ኢትዮጵያ በአንድነቷ ጸንታ በታሪኳ ደምቃ እንድትኖር ካስቻሏት እውነታዎች አንዱ የብሔር ብሔረሰቦቿ ጥብቅ ቁርኝትና ደማቅ ኅብር ነው። ይህች ታላቅ ሀገር እንደ ዕድሜ ጠገብ ታሪኳ በመልከ ብዙ ማንነት የተዋቀረች ናት። ሕዝቦቿ በበርካታ ቋንቋና ባሕሎች ይታወቃሉ። በተዋቡ አልባሳትና በልዩ ወግ ልማዶች ይለያሉ።
እነዚህ ሕዝቦች በአመጋገብ፣ በአለባበስ፣ በቋንቋዎችና በአኗኗር ገጽታቸው ልዩነትን ይዘው ዘልቀዋል። ይህ እውነታ ግን በባዕድነት ለያይቶ አንድነታቸውን አልከፋፈለም። አንዳቸው እንደብዙ፣ ብዙዎችም እንደ አንድ ሆነው ኢትዮጵያዊነትን ሲያውጁ፣ ሲያደምቁ ኖረዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በባዕዳን ዓይኖች የመግባት አጋጣሚ አግኝቷታል። ማራኪ ተፈጥሮዋ ማርኳቸው አንጡራ ሀብቷን ሊቀራመቱ ባሕር አቋርጠው በመጡ ወራሪዎችም ሰትፈተን ቆይታለች። እንዲህ በሆነ ጊዜ በሁሉም አቅጣጫዎች የሚገኙ ሕዝቦቿ ክንድ ይበረታል። ስለማንነታቸው ቋንቋና ባሕላቸው አንድ ይሆናል። ሀገር ይሏት እውነት ትርጉም ታገኝ ዘንድ አንድነት በገሀድ ይታያል። ኅብረብሔራዊነት በአደባባይ ይመሰከራል።
የኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የመኖሯ ምስጢር የሕዝቦቿ አንድነት ነው። ዘር፣ ቋንቋ ብሔር ሳይለያቸው ስሟን ጠብቀው ዘመናትን አሻግረውታል። ዛሬም ቢሆን በልማት፣ በሠላም ማስከበርና አብሮ በመኖር እሴት አንድነታቸው አይላላም። እስከዛሬ አንድ ሆነው ችግርን ተጋፍጠዋል። በአንድነት ስለሠላም ዘምረዋል። በእኩል ድርሻ ለሀገራቸው ሕልውና ዘብ ቆመዋል።
ሁሌም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ከሚለያያቸው ጉዳዮች ይበልጥ አንድ የሚያደርጋቸው እሴት ይበልጣል። በዚህ አንድነት ውስጥ ደግሞ ደስታና ችግርን በእኩል ይካፈላሉ። ዘርን ከብሔር ሳይለዩ በዝምድና፣ በጋብቻ ይተሳሰራሉ። ይህ እውነት አንድነታቸውን አጠናክሮ ባዕድነታቸውን አርቋል፣ አብሮነታቸውን አውጆ ማንነታቸውን አስከብራል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሥነጽሑፍ ሀብቶቻቸው፣ በባሕላዊ አልባሳታቸው፣ በሙዚቃዎቻቸው፣ በጥዑም ምግቦቻቸውና በሌሎችም ማንነታቸው ይዛመዳል። ከሌሎች ዓለማት በላቀ መልኩ ልዩነታቸው በአንድነት መጋመዱም ሀገርን የሚያኮራ፣ ብዙኃንን የሚያስደንቅ ነው።
በኢትዮጵያ ኅብረብሔራዊነት ዕውን መሆን ከጀመረበት አንስቶ ዜጎች በማንነታቸው ተከብረው እንዲኖሩ፣ ዕድል ተፈጥሯል። ባሕልና ቋንቋቸውን አንፀባርቀው፣ በአልባሳታቸው ደምቀው በአደባባይ ታይተዋል። ይህ ትስስር በልዩነት መሐል ውበትን ያሳየ ነው። በውበት ጥግ ደግሞ የአብሮነት ማኅተም ደምቋል። የአንድነት ኃይል ተንፀባርቋል።
ሁሌም የአንዱ ብሔር ድምቀት ለሌላው ውበት በሆነባት ሀገረ-ኢትዮጵያ ለዘመናት መቻቻል ይሉት ጥበብ ሲንፀባረቅ ቆይቷል። በጉርብትና፣ በመደማመጥና መከባበርም አብሮነት ገዝፎ ታይቷል። ዛሬ በሀገራችን የአንዱን አልባሳት ሌላው ሳይደምቅበት አይውልም። ባሕላዊ ሙዚቃውን እንደራሱ የሚያዜምበት የሚጨፍርበት በርካታ ነው። በዚህች ምድር ባሕልና ወግ በተለየ የክብር መንገድ በኩራት ይራመዳል።
ሀገራችን መልከ ብዙ የሆኑ ሕዝቦቿን በአንድ አቅፋ መኖሯ ብርቅ ሆኖ አያውቅም። የበርካታ ቋንቋዎች በረከት፣ የውብ አልባሳት መገኛ፣ የአስገራሚ ባሕሎች መፍለቂያ ናት። የተለያዩ ቋንቋዎችና ባሕል ያላቸው ሕዝቦቿ በዕምነት ሃይማኖታቸው አንድ ይሆኑባታል። በአለባበስ፣ በጭፈራ ይዛመዱባታል። ይህ ሐቅ ደግሞ ሁሌም በቱሪስቶች ዓይን ሥር ለመውደቅ ቅርብ እንዳደረጋት ኖሯል።
ኢትዮጵያ እጅን በአፍ በሚያስጭነው የኅብረ ብሔራዊነት ድምቀቷ ጎብኚዎች ደጋግመው ይቋኟታል። ታሪኳ፣ ባሕልና ወጓ አስደምሟቸውም ስሟን በወርቃማ ብዕር አድምቀው የሚጽፉ፣ ታሪኳን ለመላው ዓለም የሚያጋሩ ባዕዳን ጥቂቶች አይደሉም።
ዛሬ በሀገራችን በኅብረ-ብሔራዊነት መሠረት ላይ የአንድነት ምሰሶ ጸንቷል። በመግባባትና መተሳሳብ
የሚኖረው ዋጋ ሚዛን ደፍቷልና ከጥቅሙ የሚጋሩ ሕዝቦች በረከትን እየተካፈሉ ነው። በአብሮነት የጋራ ልማትን ዕውን ማድረግ፣ በመግባባትና መቻቻል የሠላምን ዋጋ ማግዘፍ ተችሏል።
መቼም ቢሆን ከመለያየትና መነጣጠል የሚገኝ ፍሬ የለም። ማንም እንደሚያውቀው በግጭትና ጦርነት ሠላም ይደፈርሳል ፣ የሀገር መሠረት ይናዳል። አንድነት ካለ፣ ምድር በበረከቷ ውላ ታድራለች፣ የሰው ልጆች በእፎይታ ይኖራሉ። ሕይወት ያለው ሁሉ ዋስትናው ይረጋገጣል። ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ የሕዝቦች መግባባት፣ የአብሮነታቸው መሠረት ሊጸና ይገባል።
በልዩነት መሐል አንድነት ሲንፀባረቅ ጎዶሎ ይሞላል፣ በክፋት መፈላለግ፣ በቂም በቀል መተያየት ነውር ይሆናል። የአንድነት ክንድ በበረታ ቁጥር ድህነት ታሪክ ሊሆን፣ ረሀብ ጦርነት በ‹‹ነበር›› ሊወሳ ጊዜው ቅርብ ነው። ለዚህ ደግሞ ለኅብረ ብሔራዊነት የሚሰጠው ዋጋና ቀለም ከሌሎች እንዲለይ ያደርገዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ለብሔር ብሔረሰቦች የተሰጠው ልዩ መብት ዜጎች በእኩልነትና በአንድነት የመኖር መብት እንዳላቸው የሚደነግግ ነው። የሀገራችን ሕዝቦች በማንነታቸው ሳያፍሩ፣ የሌሎችን መብት አክብረው የሚያከብሩበትን ልዩ ቀንም ለይተዋል- በወርሐ ኅዳር 29። ይህ ዕለት መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት እጅ ለእጅ የሚያያዙበት፣ ታላቅና ድንቅ ቀን ነው።
ኅዳር 29 ኅብረ ብሔራዊነት በአካል ገዝፎ በተግባር ተከውኖ የሚረጋገጥበት ነውና ልዩነት በአንድነት ተዋዝቶ በድምቀት ይንፀባረቅበታል። በዚህ ቀን ሁሉም እንደ አንድ፣ አንድም እንደ ብዙ ሆኖ የሚጋመድበት ልዩ ዕለት ነው። የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕልና ዜማዎች በመልከ ብዙ አልባሳት ደምቀው ይታያሉ። የቋንቋ፣ የባሕልና አልባሳት ኅብር በውበት ደምቆ ይልቃልና ልዩነቱ በውበት አንድ ይሆናል።
ይህ ታላቅ ቀን በየዓመቱ የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ በሆኑና በተመረጡ የክልል ከተሞች ይከበራል። በዓሉ የድምቀት ቀን ብቻ ሆኖ አያልፍም። በሕዝቦች መሐል የእርስ በርስ ትውውቅ፣ የባሕል ተሞክሮና የልምድ ልውውጦች ማድረግ የተለመዱ ናቸው።
በዕለቱ የራስን ማንነት ከማንፀባረቅ ባለፈ የሌላውን ባሕልና ወግ ተውሶ በኢትየጵያዊነት ደምቆ ማሳለፍም የኅዳር 29 ቀን ልዩ መገለጫ ነው። ዘንድሮ ለ19ኛ ግዜ የተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አዘጋጅ በሆነችው የአርባምንጭ ከተማ በድምቀት ተከብሮ አልፏል።
አርባ ምንጭ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምትገኝ እንደመሆኗ በዙሪያዋ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ይገኙባታል። ከዚህ ባሻገር የሀገራችን የቱሪስት መስሕብ በመሆን የቱሪዝም አንዱስትሪውን ትመራለች። ሰሞኑን በተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አስቀድመው የነበሩ አምስት ቀናት የተለያየ ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር።
የደቡብ ኢትዮጵያ ቀን፣ የወንድማማቾች፣ የብዝኃነትና የምክክር ቀን፣ እንዲሁም የክብረ በዓሉ የመጨረሻው ዕለት የኢትዮጵያ ቀን የሚል ስያሜ ተችሮት በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ አልፏል። ዘንድሮ የተከበረው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ‹‹ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት›› የሚል መርሕን አንግቧል። ስያሜውንና ዕለቱን በሚተረጉሙ ሁነቶችም ሁሉንም ብሔረሰቦች ባሳተፈ አንድነት ቀኑ በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉን ለመታደም ኅዳር 29 ቀን በአርባምንጭ ከተማ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችንን እንደ አንድ ታላቅ ቤተመጽሐፍት በመመሰል ገልጸዋታል ‹‹ኢትዮጵያ እንደ አንድ ትልቅ ቤተመጻሕፍት ናት ። በውስጧ ልዩ ልዩ መጻሕፍቶች፣ ልዩ ልዩ ታሪኮች፣ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ዕውቀቶችና ጥበቦች ይገኙባታል።
እነዚህን ዕውቀቶችና ጥበቦች በተናጠል ከመገልገል በላይ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ በሙሉነት ማየት ይበልጥ የሚያጠነክር፣ የሚጎላበት የሚያሻግር ስለሆነ ከሰፈር፣ ከመንደር በላይ የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማየት እንድንችል ከአንድ መጽሐፍ በላይ በቤተመጽሐፍት መገልገል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቃሚ መሆኑን በዚሁ ታላቅ በዓልና በውቢቷ አርባ ምንጭ ከተማ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ሲሉ ዕለቱን በተምሳሌት አስደግፈው ገልፀውታል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም