
አዲስ አበባ ካሏት ብዙዎቹ ከ100 ዓመታት ያላነሰ እድሜ ጠገብ ሰፈሮች ናቸው። መጸዳጃ ቤት የሌላቸው፣ የፍሳሽ ማስወገጃ የማያውቃቸው፤ ደረቅ ቆሻሻ ዘመዳቸው፣ ተፋፍጎና ተዛዝሎ መኖር እንደ ባህል የሚታይባቸው መንደሮች እና የመዝናኛ ሥፍራዎች ናቸው።
ታሪካቸው ስምና ዝና ብቻ የሆነባቸው። እነዚህን ሰፈርና ቤቶች አጽድቶና አሳምሮ ለነዋሪው ምቹ ፣ ለከተማው ውበት እና መሠረታዊ ለውጥ እንዲያመጡ አድርጎ የማስዋብ ሥራ በወንዝ ዳር ፕሮጀክት ፣ በኮሪደር ልማት አንድ ብሎ ተጀምሯል። አዲስ አበባን እንደስሟ አበባ ለማድረግ።
በዚህም አዲስ አበባ እንደ ስሟ አበባ እና ለም መሆኗን ቀጥላለች። በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የሚሠሩ የልማት ኮሪደሮች ፣ የወንዝ ዳር ፕሮጀክት ልማቶች ከተማዋን አነቃቅተዋታል። በተለያየ አካባቢ በተዘዋወርንባቸው ሰፈሮች አሮጌ ጣሪያ፣ መጥፎ ጠረን ያላቸው የውሃ መውረጃ ቦዮችን ፣ የተከማቹ የቆሻሻ ክምሮች ፣ በየወንዙ ዳር የሚፈሱ የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን የሽንት ቤት ፍሳሾችን ፣ የመዝናኛ ልበል “መደበሪያ “ ንጹህና አጠር ሥፍራዎችን ማየትና መሸማቀቅ ዛሬ ላይ ቀንሷል።
በአዲስ አበባ ነባር መንደሮች ውስጣ ውስጥ ሰፈሮች አፍና አፍንጫን ሸፍኖና ፊት አዙሮ ሮጦ ማለፍ ተረት ተረት ሊሆን ተቃርቧል። በየቦታው የለሙ ሥፍራዎችን ማየትና ማድነቅ አለፍ ሲልም በተዘጋጁት የመንገድ ዳር የማረፊያ መቀመጫዎች ላይ አረፍ ብሎ አእምሮንም ሆነ ሰውነትን ዘና የማድረጉ ጉዳይ እየሰፋ መጥቷል።
ሳይክል ነጂው በነጻነት ከሰውና መኪና ግፊያ ወጥቶ በራሱ መስመር ላይ አለሁ ብሏል። በየአካባቢው የተገነቡ የህጻናት መጫወቻ ሥፍራዎች፤ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ሱቆች ፣ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎች፣ መጸዳጃ ቤቶች ፣ የቡናና ሻይ መጠቀሚያ ቤቶች ፣ የእግረኛ መንገዶች… ሁሉ የከተማው ድምቀቶች ናቸው።
አንጸባራቂ ከተማ አድማቂ መብራቶች የተንጣለሉት የአስፋልት መንገዶች እግረኛ ያለስጋት የሚዘዋወርባቸው ምቹ መንገዶች ፤ ከልጆች ጋር በቀላሉ የሚያቀራርቡ ጤናን ለመጠበቅ የሚያስችል የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረጊያ ሥፍራዎች…ሁሉ እስካሁን የትነበርን ብለን ዛሬ በቁጭት እንድናያቸው የሚያደርጉን ናቸው።
አንድ ወዳጄ ከምሳ ሰዓት በኋላ በመንገድ ዳር በተሠሩት መናፈሻዎች ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ መጽሐፍ ሲያነብ አገኘሁት። ምን እያደረክ ነው? ስለው የመለሰልኝ መልስ ከውስጤ ውስጥ ውሏል። ከፊቱና ከኋላው፤ ከቀኝና ከግራው በእጁ እያማተረ “ይሄ አካባቢ ምን ይመስል እንደነበር ያደግንበት ሰዎች ብቻም ሳንሆን በዚህ መንገድ የተመላለሰ ወጪ ወራጁ ሁሉ የሚያውቀው ነው።
‹የሚሸት ፤ ለማየት የሚቀፍ ፣ ለማለፍ የሚዘገንን› አካባቢ ነበር ። አካባቢው ላይ እንኳን ቁጭ ሊባል ቀርቶ በመንገዱ ማለፍ ከባድ ነበር። አሁን ወዳጄ የኮሪደር ልማቱን ጥቅማጥቅም እያጣጣምኩ ነው። ንጹህ አየር እየሳብኩ በዛፎቹ መሀል መናፈሻ ውስጥ ቁጭ ብዩ ይኸው እንደምታየኝ መጽሀፌን አነባለ ሁ” አለኝ ።
እውነቱን ነው ማየት ማመን ነው። ወደ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ የነበረውን መጥፎ ጠረን የመንገድ መጣበብ ፣ ጎዳና ላይ የወጣውን ንግድ እና ሌላውንም ማስታወስ በቂ ነው። አሁን እኮ ማንም ሰው በእግሩ ልጓዝ ቢል እንኳን በተዘጋጁት ወንበሮች ላይ አረፍ እያለ ንፁህ የሆኑ ለዓይን ማራኪ አካባቢዎችን እያየና እያደነቀ ይሄዳል። ይሄ በጣም ደስ የሚል ነው። ለከተማችንም ስሟን መቀየሪያ ነው።
አካባቢውን ዘመናዊ ያደረገው መንገዱ ብቻም ሳይሆን ድልድዩም ጭምር ነው። የአካባቢው አረንጓዴነት የዓይን ልዩ ማረፊያ ነው። ይህን ያየ እንደ እኔ አዲስ አበባ እንደስሟ እየሆነች ነው ቢል አላጋነነም። ውብ ከተማ እያየን ስለሆነ። እንዳው ልማቱ አልታየኝም፣ ውበቱ አልተገለጸልኝም ፣ የሚል ጭፍን የሆነ አመለካከት ያለው ልቡን ከፍቶ ማየት የተሳነው ሰው ነው። ሥራው በራሱ ምስክር ነውና ይታያል ፤ ይዳሰሳል፤ ይጨበጣል። ተወደደም ተጠላም ፤ ደገፍነውም ተቃወምንም አዲስ አበባ አበባነቷን አጠንክራ ቀጥላለች።
እንዳው በዓይኔ ያየሁትን ለውጥንም በቅርበት የማውቀውን አካባቢ በምሳሌነት አነሳሁ እንጂ በየተሄደበት ሰፈር ሁሉ እጅግ አስደናቂና አስደማሚ የልማት ሥራዎች ናቸው የሚታዩት። ከየነዋሪው የሚሰማውም ይኸው ነው። አድናቆት። ከተማዋ እንደ አዲስ እየተወለደች ነው የሚል። “ እንዳው በቁማችን ሞተን ነበር ለካ “ ያሉኝንም አዛውንት አለማንሳት ንፉግነት ነው።
መሥራት የሚችሉ እጆች አእምሮና ጉልበት እያለን በማይሆን ሁኔታ ውስጥ ዘመናችንን ማሳለፋችን አሁንም ይቆጫል። ቁጭት ብቻ እንደማያዋጣ አውቆ ለልማቱ ተባባሪና ተሳታፊ መሆን ደግሞ ይገባል። ከአቧራ ስር ብዙ ያላያናቸው ያልተጠቀምንባቸው ወርቆቻችን ስላሉ በወርቆቻችን አምረንና አጊጠን ለመኖር ለልጆቻችን ለልጅ ልጆቻችን የተሻለች ሀገርና ከተማን ማኖር ያስፈልገናል። አኗኗራችንን መቀየር ይገባናል።
ከዘልማድ አኗኗር ወጥተን ዘመናዊነትን መለማመድም ይኖርብናል። መጠየፍ ያለብንን መጠየፍ፣ ማሳደግ ያለብንን ማሳደግና ማስፋት ይኖርብናል። በሌሎች ሀገራት የምናያቸውን የሚያስደንቁንና የሚያጓጉንን አኗኗርና ሀገር በአጭር ጊዜ ውስጥ መሥራት እንደሚቻል በአዲስ አበባ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች አይተናል።
በቆራጥነት መነሳሳቱ ካለ ጠንካራ ሠራተኛ እንጂ ተመልካች ካልሆንን በሁሉም ቦታ አንጸባራቂ ውጤቶችን፤ ዘመን የማይሽረው ድሎችን በሥራችን እንጽፋለን። ይሄንን በአጭር ጊዜ በተሠራ ሥራ አይተን አጣጥመናል። አዲስ አበባን ተባብረን እንደ አዲስ እንውለዳት ፤ ጽዱና አረንጓዴ ለነዋሪዎቹ ምቹ ለእንግዶቿ የሆነች ከተማ መሆኗን በሁሉም መልኩ ማረጋገጥ አለብን።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 2017 ዓ.ም