ገና ከልጅነቱ የወጠነው ዕቅድ፣ የሰነቀው ተስፋ ብሩህና ደማቅ ነበር። ሁሌም እንደሚያስበው አንድ ቀን ራሱን የተሻለ ወንበር ላይ ያገኘዋል። ይህ ደግሞ ህልም አይደለም፤ ዕውን እንደሚሆን እርግጠኛ ነው። ሀሳብ ዕቅዱ እንዲሳካ፣ ዓላማው ከግብ እንዲደርስ ደግሞ ተቀምጦ አይጠብቅም። በየቀኑ ልፋት ትጋቱ፣ሩጫ ፍጥነቱ ከእርሱ ጋር ነው።
ሀብታሙ በላይ መልከ መልካም ይሉት ወጣት ነው። ሁሌም ከፊቱ ደማቅ ፈገግታ አይጠፋም። ከመከም ጸጉሩ፣ ማራኪ ተክለ ሰውነቱ ሸጋ ከሚባሉት መሀል ይመድበዋል። ሀብታሙ ሁሌም መሽቶ በነጋ ቁጥር ከእንቅልፉ የሚነቃው አድምቆ ከሚነድፈው ብሩህ ተስፋ ጋር ነው።
አንድ ቀን ይህ ወጣት አስቀድሞ የጤና ምርመራ ሲያደርግለት ከነበረው ሀኪሙ ፊት ቀረበ። ሀኪሙ በእጁ የያዘውን የምርመራ ውጤት እያገላበጠ በዝግታ እውነታውን አሳወቀው። ሀብታሙ ሊድን በማይችል ከባድ ህመም ተይዟል።ይህ ህመም ውሎ አድሮ ውጤቱ የከፋ ነው። መላ አካሉን ከእንቅስቃሴ፣ ፈጣን እግሮቹንም ከእርምጃ ያግዳል።
በዛች ዕለት የሰማው ክፉ ቃል የሀብታሙን ብሩህ ተስፋ ለማጨለም አቅም አላጣም። ወጣቱ በእጅጉ ሀዘን ገባው። ህልም ሩጫው ፣ ተስፋና ዓላማው እንዳልነበር መሆኑን አስቦ አንገቱን ደፋ፣ የተሰበረ ልቡ በቀላሉ የሚጠገን አልሆነም። የእሱን ውስጠት የሚያጽናና፣ ማንነቱን የሚያበረታ ቃል እስኪጠፋ በሀዘን ተጎዳ። አሁን ሲያስባቸው የቆዩ ዕቅዶቹ፣ሲነድፈው የነበረ ታላቅ ህልም ከጫፍ ላይደርስ ከመንገድ ቀርቷል።
ሀብታሙ ደጋግሞ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተመላለሰ። በየቀኑ በድብርትና ቁዘማ ፣ በዝምታና ጭንቀት ተዋጠ። መለስ ብሎ ደግሞ ወደ አዕምሮው ውል ስላለበት ጉዳይ ማሰላሰል ያዘ። በዚህ ስብራቱ ታሞ መዝለቅን አልፈለገም። ወደ አንድ ገዳም ለመሄድ ወስኖ ከስፍራው ደረሰ። የሰው ድምጽ ከራቀበት ፣ ወፎች በዜማ ከሚንጫጩበት መንፈሳዊ አጸድ ለሶስት ቀናት ውሎ ሊያድር አስቧል። እንደ ዕቅዱ ሆኖ ተሳካለት።
ዕለቱ አንድ ሁለት ማለት ጀመረ። ሊቆይ የወሰነበት የሶስት ቀን ገደብ ተጠናቆ ቀጣዮቹ ቀናት ተተኩ። ሀብታሙ እንደቀጠሮው ወደመጣበት አልተመለሰም። ሳምንትና አስራ አምስት ቀን፣ ወርና መንፈቅ ፣ ክረምትና በጋ ተራ በተራ ተፈራረቁ። ሀብታሙ ነገረ ዓለሙን ተወ። ቤት፣ህይወቱን ረሳ ። ራሱን ለጸሎትና ምልጃ አስገዝቶ በገዳሙ ቆየ። ለሶስት ቀን ያቀደው ጊዜ እንደዋዛ ዓመታትን ቆጠረ። አምስት ድፍን ዓመታት።
አንድ ቀን ሀብታሙ ካሸለበበት ዕንቅልፍ በድንገት ነቅቶ ተነሳ። ሁለቱም እግሮቹ አጋጣሚው ጥሩ አልሆነም። ሁለቱም እግሮቹ በድን ሆነው ነበር። በመጀመሪያው ተስፋ መቁረጥ ላይ ሌላ ሊቋቋመው ያልቻለ ተስፋ መቁረጥ ተደረበበት። ቀናት በትካዜና አንገት መድፋት አለፉ።
ወቅቱ የዓብይ ጾም መያዣ ነበር። በዚህ ጊዜ ከምዕመኑ የበዛ ጸሎትና ምልጃ ይኖራል። የሀብታሙ ውስጠትም መዳን መፈወስን እየተመኘ ነው። እሱ ዘንድ በየጊዜው የቅርብ ባልንጀሮች እየመጡ ይጎበኙታል። የዛን ቀንም እንደ ሁልጊዜው ጎብኝተውት መመለሳቸው ነበር። ዕለቱን ብሩህ፣ ደማቅ ጸሀይ ስፍራውን ስታሞቅ ውላለች። እነሱ ከሄዱ በኋላ ግን በአካባቢው ዝናብ ያካፋ ጀመር። ጥቂት ቆይቶም ሀይለኛ ዶፍ ያወርደው ያዘ።
ሀብታሙ ጸሎቱን አጠናቆ ቀና ከማለቱ ዶፉ በላዩ ይወርድ ጀመር። በዙሪያው ማንም የለም። ራሱን መከላከልና መጠበቅ አልተቻለውም። የዛን ቀን በዝናቡ የተደበደበው ማንም ከአጠገቡ ባለመኖሩ ነበር። እንዲያም ሆኖ ሀብታሙ አልተከፋም፣ አላዘነም። ‹‹በህይወት ላይ ሁን ያለው ይሆናል ሁን ያላለው ደግሞ አይሆንም›› ሲል ለውስጡ ነገረው።
ይህ ቃል አስገራሚ ብርታት ሆነለት። ‹‹ሁሉን ነገር መጋፈጥ፣መታገል ብችል ማሸነፍ እችላለሁ›› ሲል ራሱን አሳመነው። አፍታ አልቆየም። ዝናቡን በበረከት ተቀብሎ ለአዲስ ህይወት ተነሳሳ።ከዛን ዕለት ጀምሮ የማንነቱ ለውጥ ሲያንሰራራ፣ሲታደስ ተሰማው።
ዛሬ ሀብታሙ በታላቅ የለውጥ ጎዳና ላይ ራሱን አግኝቶታል። focus on Ablity በተሰኘው አራተኛው የፊልም ፌስቲቫል ላይ ተሳትፎም አሸናፊነትን ተጎናጽፏል። በአካል ጉዳተኞች ሕይወት ላይ በሚያተኩረው በዚህ አጭር ፊልም ውድድር ሀብታሙ Good View /መልካም እይታ/ በሚል ርዕስ የራሱን ታሪክና የህይወት ተሞክሮ አሳይቶበታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገሩን ወክሎ ባደረገው ውድድር ሀብታሙና ጓደኛው ፍሬዘር ያዘጋጁት አጭር ፊልም ተወዳጅና ትኩረት የሚስብ ሆኖ ተመርጧል።
ሀብታሙ በፊልሙ ላይ የነገውን ህልምና ስኬቱን በትክክል አስቀምጧል። እሱ ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉ የንግድና ቢዝነስ ሰዎች መካከል አንዱ ለመሆን ዕቅድ አለው። ይህን በማሳካቱም ለሀገሩና ፣ለወገኑ ታላቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይተማመናል።
በሀብታሙ እሳቤ አካል ጉዳተኝነት ለፈጣሪው የቀረበ፣ በሚሳተፍበት ተግባር ሁሉ ኃላፊነትን የሚወስድ ማለት ነው። በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ራሱን ማውጣትና ማሸነፍ የሚችል ብርቱና ጠንካራም ነው። በህይወት አጋጣሚው ደግሞ ሀብታሙ መዳንን በሁለት ከፍሎ ይለየዋል። ለእሱ የመጀመሪያው ድህነት ሰው ካለበት፣ ከቆየበት ውስጣዊና አካላዊ ህመሙ መፈወስ ሲችል ነው።
ሁለተኛው መዳን የሚለው ደግሞ አንድ ሰው በሽታው ሳያሸንፈው ህመሙን ታግሎና አሸንፎ ሲጥል እንደሆነ ያምናል። ስለዚህም ‹‹እኔ ድኛለሁ፣አሸናፊ ነኝ ››ሲል በሙሉ ልብ ይናገራል።ይህ እውነት የጠንካራውና ብርቱው ሀብታሙ በላይ የህይወት ተሞክሮ ነው። ሀብታሙ በአካል ጉዳተኝነቱ አንገቱን አይደፋም ፣አያዝንም። አንዳንዴ ስሙን በማንነቱ አሳምሮ ሊጠራው ሲሻ ‹‹የማይራመደው›› የሚል ቅጽል ያክልበታል። ‹‹የማይራመደው›› ።
ሰሞኑን በብሪትሽ ካውንስል ቅጥር ግቢ በተደረገው የአራተኛው Focus on Ability የፊልም ፌስቲቫል ላይ ዓለም አቀፍ ሽልማት ያገኙ ሌሎች ፊልሞች ጭምር ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ሀብታሙና ጓደኛው ረቂቅም በስፍራው ተገኝተው የማበረታቻ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።
ምሽቱን በብሪትሽ ካውንስል በተደረገው የፊልም ፌስቲቫል መርሀ ግብር በክብር እንግድነት የተገኙት በሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሴቶች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ ነበሩ። ርግበ አካል ጉዳተኛ መሪ ናቸው። ይህ እውነትም የአካል ጉዳትን ስሜት ከሌሎች የበለጠ እንዲያውቁት ምክንያት ሆኗል።
ኮሚሽነሯ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን ‹‹የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና እናጉላ›› በሚል መሪ ቃል ነውና ለጉዳዩ ትኩረት እንደሰጡት ይናገራሉ። እሳቸው የመሪነት ሚናቸው የጀመረው ግን ዛሬ ሳይሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ መሆኑን ይናገራሉ።
ርግበ አካል ጉዳተኞች ወደ መሪነት እንዳይመጡ መሰናክል የሚሆኑ የአስተሳሰብ፣ የአካባቢ፣ የአካላዊና ተቋማዊ ምክንያቶችን ማስወገድ ከእያንዳንዱ ወገን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ቁሳቁሶችና መገልገያዎች ለመጠበቅ ትኩረት እንዲሰጡና የሰዎችን ደህንነትና ፀጥታ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን›› ገልጿል።
በተያያዘ ዜናም፣ የእሥራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዴዎን ሳር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በፀጥታ ምክንያት በጣም የተወሰነ እርምጃ ብቻ መውሰዱን ገልጸዋል። ሚኒስትሩ አክለው እንደተናገሩት፤ እሥራኤል በሶሪያ ውስጣዊ ጉዳይ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትና የሚጨነቁት ዜጎቻቸውን ብቻ ለመከላከል እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ መከላከያ ሚኒስትሩ ካትዝ እንዳሉት የእሥራኤል ጦር ከባድ ስትራቴጂክ መሣሪያዎች፣ ሚሳይሎችን እና አየር መከላከያ ሲስተሞችን ጨምሮ ማውደሙን ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም