ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ዶናልድ ትራምፕ ከውይይቱ በኋላ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። “በዩክሬን ጦርነት ብዙ ሰው ሞቷል፣ ብዙ ቤተሰብ ፈርሷል እስካሁን የሆነው በቂ ነው፣ ጦርነቱ ሊቆም ይገባል” ሲሉም ዶናልድ ትራምፕ ጽፈዋል።
በአሜሪካ ከአንድ ወር በፊት በተካሄደ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ በፓሪስ ታይተዋል። ተመራጩ ፕሬዚዳንት ወደ ፓሪስ የመጡት ከሦስት ዓመት በፊት የእሳት አደጋ የደረሰበት ዝነኛው ሮተርዳም ቤተ ክርስቲያን ታድሶ ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ለመታደም ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም ዶናልድ ትራምፕ፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የዩክሬኑ አቻቸው ቭላድሚር ዘለንስኪ የሦስትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
“ሩሲያ እና ዩክሬን የሠላም ስምምነት በቅርቡ እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፣ ይህ እብደት መቆም አለበት” ሲሉም ትራምፕ አክለዋል። ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው ዶናልድ ትራምፕ ስለ ሠላም የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀው ሠላም ለዩክሬን እና ለሩሲያ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ይህ የሦስትዮሽ ውይይት በተጠናቀቀ በሰዓታት ውስጥ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ የጦር መሣሪያ እርዳታ የመስጠት እቅድ እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም