሲጠቀሙ ነበር ።
በጋዜጣችን በመጋቢት 2015 የወጣ ፌስታል ይታገድ፤ ይወገድ! የሚል ዘገባ ወጥቶ ነበር። ጽሑፉ ወደ ገጠር ከተሞች የሚያደርሱ ዋና ዋና የአስፋልት መንገዶች ዳርቻ በፕላስቲክ ‹ጠርሙሶች› እና በፌስታል እየተሞላ ነው። ይህ ደግሞ ግብርናውን የሚጎዳ ነው።
ከብቶችም ‹በቴክኒክ ብልሽት› ፌስታል የሚበሉ በትና የሚጎዱበት አጋጣሚ አለ። ማስወገዱን ትተነው የፌስታል ግብይት እንዲወገድ ግብርና ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴሮች አካባቢ ጥበቃና አቻ የክልል ቢሮዎች ሌሎችም ይንቀሳቀሱ ብሎ ነበር።
ጽሑፉ ከወጣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ፕላስቲክ ‹ጠርሙሶች› ከተጣሉበት ሰዎች እየሰበሰቡ መሸጥ ጀመሩ። የውሃ ፋብሪካዎቹም ፕላስቲክ ‹ጠርሙሶች›ን በዳግም ዑደት (ሪሳይክል) እያመረቱ ይጠቀሙ ጀመር። ይህ ሁለት ጠቀሜታ አለው። አንደኛ ሥራ አጦች በየመንገዱ ፕላስቲክ ‹ጠርሙሶች› በከረጢት ለቃቅመው እየሸጡ ገንዘብ ያገኛሉ። ከተማውም ፅድና ውብ ይሆናል።
እንደ ጎጃም በረንዳ ያሉ አካባቢዎች በሃላይላንድ ሽንታቸውን ሸንተው ከድነው አስፋልት እየጣሉ፤ መኪናዎች እየበረሩ መጥተው ሲረግጡት እየፈነዳ እግረኞች ላይ መስኮታቸውን ክፍት ባደረጉ መኪና ተሳፋሪዎች ላይ ጭምር ሲረጭ በተደጋጋሚ አይቻለሁ። ቢያንስ ፕላስቲክ ‹ጠርሙስ› መሸጥ ሲጀምር ይሄ ነገር ቀረ።
የወንዞች ዳርቻዎች ልማት፣ የኮሪደሩን ልማት ከፌስታልና ፕላስቲክ ‹ጠርሙሶች› ጋር ብናየው ደግሞ ረቂቅ አዋጁ ሁነኛ ሚና እንዳለው ያሳያል። የወንዝ ዳርቻዎች እና የኮሪደር ልማት ውበት እንዲጠበቅም ይረዳል። በክረምት ወቅት ወንዞቻችን ብናያቸው ሞልተው የፕላስቲክ ከረጢት በብዛት ስለሚታይ የዘነበው ራሱ የፕላስቲክ ከረጢት ቢመስላችሁ እንዳትገረሙ።
በአስፋልት ዳርቻ ያሉ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ፌስታልና የፕላስቲክ ከረጢት ስለሚጣልባቸው እየተደፈኑ ፍሳሻቸው አስፋልቱ ላይ ሲሞሉት ይታያል። ከረቂቅ አዋጁ የጠቀስናቸው ችግሮች የሚያግድ ነው። ‹‹የበከለን ማስከፈል››፣ ቆሻሻን ከምንጩ መቀነስ፣ መልሶ መጠቀም፣ መልሶ ዑደት ማድረግ እና በአግባቡ ማስወገድ፤ እና የኅብረተሰብ ተሳትፎ ማሳደግም ከጠቀሜታዎች መካከል ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራን በገመገሙበት ወቅት የፕላስቲክ ችግር ጠቅሰው ነበር። በወቅቱ የፌዴራል መንግሥት ፕላስቲክን በተመለከተ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፕላስቲኮች ‹‹ወደ ሀገር ውስጥ የማይገቡበትን መንገድ ለመፍጠር እንሞክራለን›› ብለው ነበር።
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ላይ የሚሠሩ የፕላስቲክ ቤቶች እና የፕላስቲክ በረንዳዎች መከልከል እንዳለባቸው ገልጸውም ነበር። ‹‹ማንም ሰው በቤቱ በረንዳ ላይም ይሁን ቡና ለመሸጥ በፕላስቲክ የሚሠራ ቤት ሕገ ወጥ መሆን አለበት። መጀመሪያ ላስቲክ ነው፣ ቀጥሎ ነው ሕጋዊ ቤት የሚመስለው። ግን ፕላስቲክ የሚባል መፈቀድ የለበትም›› ሲሉ አሳስበው ነበር።
በኢትዮጵያ ዓመታዊ የፕላስቲክ አጠቃቀም በነፍስ ወከፍ በ2007 ከነበረበት 700 ግራም በ2022 ወደ 3 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም የተመነጠቀበት ይህም በ15 ዓመታት 540 በመቶ ጭማሪ ያሳየበት እንደሆነ Natural Resources Stewardship Programme ከጀርመን በwww.giz.de ድረ ገጽ ያወጣው መረጃ ያሳያል።
በአማካይ በአዲስ አበባ እያንዳንዱ ዜጋ በዓመት 51 ኪሎ ግራም የሚደርስ ፕላስቲክ እንደሚወገድ ይገመታል። ከነዚህ ውስጥ ግማሽ የሚደርሱት ኦርጋኒክ ቆሻሻዎች ናቸው። ፕላስቲክ ከረጢት ይሙት በቃ! ቢፈረድበት ተገቢ እርምጃ ነው ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም