
የአዳኙ ወጥመድ ከመድረኩ ላይ ነው። ጀግናው ተውኔት አዳኝ ቀስቱን ቀስቶ ሰርክ ለአዳን ወደ ተራራው አናት ይወጣል። ቁጭ ብሎ ከታች ከቲያትራዊ የምናብ ጫካ ውስጥ እየማሰነ ልቡ ካረፈው ላይ አጨንቁሮ ዳናውን ሲከተል ይጠጋል። በብዕር አምሳልና ቀለም የሾረውን ቀስቱን ወደ ላይ ከትከሻው ሰያፍ አሰንስኖ ይልከዋል። ልክ ከምናቡ ላይ በነደለው መጠን አነጣጥሮ የደለበውን ያድነዋል።
በገቢር በፈርጁ እየበለተ፣ በቀስት የጣለውን ፍሪዳ በቅስት መድረክ ላይ ያንጠለጥለዋል። ከየአቅጣጫው ለሚጎርፈው የአዳራሹ ታዳሚ የአዳኙ ግብዣ ቢትረፈረፍ እንጂ አንሶት አያውቅም። ብርንዶው ከሰላ ጥበብ ጋር ቀርቦለት አጨብጭቦ ሲያመሰግን ይወጣል እንጂ አጉረምርሞም አያውቅ። አዳኙ ከሀሳባዊ የጥበብ ጫካ ውስጥ ያሻውን በወደደው ልክ ማደን ያውቅበታል። ደግሞ ሲመለከተ ጊዜና ሁኔታ የጣለውን አንስቶ ማዳንም ይችልበታል።
እንዲያው ግን ይሄ ሳተና አዳኝ ማን ይሆን…ብዙዎች ግን እንዲህ ሲሉ ነው የሚጠሩት “ጋሽ አባተ መኩሪያ” የእውነትም ኩራትን የባተ ትክክለኛው ሰው እርሱ ነው። በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ፣ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሁሉ ይህን ስም ልቡ ተነቅሶታል። ምን ሠርቶ ያለፈ ጀግና እንደሆነ ባያውቅ እንኳን እንዲሁ በደመነብስ ምስሉን አግዝፎ ያሳየዋል። ማንም ለስሙ እንግዳ አይሆንም። ራሱን ኩራትን ያኮራ የጥበብ መንኮራኩር ነው። አዳኝ ብቻም ሳይሆን ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል፣ ከ50 ላላነሱ ዓመታት የጥበብን ዘር፤ ተውኔትን ሰብስቦ ሲዘራና ሲያጭድ፣ ሲወቃና ሲሰበስብ የኖረ ገብሬም ጭምር ነው። ዘርቶ ያገኘውና ሰብስቦ የሰጠው ሁሉ በወቄት የማይመዝኑት ወርቅ፣ በፈረሱላ የማይመጥኑት ዛላ፣ በቁና ሰፍረው፣ በሚዛን የማያኖሩት ልኬት አልባ ጥበብ…ወደር የለሽ አዳኝ ነው።
በሥራ እውን ሆኖ በመልክ የሚታየው መሠረቱ የሚገነባው ሰው ካለፈበት ህይወቱ፣ ቤትም ከምሰሶው ላይ ነው። መጀመሪያ የሌለው መጨረሻም የለም። አባተ ከመባቱ የትና እንዴት ነበር…ከጥበብ ህይወት አሀዱ አስቀድሞ የልጅነት አስኳላን ከፊደል ተራ እስከ ቅኔው ተራራ ወገብ ድረስ፤ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአሁኑ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ተምሯል። አንደኛ ደረጃን ተምሮ ሁለተኛውን ያከተመውም ከዚሁ ነው። በመቀጠልም ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገባ። ለመማር የጀመረውም የእንግሊዝኛ ቋንቋን ነበር። ይህን መምረጡ ኋላ ዙሪያውን ከበው የሚገኙት እንግሊዞች ስለመሆናቸው ታይቶት ይሁን ልቡስጥላው መርቶት የሚያውቀው ራሱ ብቻ ነው።
ነገሩን ማናቸውም ሹክ ይበሉት ብቻ የመጀመሪያውን የጥበብ ህይወቱን እንዲገናኝ መንገድ ዘዋሪ ሆነው የመጡለት እንግሊዛዊ ሰው ነበሩ። አባተ ከዩኒቨርሲቲው ሳይወጣ እንግሊዛዊው ዶክተር ፊሊፕ ወደ ዩኒቨርሲቲው ገቡ። አመጣጣቸውም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በኪነ ጥበባት ዘርፍ እንዲሠሩና እንዲመሩት ውል ገብተውና በፊርማ ተሳስረው ነበር። ዶክተር ፊሊፕ ሥራውን ሲጀምሩ “ኪነ ጥበብ ወ ቲያትር” የተሰኘ አንድ ክፍል አቋቋሙ። ወደ ክፍሉ ቀድሞ ለመግባት አባተን የቀደመ አነበረም። የመጀመሪያው ተማሪዎች ከነበሩትም መካከል አንዱ ነው። ዶክተር ፊሊፕም በዩኒቨርሲቲው ሲያሳልጡት የነበረው የኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነበርና በአባተና በሌሎች ተማሪዎችም ዘንድ ተወዳጅ አደረጋቸው። ኪነ ጥበብ ወ ቲያትርም በጥቂት ጊዜ ውስጥ ማበብ ጀመረ።
በኪነ ጥበብ ዋሻ ውስጥ እያቆራረጡና ጥበብን እያደኑ ከነበሩት መሃል ከፊት አባተ መኩሪያ ነበረበት። ከአዳኙ ጋር ለአዳን የተሰናዱ ሌሎች ተወርዋሪዎችም በኪነ ጥበብ ወ ቲያትር በግራና ቀኝ፣ ከኋላና ፊት ቆመዋል። ዋናዎቹም መንግሥቱ ለማ፣ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን፣ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ እና ዳኛቸው ወርቁም ነበሩ። እኚህ ሁሉ አብረውት ሲያድኑ የነበሩ ናቸው። ከዚህ ተወንጫፊ ጥምረት የሚያመልጥ ምንም አነበረም። በተውኔት፣ በሙዚቃ፣ በስዕል፣ በስነ ጽሁፍና ግጥም የዩኒቨርሲቲውን መውጫ መግቢያ አጠሩት።
በዚህ የተጧጧፈ የጥበብ አውድማ መሃል ነበር፤ በ1954 ዓ.ም አንድ ነውጥ ያስከተለ ለውጥ ዱብ ማለቱ። በጃንሆይ የተሾሙት ደጃዝማች ካሣ ወ/ማርያም የሥልጣን ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ዩኒቨርሲቲው ከች አሉ። ዙሪያ ገባውን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩትም እሳቸው ሆኑ። ነገር ግን ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ነገሩ አልጥም አልዋጥ አለው። ገና ከጅምሩ ውስጥ ውስጡን አጉረምራሚው ብዙ ነበር።
በዚያው የሹመት ሰሞን፣ ከዚያው የማጉረምረም ሰሞናት ላይ “ኪነጥበብ ወ ቲያትር” አንድ የጥበብ ምሽት አሰናዳ። የጥበብ ምሽቱም ባማረ መልኩ ተጀምሮ ዝግጅቱ ደምቋል። በፉጨትና ጭብጨባ አዳራሹን ያጋለው ታዳሚም ሌላኛው ድምቀት ሆኗል። አባተን ጨምሮ ሁሉም በየተራው ሥራዎቻቸውን በግልም በጋራም እየሆኑ ያቀርባሉ። የሚቀጥለውም ተራ የዮሐንስ አድማሱ ነበር። ግጥሙን የጻፈባትን ወረቀት አንጠልጥሎ ወደ መድረኩ ወጣ። ከሚያነባት ግጥም ውስጥም እንዲህ የምትል ስንኝ ተስፈነጠረች፤
“ላም እሳት ወለደች
በሬ ቀንድ አወጣ
በሥልጣን ሊቅ መሆን
ይኸም አለ ለካ” ብሎ እሳት የተለኮሰባቸውን ቃላት አከታትሎ ወደ አዲሱ ፕሬዚዳንት አስወነጨፋቸው። ኢላማውንም ሳይስቱ ቀስቶቹ ከፕሬዚዳንቱ ደጃዝማች ካሣ ጆሮ ተሰካኩ። እሳቸውም ለአጸፋው ሳይዘገዩ በሳምንቱ መልሰው አቀመሷቸው። ዳፋው ለመላው ኪነ ጥበብ ወ ቲያትር ሆነ። ዝግጅቱን ባቀረቡ በቀናት ውስጥ ተዘጋና አረፉት። የዶክተር ፊሊፕ የውል ስምምነት ተቋርጦም እንዲወጣ ሆነ። አባተ መኩሪያም አልቀረለት፤ እሱም ቅንጣቸውን ተብለው ከወጡት አንዱ ሆነ።
ሳይደግስ አይጣላምና አባተ መኩሪያ ከዚያ እንደወጣ ሌላ መግቢያ በር አገኘ። በጊዜው በመቋቋም ላይ በነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አዘጋጅ ሆኖ የመሥራት ዕድል አገኘ። በወቅቱም አብዛኛው የድርጅቱ አካላት እንግሊዛውያን ነበሩ። እናም ለአባተ ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄዶ እንዲማር ተመቻቸለት። የሚዲያ ተግባቦት አጥንቶም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። የቀደመውን ሥራውን በዳበረ መልኩ ቀጥሎ በሀገር ፍቅር ቲያትርም ጭምር በመሥራት ሳለ እንደገና ወደ ጀርመን የማቅናት አጋጣሚ አገኘ። ከዚያም ሲኒማ ቶፖግራፊ ተምሮ ተመለሰ።
ከጀርመን መልስ በትምህርትና ልምድ ያካበተውን ሙያዊ ክህሎቱን ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ፍቅር አዋለው። የኢዩኤል ዮሐንስ “መልክአ ምድር” (ኦ! ዘመቻ) የተሸኘ ቲያትር አዘጋጅቶ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ታየ። ተመልካቹን ቢያስደስትበትም ለርሱ ግን ሁለተኛው ጅራፍ የሚመዘዝበት ሆነ። የቲያትሩ ጭብጥ የሚያጠነጥነው ስለ ዝቅተኛው(ጭሰኛው) የማህበረሰብ ክፍል ነውና ዙፋኑን የሚረብሽ ነበር። በተመዘዘለት የእግድ ጅራፍም በሀገር ፍቅርም ሆነ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራዎቹን እንዳያቀርብ ተደረገ። አንዴ ከሀገሩ፣ ሌላ ጊዜም ከእንግሊዝ እያለ ከተወሰነ ቆይታው በኋላ መልሶ የቀደመ ሥራውን መቀጠሉ ግን አልቀረም፡፡
አባተ በስንቱ ባተ? አባተ ማለት ይህ ነው ብሎ ለመናገርም ቅርጽ አልባ እየሆነ ሲጨብጡትም የሚያሟልጭ ነው። እልፎች እንደሚያውቁለት የተውኔት አዘጋጅ ነው። ሌሎች እንዳጤኑለትም በአዘጋጅነቱ ላይ ጸሀፊ ተውኔትነቱም ይጎመራበታል። ወዲህ ደግሞ ውዝዋዜም ያምርበታል። በጊዜው በርካቶች ያደነቁት የውዝዋዜ(ኬሮግራፊ) አሰልጣኝ ነው። ታዲያ ቲያትርን ሲያዘጋጅ መድረክ ከነ መሶበወርቅና ግጣሙ ነው። ቲያትሩ ከመሶበወርቁ ውስጥ፣ መሶበወርቁም ከመድረኩ ላይ ግጥም ብሎ መጋረጃውን ዳንቴል ሲያለብሱት ገና በሽታው ያስጎመዣል። ቲያትር ብቻም አይደለም፤ ፊልም ሲያዘጋጅም እንዲሁ ነው፡፡
ይሁን እውነታ ለማስረገጥ ከሥራ ፍሬዎቹ በስሱ ለመልቀም ያህል የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ሀሁ በስድስት ወር አንዱ ነው። የሁለቱ ታላቅ ሰዎች ጣምራ ክንድ ለሀገራችን ቲያትር አርማው ምልክቱ ነው። ሁሌም እንደተጣምሩ ነውና ከሠሯቸው ዘመን አይሽሬ ቲያትሮች አንዱ ይሄው የ1966ዓ.ም ዋንጫቸው ነው። አባተ ለዓድዋ ያለው የስሜት ነፀብራቅ የሚጨምር እንጂ የማይደበዝዝ ሆነና እዚያ አካባቢ ከተራራው አናት ላይ ቁጭ ብሎ በጥበብ እንደተቃኘው ነው።
በ1972ዓ.ም ያዘጋጀው “አሉላ አባነጋ” ቲያትር ከእነዚህ መካከል ነው። ከዚያ ቀደም ብሎ በ1971ዓ.ም ደግሞ “አቡጊዳ ቀይሶ” እና “መልእክተ ወዛደር” ከሁለቱ ላይ ሰፍሮ ተጠቦባቸዋል። የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን “አፋጀሽኝ” የተሰኘውን የከረመ ተውኔት ዳግም ወደ መድረክ በማምጣት የባለውለታውን ውለታ አጊጦለታል። “ያላቻ ጋብቻ” በመንግሥቱ ለማ ሲጻፍ በቀሪ የመድረክና ተውኔት ዝግጅቱ አባተ መኩሪያ አለበት። አባተ መኩሪያ ሲታወስ ደግሞ “ቴዎድሮስ” ከነ ጀግንነት ቆንዳላው ፊት ላይ ግጥም ይላል። ሥራው ልብን ይሞላል። ሎሬቱ ጻፈው፣ አባተ ከሽኖ አዘጋጀው፣ ውሕደቱ ለዝንተ ዓለሙ አፈካው፡፡
አባተ ቲያትርን ከማዘጋጀቱ አስቀድሞ ራሱን በጥበብ ሆድ ውስጥ የሚሰውር ሰው ነው። ገና ለማሰብ ሲጀማምር ከዚያ ውስጥ ሆኖ ነው። እንዲህ እንድንለው የሚያስገድደን አንድም እይታው ነው። ራሱ ጽፎ ራሱ ቢያዘጋጀው ሳይሰለች ይወደድለታል። የሌሎችን ለማዘጋጀት ቀና ብሎ ጥቂት አሰብ ካደረገ የትኛው የተውኔት ጽሁፍ ከእርሱ ዘመን ተሻግሮ፣ በቀጣዩም ትውልድ ሰላምታውን ሊያደርስለት እንደሚችል ጠንቅቆ የማወቅ ችሎታ አለው። መርጦ ካዘጋጃቸው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ቢሆኑም ታሽቶ የሚጣል የሌላቸው ናቸው። እርሱም እንቡጥ እንቡጡን ካገኘ የማንንም ለመሥራት ዓይኑን የማያሽ ቢሆንም፤ አብዝቶ ወደ ሎሬቱ ማዘንበሉ ምናልባትም የልቡን የሚያደርስለት እሱ ስለሆነ ነው። ጠብስቆ በገባ ብዕር በግጥማዊና ቅኔያዊ ስብ ስለሚያኮረኩረው፤ የአባተም ምርጫና ጉርሻ ከዚያ ላይ ሆኗል። ተመልካቹም እየጣፈጠው፣ ጠግቦ ሳይሰለች ይደገም የሚለው ያንኑ ነበር፡፡
ተውኔት አዳኙ አባተ መኩሪያ አብዛኛውን ጊዜ ውስጣዊ የስሜት መዳረሻው ከማህበራዊ ቁጥቋጦዎች ስር የሚበቅል ነው። ሀገር፣ ባህል፣ ህዝብ፣ ሞራላዊ ሙርድ ሰብአዊነት ላይ ማጠንጠን ያዘወትራል። ከግማሽ በበለጡ ሥራዎቹ ውስጥ የምንመለከተው መልኩ ይህንኑ መሳይ ነው። ከመሰል ሥራዎቹ መካከልም በ1982ዓ.ም ከመድረክ ላይ የተከለው “የሊስትሮ ኦፔራ” የተሰኘው ሙዚቃዊ ተውኔቱ ዓለም አቀፍ ሽልማትን ተጎናጽፎበታል። ተውኔቱን ራሱ ጽፎ፣ በራሱ አዘጋጅነት ምን ያህል ለመጓዝ እንደሚችል አሳይቶበታል።
መገፍተር ሁልጊዜም መጥፎ አይደለም፤ ከአንደኛው መራቅ ለሌላኛው መቅርብም ይሆናልና። አባተ በእግድ ከሥራ የተገለለበት ሁኔታ ሌላ ላቅ ያለውን ታሪክ እንዲያጽፍ አድርጎታል። ከተቋም ሲባረር የራሱን ተቋም ስለማቋቋም አስቦ በሌላ ጊዜ እውን አደረገው። ድልድይ ቢፈርስ ድልድይ ይሠራል፤ ያለም ይመስላል። ይኸውም ሥራውን ብቻ ሳይሆን ዕውቀትና ልህቀቱንም ለመስጠት በማሰብ በአባቱ ስም “መኩሪያ የጥበብ ማዕከል” (ስቱዲዮና መዝናኛ) ተቋም ከፍቶ እንካችሁ ማለቱ ነው። በርካቶችን በተቋሙ ውስጥ ሰብስቦ ከብዕራዊ ቀስት አያያዝ ጀምሮ በተውኔት ተራራ ላይ ጥበብን ከሙያ ጋር አስታቅፏቸዋል። ሲሰጥ ታዲያ ስስትን አያውቅምና በትወና ጉድባ ላይ አስፍሮ ብቻ አልተዋቸውም። በሙዚቃ አብሮ ሲወዛወዝ ገሚሱንም ተወዛዋዥ አድርጎ ሠርቷቸዋል። በሙዚቃ ዛቢያም የተሽከረከሩ ነበሩ። ስፖርትና ጥበብን አዋዶም በሰርከስ እንዲፈናጠጡ ያደረጋቸው ቀላል አይደሉም፡፡
የጀመረውን የማህበራዊ ህይወት ሽመና ከዚህም ሰፋ አድርጎ ቀጥሎታል። ምሰሶውን ተክሎ ያቆመው ተቋም ውጥኑን ወጥኖ የሀሳብ ምኞቱን ለማድረስ ምቹ ታዛን ፈጥሮለታል። ከስር የተሞረዱትን የጥበብ ልጆቹን ይዞ በመላው ሀገሪቱ ከአብዛኛው ክፍለ ሀገር ወርዷል። ባህር ማዶ እያሻገረም ያሰናዱትን ትርኢት ሰንቀው ከአንዳንድ ሀገራት ሰማይ ላይ ወርደዋል። ከዚህ ሁሉ ጋር በማህበሩ ውስጥ ከተበረከቱ ተውኔቶች “በሐምሌ ጨረቃ”፣ “ሕሊና”፣ “ጠለፋ”፣ “ጆሮ ዳባ” እና “ድንቅ ሴት” የተሰኙት ተጠቃሽ ናቸው። ከተውኔቶች ባሻገር ልዩ ልዩ ዘጋቢ ፊልሞችንም ይገኙበታል። ከእነዚህም “ፍትሕ ፍለጋ” እና “የመስከረም ጥቃት” አብነቶች ናቸው፡፡
አዳኙ የጠራችውን ጥበብ ፍለጋ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ ታንዛኒያም ደርሶ ነበር። ምክንያቱም ከዚያ አንድ የአፍሪካ ቲያትር ተቋም እርሱን ሲጠብቀው ነበርና። ይህን ተቋም ከመሠረቱት አባላት መካከል አንደኛው አባተ መኩሪያ ነበር። የሄደው ግን የተቋሙን የኃላፊነት መንበር ተረክቦ ለመምራት ነበር። እናም በሚገባ መርቶታል። ዓለም አቀፉን የመድረክ አዳኝነት ያገኘው በዚህ ሥራ ብቻ አነበረም። በአንድ ወቅት ወደ ዩኔስኮ ያደረሰውን አጋጣሚ አገኘ። ከእነርሱ በደረሰው ግብዣም አፍሪካዊ ገጽታ ያለውን አንድ ቲያትር እንዲያዘጋጅ ጠየቁት። አባተም ግብዣውን አሜን ብሎ ለዚህ ዝግጅት ይመጥናል የሚለውን ተውኔት ማደኑን ጀመረ። በመጨረሻም ከጸጋዬ ገ/መድህን ግርጌ ላይ “የዋርካው ሥር ንግርት” (ኦዳ ኦውክ ራክል) የተሰኘውን ያዘ። በዚህ ሥራ ከቀረበ በኋላ ነበር ከእንግሊዛዊው የቲያትር አዘጋጅ ፒተር ሆል ጋር ኦቴሎን በጥምረት ለመሥራት የበቃው፡፡
እሳት ለበሱ ጥበብ አዳኝ ስሙ ከፍ ብሎ ከነገሠባቸው ተራሮች አንዱ ዓድዋ ነው። የዓድዋ ድል መታሰቢያ 365 ቀናትን ቆጥሮና ከዓመት ተቃጥሮ በመጣ ቁጥር ሁሉ አባተ ከወዴት ነህ መባል ጀምሮ ነበር። “ዓድዋ አለፈ እንጂ መቼ ታለፈ” የሚያስብል የዝግጅት መንገድ ጀምሮ፤ ዓድዋን ከእርሱ ጥበብ ጋር መመሸግ ያስመኛል። በጊዜው አባተ ከጦር አውድማው ላይ ሆኖ በተመስጦ ሲመለከት የነበረ ይመስላል። ትርኢቱን ለማሳየት መድረክ ብቻ አይበቃውም ነበር፤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሁሉ ዓድዋን ከነቃጭሉ ያመጣዋል። እንኳንስ ለያኔዎቹና ለዛሬዎቹ ለኛም ድርሻችንን አኑሮልናል። እንዴት ካሉ ደግሞ፤ ስለ ዓድዋ በሠራው ፊልሙ።
ኩልል እንዳለ የምንጭ ውሃ፣ ሁሉን ጥርት አድርጎ የሚያሳየው ቴሌቪዥናችን፤ በዓድዋ ሰሞን ነጭ ከጥቁር ብዥ! ጭር! እያደረገ ከሚያሳየን የቅድመ ጦርነቱ ተንቀሳቃሽ ምስል ውስጥ አሻራው የአባተ መኩሪያ ነው። ዘማች በሽለላና ፉከራ ታጅቦ፣ ከዳር በሴቶች የስንቅ አጀብ ተከቦ፣ የአዲስ አበባን ድልድይ ሲሻገር፤ ያንን የዓድዋን ትዕይንት በ4 መቶ ያህል ተዋኞች አሳምሮ ሠርቶታል። አስመስሎታል ሳይሆን ዓድዋን አምጥቶታል ማለቱ ይቀላል።
በስተማሳረጊያውም ከሁሉም የቀደሙ ታሪኮቹ መጨረሻ በር መዝጊያ የሆነውን ሞት በ76 ዓመቱ፤ በ2008ዓ.ም ከፍቶ ገባና አረፈው። ታሪኩ ግን፤ ገና ምኑም አልተነካም፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2017 ዓ.ም