አዲስ አበባ፦ በቀጣይ ጥቃት አድርሶ እንደተፈለገ መኖር የማይቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አስታወቁ፡፡ ጥቃት አድራሾችን መመዝገብ የሚያስችል ዲጂታል የመረጃ ሥርዓት እየጎለበተ እንደሆነም ጠቆሙ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የሴቶችና የሕፃናት ጥቃት ከእለት ተእለት እጨመረ መጥቷል። ችግሩን ውጤታማ በሆነ መንገድ መከላከል የሚያስችል አስተማሪ ሕግ እየተረቀቀ ነው ብለዋል ።
በአሁኑ ሰአት ቀደም ሲል የነበረውን ሕግ ለማሻሻል፤ ሕጉን የመፈተሽ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረው፤ ማሻሻያው በቀደመው ሕግ ላይ የነበሩበትን ክፍተቶች በመለየት የመከላከሉን ሥራ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ጠንካራ ሕጎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡
የሕጉ መሻሻል ያስፈለገው በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸው ፣ጥቃቶቹ በምስክር ፊት የሚደረጉ አለመሆናቸው፣ ከዛም ባለፈ ጥቃቶች እየረቀቁ በመምጣታቸው እንደሆነ አስታውቀዋል። ችግሩ በፍርድ ሂደቱ ላይ ፈተና እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።
ችግሩን በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ፤ከሕግ ማሻሻያ ሥራው ጎን ለጎን ጥቃት አድራሾችን መመዝገብ የሚያስችል ዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን እየጎለበተ ይገኛል፡፡ ጥቃት አድራሾች ጥቃቱን ሲፈጽሙ መረጃቸው ተመዝግቦ ከዲጂታል መታወቂያ ሥርዓቱ ጋር እንዲያያዝ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርስን ሰው መረጃው ለማህበረሰቡ በቅርበት እንዲደርሰው በማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከዛም ባለፈ አንዳንድ አገልግሎቶችን እንዳያገኝ የማድረግ ሥራዎች የሚሠሩበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተናግረዋል፡፡
የሚለማው የዲጂታል ሥርዓት ጥቃት አድርሶ እንደተፈለገ መኖር እንደማይቻል እና ቀድሞ ማሰብ እንደሚገባ የሚያደርግ መተግበሪያ ነው። የማልማት ሥራውም ተጀምሯል፡፡ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም