
ይህ ሳምንት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለምዶ ‹‹የታኅሣሥ ግርግር›› እየተባለ የሚጠራው የ1953 ዓ.ም የከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገበት ነው።
የታኅሣሥ ግርግር ከ64 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ በተደረገ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተከሰተ ግርግር ነው። ግርግሩ ለአንድ ሳምንት ያህል ቀጥሏል። ይህን ክስተት በሕይወት ያሉ ሰዎች (ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ) ያስታውሱታል። ብዙ ጸሐፊዎች የጻፉት በዓይናቸው ያዩትን ጭምር ነው። ለምሳሌ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የታኅሣሥ ግርግርን ክስተት በዓይናቸው ያዩትን በመጽሐፋቸው ጽፈዋል። አቶ ብርሃኑ አስረስ ‹‹ማን ይናገር የነበረ›› በሚል የነበሩበትን በመጽሐፍ ጽፈዋል። ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ የአንዲትን አራስ (የወለደች) እናት መገደል አይቷል።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የታኅሣሥ ግርግርን እና ተደብቆ ነበር ይባል የነበረውን የዳግማዊ አጼ ምኒልክን ሕልፈተ ሕይወት እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑ ሌሎች ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የታሪክ አጋጣሚዎችን እናስታውስ።
ከ76 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 1 ቀን 1941 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1948) ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፀድቆ ተፈረመ። ይህ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በእንግሊዘኛ ቃሉ ‹‹Universal Declaration on Human Rights (UDHR)›› የሚባለው ነው። ቀኑ በየዓመቱ ታኅሣሥ 1 ‹‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን›› ተብሎ ተሰይሟል። ይህ ዓለም አቀፍ የሰው ልጅ የዕኩልነት መብት የመሰልጠን ምልክት በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ዓለም አቀፍ ጉዳይ ሆኖ ይታወሳል።
ከ98 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሳሥ 3 ቀን 1919 ዓ.ም በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመነ መንግሥታት ላቅ ያለ ተሰሚነት እና የመሪነት ሚና የነበራቸው (የዳግማዊ አጼ ምኒልክ የቅርብ ሰው የነበሩ) ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) አረፉ፡፡
ከ95 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 3 ቀን 1922 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) ዋነኛው ጠንሳሽና መሐንዲስ የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ደጀኔ ተወለዱ።
ከ21 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 4 ቀን 1996 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ዴሴምበር 13 ቀን 2003) የኢራቅ ፕሬዚዳንት የነበረውና ዓለም አቀፉ አነጋጋሪ ሰው ሳዳም ሁሴን በአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች ተያዘ።
ከ14 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሳሥ 6 ቀን 2003 ዓ.ም ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ካፈራቻቸውና ካየቻቸው ታላላቅ የእግር ኳስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነው፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጫዋችነት እስከ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ድረስ ስኬታማ ታሪኮችን ያስመዘገበው የእግር ኳስ ጥበበኛ መንግሥቱ ወርቁ አረፈ።
በዝርዝር ወደምናየው የታኅሣሥ ግርግር እንሂድ።
በተለምዶ ‹‹የታኅሣሥ ግርግር›› እየተባለ የሚጠራው ይህ የታኅሣሥ የመጀመሪያ ሳምንት ክስተት ከ64 ዓመታት በፊት (1953 ዓ.ም) በወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ የተደረገ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው። ግርግሩም ከታኅሣሥ 4 ቀን ጀምሮ በተከታታይ እስከ ታኅሳስ 8 ቀን ድረስ የቆየ ነበር።
የታሪክ ተመራማሪው አቶ አበባው አያሌው እንደሚሉት፤ መፈንቅለ መንግሥት በባህሪው ጥርት ያለ መረጃ አይኖረውም፤ ምክንያቱም መፈንቅለ መንግሥት የሚደረገው በድብቅ ነው። ስለዚህ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች የጻፉትን እና በተለያየ ወቅት ስለክስተቱ የተናገሩትን መረጃ እንጠቀማለን።
ታኅሣሥ 4 ቀን 1953 ዓ.ም በወንድማማቾች መንግሥቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ የተጠነሰሰው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተጀመረ። በነጋታው ታኅሣሥ 5 ቀን የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ዓላማውን ይፋ አደረገ። አሁንም በነጋታው ታኅሣሥ 6 መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃረነው ወገን (የንጉሱ ታማኝ) ውጊያ ጀመረ። ታኅሣሥ 7 የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ ኃይል እየተዳከመ በአንጻሩ ደግሞ የአክሻፊዎቹ ኃይል እያየለ ሄደ። ታኅሣሥ 8 የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ ኃይል ተደምስሶ፤ ንጉሠ ነገሥቱም ከብራዚል ተመልሰው በአስመራ በኩል አዲስ አበባ ገቡ።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ባይሳካም በፖለቲካው ተቃውሞ ግን ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን አድራጊ ወንድማማቾችም ወታደራዊውን እና ሲቪሉን የሚወክሉ ናቸው። ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ወታደራዊውን ሲወክሉ ገርማሜ ደግሞ ምሁሩን (ሲቪሉን) ይወክላሉ ማለት ነው።
አቶ አበባው አያሌው እንደሚሉት፤ የ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በፖለቲካው ባህል ውስጥ መነቃቃት ፈጥሯል። የፈጣሪ ኃይል ነው ተብሎ ይታመን የነበረውን የንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን ‹‹ለካ መቃወም ይቻላል እንዴ? ለካ እንደማንኛውም ሰው ናቸው እንዴ?›› የሚል አመለካከት እንዲፈጠር አድርጓል።
በወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይና ግርማሜ ንዋይ የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለኢትዮጵያ የተሻለ የአስተዳደር ስርዓት ለማምጣት ታልሞ የተደረገ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል።
በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ 1953 ዓ.ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለጉብኝት ወደ ብራዚል መሄዳቸውን ተከትሎ፣ የክቡር ዘበኛ ጦር አዛዡ ብርጋዲዬር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ እና በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ከተማሩት ታናሽ ወንድማቸው ግርማሜ ነዋይ ጋር መከሩ።
ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራውን ሀሳብ የጠነሰሱት ከወቅቱ የፀጥታና ደህንነት ክፍል ኃላፊው ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ እና ከፖሊስ ኃይል አዛዡ ከብርጋዴር ጀኔራል ጽጌ ዲቡ ጋር ሆነው ነበር። ታኅሳሥ 5 ቀን 1953 ዓ.ም የወንድማማቾቹ ቡድን ዓላማውን ለሕዝብ ይፋ አደረገ።
የተሻለ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስሪት ያላትን ሀገር እውን ለማድረግ ፍላጎትና ዓላማ እንዳለው ገለፀ። ‹‹ለውጥ ፈላጊ ናቸው›› የሚባሉት ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሾማቸውንና አልጋ ወራሹን አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴንም በማስማማት (አስገድደው ነው የሚሉም አሉ) መንግሥት በቆረጠላቸው ደመወዝ እየተዳደሩ ለሕገ መንግሥት የሚገዙ ንጉሥ ሆነው እንደሚያገለግሉ እራሳቸው ለሕዝቡ በራዲዮ እንዲያስተላልፉ አደረገ።
በቀጣዩ ቀን በወንድማማቾቹ የተጠነሰሰውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሚቃረነው እና የንጉሡ ታማኝ የሆነው የእነ ጄኔራል መርዕድ መንገሻ ኃይል ሙከራውን ለማክሸፍ ዝግጅቱን ጨረሰ። በአየር እና በታንክ ጭምር የተፋፋመ ውጊያ ሲጀምር፤ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ መምሪያ ክፍላቸውን ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ) አዛወሩ።
በቀጣዮቹ ቀናት የምድር ጦሩንና የአየር ኃይሉን ያላሳተፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተዳከመ፤ በአንጻሩ ደግሞ የንጉሱ ታማኞች እያደር እየበረቱ መሄዳቸውን የተገነዘቡት እነ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ በቁጥጥራቸው ስር የነበሩትን መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሚኒስትሮችንና መኮንኖችን ወደ ሌላ ቦታ አዛውረው፣ አልጋወራሹንና አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ለብቻቸው እንዲጠበቁ አደረጉ።
ጄኔራል ጽጌ ዲቡ ወዲያው ከተቃራኒ ወገን (ከንጉሡ ታማኞች ማለት ነው) በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ፣ እነ ብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ደግሞ የያዟቸውን እስረኞት ረሽነው ለማምለጥ በመወሰን፤ ራስ አበበ አረጋይ፣ ሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ራስ ስዩም መንገሻ፣ አቶ መኮንን ሀብተወልድ፣ አባ ሐና ጅማና ሌሎች የንጉሰ ነገሥቱን ባለስልጣናት ረሸኑ።
በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥም የሞቱ ባለስልጣናት ነበሩ። ከእነዚህም መካከል የስመ ጥሩው አርበኛ የኃይለማርያም ማሞ ልጅ እና የንጉሠ ነገሥቱ የልጅ ልጅ የልዕልት ሶፊያ ደስታ ባል የሆኑት ሻምበል ደረጀ ኃይለ ማርያም ይጠቀሳሉ።
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴም ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ተሳትፈዋል የተባሉት ወገኖችም እየታደኑ ተገደሉ። የመንግሥት ግልበጣው መሪ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይም ተይዘው በስቅላት ተቀጡ። ወንድማቸው ግርማሜ ነዋይ ደግሞ በሽሽት ላይ ሳሉ ዝቋላ አካባቢ ከሚያድኗቸው ፖሊሶች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተገደሉ። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውም ሳይሳካ በአጭሩ ተቋጨ።
እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ገለጻ፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎች ዋና ስህተት የጦሩ ዋና አካል የሆነውን የምድር ጦሩን እና የአየር ኃይሉን አለማሳተፋቸው ወይም ሳይቀድመን እንቅደመው በሚል ከጥቅም ውጭ አለማድረጋቸው ነው።
‹‹አማፅያኑ ቢወገዱም ያቀጣጠሉት የለውጥ ችቦ ከእነርሱ ጋር አልጠፋም›› ያሉት የታሪክ ጸሐፊው፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው እንዲያውም የተጀመረው ተቃውሞ የበለጠ እንዲጠናከር ነው ዕድል የፈጠረ። ይህንንም በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ማግስት በህቡዕ ይወጡ የነበሩ መልዕክቶች ያረጋግጣሉ።
‹‹አንድ ሺህ ቀኖች በግ ሆኖ ከመኖር አንድ ቀን አንበሳ ሆኖ መሞት ይሻላል፣ ካለ ደም ስርየት የለም፣ ለአመጸኞች መገዛት ኃጢአት ሲሆን በአመጸኞች ላይ ማመጽ የተቀደሰ ሥራ ነው፤ የታኅሣሥ ሰማዕታት አልሞቱም አሉ በሕይወት….›› የሚሉ መሪ ቃሎች በታሪክ ምሁሩ መጽሐፍ ላይ ይገኛሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ ለ13 ዓመታት ያህል የቆየው የንጉሡ ሥርዓት፤ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ 1966 ላይ ዋናው አብዮት ተቀጣጥሎ ፍጻሜውን አገኘ፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም