ልጅነት ያልመለሰው ቂም

አኗኗራቸው ቅርርብ የተሞላበት ነው። በመሆኑም በየእለቱ አንዱ ሌላኛው ጎረቤቱን ቡና ሳይጠራ፤ አብረው ሳይጨዋወቱ ውለው አያድሩም። የተለያዩ በዓላት ሲሆኑ ደግሞ በህብረት ማክበር የተለመደ እና በሚኖሩበት አካባቢ ትልቅ ትውስታን የሚፈጥር ጭምር ነው። ልጆች ከወላጆቻቸው ባህሪን እንደሚወርሱ በአንድ ሰፈር ውስጥ አብሮ ማደግ ጓደኝነት ብቻ ሳይሆን ወንድማማችነት ቤተሰባዊነት ጭምር የሚፈጥር ነው። ሆኖም ተክለሃይማኖት አካባቢ የተፈጠረው ከዚህ የተለየ ነው።

ስንታየሁ ለዚህ ሰፈር ገና አዲስ ነው። ሆኖም ቀደም ሲል የነበረበትን እና ያደገበትን ሰፈር ይወደዋል። ነገር ግን በቤተሰቦቹ የሥራ ቦታ መቀየር ምክንያት ወደ ተክለሃይማኖት ሰፈር መጥቶ መኖር ከጀመረ የወራት ያህል እድሜ ብቻ ነው ያለው። ነገር ግን ከሰዎች ቶሎ የሚግባባ በመሆኑ እና ኳስ ወዳጅ ስለሆነ ከተክለሃይማኖት ሰፈር ልጆች ጋር ለመወዳጀት እና ጓደኛ ለማፍራት ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። አዲስ ካፈራቸው ጓደኞቹ ጋር በፍጥነት በመግባባት ትምህርት ቤት የሚያካሂዱት፣ አብረውት ሰፈር ውስጥ ኳስ የሚጫወቱ ጓደኞችን አፍርቷል። ከእነዚህ ጓደኞቹ ጋርም ቀድሞ በነበረበት ሰፈር ውስጥ ያደርግ የነበረውን ወዳጅነት መስርቷል።

በአካባቢው ሰዎች ከቤታቸው በመውጣት ከሚያከብሯቸው በዓላት ውስጥ የቡሄ በዓልን፣ የመስቀል በዓልን በህብረት ማክበር የተለመደ ነው። አማኑኤል፣ ስንታየሁ፣ ዳግማዊ በሰፈር ውስጥ አብረው መሆንን የሚዘወትሩ ጓደኛማቾች ናቸው። ኳስም ሲጫወቱ ሆነ ከትምህርት ቤት መልስ ጊዜያቸውን አብረው ያሳልፋሉ።

የደመራ ዋዜማ

የመስቀል ደመራ በዓል በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው። በዚህ እለት ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ መስቀል አደባባይ በዓሉን ሄደው ከሌሎች ምዕመናን ጋር በመሆን ያከብራሉ። ከዚያ ሲመለሱም በየሰፈራቸው የራሳቸውን ደመራ አዘጋጅተው ከጎረቤቶቻቸው፣ ከወዳጆቻቸው ጋር በሕብረት በዓሉን በየዓመቱ ያከብራሉ።

የመስቀል ደመራ በዓል በሚከበርበት እለት መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 6፡30 እስከ 7፡00 ባለው ጊዜ ውስጥ ስታየሁ እና ጓደኞቹ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ልዩ ቦታው ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ሰፈር የደመራ በዓል ለማክበር በመረጡት ቦታ ላይ ደመራቸውን ማስተካከል እና የመድረክ ማስዋብ ሥራን በህብረት እያከናወኑ ነው።

ታዲያ ለዚህ የመስቀል በዓል አከባበር የመድረክ ማስዋብ ሥራ እና የደመራ ዝግጅት ወጣቶቹ ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በአካባቢው ካሉ ነዋሪዎች በመንገድ ከሚያልፉ ሰዎች ይሰበስባሉ። በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችም ይህንን ልምድ ስለሚያውቁት በቦታው ሆነው ባያግዟቸውም በገንዘብ በመደገፍ ወጣቶቹ በፈለጉት መንገድ ሰፈሩን በዓል በዓል እንዲሸት ገንዘብ በማዋጣት ይተባበሯቸዋል። በዚህ በዓላት ላይ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ እናቶች እና አባቶችም የራሳቸውን ህብረት በመፍጠር የተለያዩ ምግቦችን በህብረት ማዘጋጀት የተለመደ ነው።

ታዲያ ለዚህ ሥራ ሁሉም የሥራ ድርሻቸውን ተከፋፍለዋል። ገንዘብ የሚሰበስበው፣ አካባቢውን ለበዓሉ ዝግጁ በማድረግ መድረክ የመሥረታ ችሎታ ያለው፣ ደመራ የመሥራት ችሎታ ያላቸው ደግሞ በሰፈሩ ታላቅ የሚባሉ ከስንታየሁ እና ጓደኞቻቸው ከፍ ያለ እድሜ ያላቸው ደመራው በመሥራት ላይ ናቸው። ቢንያም በዚህ ቡድን ውስጥ ከሰዎች ገንዘብ የመሰብሰብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ዳግማዊ ደግሞ መድረኩን በመሥራት ላይ ነው። በድንገትም ቢንያም የታዘዘውን እቃ ለማምጣት በአካባቢው ባለመኖሩ ለበዓሉ የሚውል ገንዘቡ ዳግማዊ ከሚሰጠው ሰው ከተቀበለ በኋላ ለቢንያም መስጠት ሲገባው ወደ ኪሱ ሲከተው ስንታየሁ ይመለከታል። ከዚያም ገንዘቡን የመሰብሰብ ኃላፊነት ለተሰጠው ጓደኛው እንዲመልስለት ይጠይቀዋል። በስጥ አልሰጥም የተፈጠረው የቃላት ልውውጥ ለጸብ እንዲጋበዙ ሲያደርጋቸው በቅርባቸው የነበሩ ሰዎች አገላግለው ለጊዜው ረገብ እንዲል አደረጉት። ወጣቶቹ ግን ግጭታቸው በዚህ አልተፈታም ነበር።

ለመስቀል በዓል የታሰበው የመድረክ ማስዋብ ሥራ ተሰርቶ ልክ በሌሎች አካባቢዎች እንደሚከበረው ዳግማዊ ሰፈርም በጥሩ ሁኔታ ተከብሮ እለቱ አለፈ። ዳግማዊ እና ስንታየሁ ጓደኛማቾች ቢሆኑም የተዋወቁት በቅርቡ ነው። ስንታየሁ እና ቤተሰቦቹ እነ ዳግማዊ ሰፈር የገቡት በቅርብ ነው። ነገር ግን ልጆች በመሆናቸው ዳግማዊ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የተግባባው በቶሎ ነበር። ጓደኝነት የዚህ ሰፈር የዚያ ሰፈር፤ የታች ሰፈር ልጆች የላይ ሰፈር ልጆች የሚል ቡድን ይኖረዋል። በየቡድኑ ደግሞ አንድ በጣም የሚወደድ ሰው የቡድኑ መሪ ይሆናል።

ዳግማዊ በባህሪው ቁጡ እና ትንሽ ነገር ይበቃዋል የሚባል ባህሪ ያለው ነው። ታዲያ ይህ ባህሪው ስንታየሁ ጋር ብዙም የሚገጥም አይደለም። ዳግማዊ 20 ዓመቱ ሲሆን ስንታየሁ ደግሞ ከእሱ በሁለት ዓመት ያንሳል። ሁለቱም ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው በተቀራራቢ እድሜ ላይ የሚገኙ ጓደኛማቾች ናቸው። ታዲያ በትምህርት ቤት የኳስ ጨዋታ በሰፈር የሚያጋጫቸው ጉዳይ አይጠፋም። ነገር ግን ጓደኛማቾች የአንድ ሰፈር ልጆች በመሆናቸው ዞረው መገናኘታቸው አይቀሬ ነው።

ያደረ ቂም

በእዚህ ቀን ስንታየሁ እና ጓደኛው አማኑኤል ኳስ ተጫውተው በመመለስ ላይ ናቸው። ወደ ሰፈራቸው ሲገቡም ቀኑ ወደ መምሸቱ ነበር። ታዲያ ዳግማዊ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን ሁልጊዜ ተቀምጠው ከሚያመሹበት እና ከሚጨዋወቱበት ሥፍራ አምሽተው ወደቤታቸው ለመሄድ ተሰነባብተው ተለያዩ። ከስንታየሁ ጋር በመንገድ ተገናኙ። ጸብ የማይረሳው ዳግማዊ በዚህ ምሽት ስንታየሁን ለይቶት ኖሯል ገፋኸኝ በሚል ምክንያት መነጋገር ጀመሩ። ንግግራቸው መንገድ ለምን አልለቀቅልኝም ሳይሆን የቆየ ቂም የነበረው በመሆኑ ከቃላት ልውውጥ፣ ከስድብ ባለፈ ወደ እጅ መሰንዘር ገቡ።

እጅ ለእጅ ከተያያዙ በኋላ ዳግማዊ በቦክስ ስንታየሁን አፍንጫውን መታው ዳግም መሬት ላይ ወደቀ። በወደቀበት ሌላ ቦክስ የስንታየሁ ፊት ላይ አረፈ በቦታው የነበረው የጋራ ጓደኛቸው አማኑኤል አገላገላቸው። ዳግማዊ ሮጦ ወደቤቱ ገባ ፤ ታዲያ እልኸኛው ስንታየሁ ዝም ብሎ ወደቤቱ ለመሄድ አልፈለግም ተከትሎት ወደ ዳግማዊ ቤት ሮጠ ‹‹ ና ውጣ እያለ ይጠራው ጀመር የቤቱን በርም በድንጋይ መታው ለማገላገል በቦታው የነበሩ ጓደኞቹ እንዲህ የከረረ ጸብ ውስጥ ይገባሉ የሚለውን አልገመቱም በመሆኑም አማኑኤል ብቻ ሲቀር ሌሎቹ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ከዚህ በኋላ የሆነው ግን ያልጠበቀ ጉዳይ ነበር።

ዳግማዊ ቤት ውስጥ የተቀመጠ ስለት ይዞ በመውጣት ከፊት ለፊቱ ያገኘውን ስንታየሁን ደረቱ ላይ ጀርባው ላይ በተደጋጋሚ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ጓደኛውን በመውጋት ተመልሶ ወደቤቱ ገባ። ስንታየሁ መቋቋም የማይችለው ጥቃት ደርሶበታልና ተዝለፍልፎ መሬቱ ላይ ወደቀ ራሱን እንኳን መከላከል አልቻለም። በቦታው የነበረው አማኑኤልም እጅግ አስደንግጦት ሌሎች ሰዎች እስኪሰበሰቡ እና እንዲረዱት መጮሁን ቀጠለ። በአካባቢው የነበሩ ሰዎችም ከየቤታቸው ጩኸቱን ወደሰሙበት አካባቢ ሄዱ። የስንታየሁ የአክስት ልጅ፣ ጓደኞቹ እና በወቅቱ በሰፈሩ የነበረውን የላዳ ሹፌር በመጠቀም ወደ አቅራቢያቸው ሆስፒታል ስንታየሁን ለማትረፍ ሄዱ።

የፖሊስ ምርመራ

ስንታየሁ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ በቅድሚያ የመጀመሪያ ርዳታ ለማግኘት ወደ ተክለሃይማኖት አጠቃላይ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር። ነገር ግን የደረሰበት ጉዳት በርካታ ቦታዎች ላይ በስለት ጉዳት በመድረሱ እና ከፍተኛ ደም በመፍሰሱ ሕይወቱ በዚያኑ እለት ሊያልፍ ችሏል።

መረጃው የደረሰው ፖሊስ ወደቦታው በማምራት ጉዳዩን ፈጽሟል የተባለውን ዳግማዊን በቁጥጥር ስር አዋለው። ስንታየሁ በስለት ደረቱ ላይ ሁለት ጊዜ፣ ጀርባው ላይ ሁለት ጊዜ፣ የግራ እጁ ላይ አንድ ጊዜ እንዲሁም ሆዱ ላይ አንድ ጊዜ በርካታ ቦታዎች ላይ በስለት በመወጋቱ በደረት እና በሆዱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ምክንያቱ ርዳታ ለማግኘት በሄደበት ሆስፒታል ሕይወቱ እንዳለፈም መረጃውን ማግኘት ችሏል። በመሆኑም ዐቃቢ ሕግ ዳግማዊ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 (1) (ሀ) ስል የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽሟል ክስ መስርቶ ምርመራውን ማድረግ ጀመረ ።

የወንጀሉ ዝርዝር

የፌዴራል ዐቃቢ ሕግ ተከሳሽ ዳግማዊ በ27 ቀን ጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ሟች ስንታየሁ በመንገድ ላይ አግኝቶት ገፋኸኝ በማለት ንግግር ከጀመሩ በኋላ ተከሳሽ ዳግማዊ ስንታየሁን በቦክስ መትቶት ወደ መሬት ወደቀ ከዚያም እርስ በእርስ ከተያያዙ በኋላ ጓደኛቸው አማኑኤል ሲገላግላቸው ዳግማዊ ሮጦ ወደቤቱ ገባ፤ ስንታየሁም ወደ ዳግማዊ ቤት በመሄድ ና ውጣ በማለት በድንጋይ የቤቱን በር ሲመታው ዳግማዊ በቤት ውስጥ የነበረ ስለት ይዞ በመውጣት እና ስንታየሁን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በአሰቃቂ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመውጋት ጉዳት አድርሶበታል። ዓቃቤ ሕግ በመሰረተው ከባድ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃውን ማሰባሰብ ጀመረ። ተከሳሽ ዳግማዊንም ወንጀሉ ከተፈጸመበት እለት አንስቶ በቁጥጥር ስር አዋለው።

ማስረጃዎች

ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያጠናክርልኛል ያላቸውን የሰው ማስረጃ በቦታው የነበሩ እና በሟች ስንታየሁና በተከሳሽ ዳግማዊ መካከል የነበረው ጸብ የሚያስረዱ ምስክሮችን በተሰጠው የቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት ይዞ ቀረበ። ዐቃቢ ሕግ ባቀረበው የሰው ማስረጃ የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ተከሳሽ ዳግማዊ ሟች ስንታየሁን ደጋግሞ መውጋቱን አረጋግጠዋል። ወንጀሉን የፈጸመው ተከሳሽ ዳግማዊም ለፖሊስ በሰጠው ቃል ወንጀሉን መፈጸሙን በሰጠው ቃል አረጋግጧል። ዓቃቤ ሕግ የሟች የአስክሬን ምርመራ እና የምርመራ ውጤቱን ዝርዝር ትርጓሜ ይዞ ለመቅረብም ተጨማሪ የ14 ቀን ቀጠሮ ጥያቄ ለፍርድ ቤት አቀረበ። ፍርድ ቤቱ ሌሎች መረጃዎች እንዲቀርቡ ተጨማሪ የ10 ቀን ቀጠሮ ፈቀደ።

ሟች ስንታየሁ ከበደ የመጀመሪያ ርዳታ ለማግኘት ከሄደበት ተክለሃይማኖት አጠቃላይ ሆስፒታል የሞት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ በላከው የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ መረጃ በውጫዊ አካሉ ላይ ሟች ስንታየሁ በስለት የተወጋባቸው ቦታዎች ደረቱ ላይ ሁለት ጊዜ ፣ የግራ ክንዱ ላይ አንድ ጊዜ ፣ ጀርባው ላይ አንድ ጊዜ፣ ሆዱ ላይ አንድ ጊዜ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን በውስጣዊ አካል ላይ መረጃ የውስጥ ደም መፍሰስ መኖሩን የሚያስረዳ የአስክሬን ምርመራ ውጤት እንደማስረጃ ተጠቅሟል።

ዓቃቤ ሕግ ባቀረባቸው ገላጭ ማስረጃዎች ወንጀሉ ከተፈጸመበት ሥፍራ የተገኘ ደም የነካው ቢላ፣ የሟች አስክሬን የጉዳት መጠን፣ የወንጀል ሥፍራውን የሚያሳዩ 12 የፎቶግራፍ ማስረጃዎችን ይዞ ቀርቧል። ከወንጀል ሥፍራ የተገኘ ቢላዋ በኤግዚቢትነት ተይዟል።

ውሳኔ

በከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ ዳግማዊ ታገል ከበደ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በነበረው ክርክር በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 ( 1 ) ( ሀ ) ስል የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፍርድ ቤቱ በጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ዳግማዊ በተከሰሰበት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል የቀረቡለትን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በመመልከት ተከሳሽ በ15 ዓመት ከሶስት ወር ጽኑ እሥራት ይቀጣ በማለት ውሳኔ አሳልፏል ።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You