በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላላቅ ስም ባላቸው የስፖርት ተቋማት ውስጥ ምርጥ ብቃታቸውን በማስመስከር ስማቸውን ከሚያስጠሩ ስፖርተኞች መካከል የሰርከስ ባለሙያዎች ተጠቃሽ ናቸው:: አስደማሚ በሆነ የሰውነት ቅልጥፍና የተመልካችን ቀልብ የመያዝ እንዲሁም አስደናቂ እንቅስቃሴዎችን በማሳየት እጅን አፍ ላይ የሚያስጭኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሰርከስ ስፖርተኞች አሉ:: በስፖርቱ ጠንክረው በመሥራት በከፍተኛ የስኬት ደረጃ በመድረስ አነጋጋሪ ከሆኑት መካከል አንዱ የሰርከስ ባለሙያው ተገኘ ወርቁ ነው::
ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ አለርት ሆስፒታል አካባቢ ነው። ወጣቱ የሰርከስ ጥበበኛ በታዳጊነት ዕድሜው ወደስፖርቱ ገብቶ በሂደት ብቃቱን በማዳበር አሁን ላይ በሰባቱም የዓለማችን አሕጉራት በመዘዋወር አስደናቂ የሰርከስ ትርዒት ከሚያሳዩ ምርጥ ባለሙያዎች መካከል ሊሰለፍ ችሏል:: በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ሻምፒዮናዎች ላይ አዲስ አበባ ከተማን በመወከል በጂምናስቲክ ስፖርት በርካታ ድሎችን አስመዝግቧል። በሩሲያ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔንና ሌሎችም ሀገራት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሸላሚ ሆኗል:: በዓለም ላይ ድንቃ ድንቅ ነገሮችን በማወዳደር በሚመዘግበው የጊነስ ቡክ ኦፍ ወርድ ደግሞ በሰርከስ ትርዒቶች ስሙን በተደጋጋሚ እስከማስፈር ከደረሱ ጥቂት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው::
ከተወዳዳሪነት ባለፈ በጂምናስቲክ ስፖርት የአሠልጣኝነትና የዳኝነት ሥልጠና በመውሰድ ራሱን ያበቃ እንዲሁም በኤሮቢክስ የአሠልጣኝነት ምስክር ወረቀት ያለው ጠንካራ ባለሙያም ነው:: አፍሪካን ድሪምስ የሚል መጠሪያ ካለው ቡድን ጋር በመሆንም በዓለም ላይ በግዝፈቱ በቀዳሚነት በሚጠቀሰው የካናዳው ሰርከስ ዱ ሶሊል ውስጥ የመሥራት ዕድል የገጠመው ሲሆን፤ በዚህ ወቅት ደግሞ በአሜሪካው ዩኒቨርሶል ሰርከስ ውስጥ በ32 የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ በመዘዋወር ትርዒቶቹን እያሳየ ይገኛል:: ወጣቱ የሰርከስ ባለሙያ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ሰፊ ተሞክሮና ልምዱን እንደሚከተለው አጋርቷል::
አዲስ ዘመን፡- ወደ ሰርከስ የገባህበት አጋጣሚ እንዴት ነበር?
ተገኘ፡- ተማሪ ሳለሁ የሰርከስ ትርዒት ለማሳየት ወደ አካባቢያችን የመጡ ወጣቶችን መመልከቴ ፍላጎት እንዲያሳድርብኝ አድርጎኛል:: በእርግጥ በልጅነት ሜዳ ላይ መገለባበጥ የተለመደ ነው፤ ነገር ግን ያየሁት በሥልጠና የዳበረ በመሆኑ መነሳሳትን ስላሳደረብኝ ስፍራውን በማጠያየቅ ልመዘገብና ልቀላቀል ቻልኩ:: ሰርከስ እንደየትኛውም ስፖርት በአካል ለመጠንከርና በአስተሳሰብ ንቁ ለመሆን የሚያግዝ ሲሆን፤ በታዳጊነት ዕድሜ ራስን ከማይገቡ ስፍራዎች ለመጠበቅ እንዲሁም ጓደኞችን ለማፍራት ከማገዙ ባለፈ በበርካታ ሃገራት እየተዘዋወሩ የመሥራትና በገቢ ራስን የመቻል ዕድልንም ይፈጥራል::
አዲስ ዘመን፡- ብዙ አይነት የሰርከስ አይነቶች አሉ። አንተ የምትሳተፍበት የሰርከስ ዓይነት የትኛው ነው?
ተገኘ፡- ሰርከስ በስሩ በርካታ ዘርፎች አሉት፤ እኔ የምሳተፍበት ደግሞ በቀለበት ላይ እየተገለበጡ ማለፍ (ሁፕ ዳይቪንግ)፣ ቋሚ ነገር ላይ መውጣት (ፖል ክላይምቢንግ)፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ቁሳቁሶችን አየር ላይ እየወረወሩ መቅለብና መቀባበል (ክለብ ጃግሊንግ) የመሳሰሉት ላይ ነው:: ይህም የሚሠራው በቡድን ሲሆን ትርዒት በምናሳይበት ወቅት ቁጥ ሩ ይጨምራል::
አዲስ ዘመን፡- ሰርከስን ከማዘውተር አልፈህ በትልቅ ደረጃ ለመወዳደር የበቃኸው እንዴት ነበር፣ መጀመሪያ ላይ የገጠመህስ ውጤት ምን ይመስል ነበር?
ተገኘ፡- የመጀመሪያ የውድድር ተሳትፎዬ በጂምናስቲክ ሲሆን፤ ኢትዮ-ሠላም በሚል ቡድን በውስጥ ከተወዳደርን በኋላ በክለብና በክፍለ ከተማ ደረጃ ከዚያም ከተማን እስከመወከል ሊደርስ ቻለ:: በዚህም አሁን በተቋረጠው መላ የኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ ሦስተኛው (በአዲስ አበባ፣ አዳማ እና ባሕርዳር) ድረስ አዲስ አበባ ከተማን ወክዬ በመሳተፍ በተከታታይ አሸናፊ ነበርኩ::
እንደሚታወቀው በአክሮባት ብቃት ያለው ሰው በቀላሉ ወደ ሰርከስ ለመግባት ይችላል:: ምክንያቱም ልዩነታቸው አክሮባት መሬት ላይ መገለባበጥ ሲሆን፤ ሰርከስ ደግሞ በተለያዩ ቁሳቁሶችን የሚያካትት በመሆኑ ነው:: እኔም አጀማመሬ በጂምናስቲክ ቢሆንም ወደ ሰርከስ ስገባ ተሳትፎው ዓለም አቀፍ ይሆናል፤ ፉክክሩም ከተለያዩ ሃገራት ከተወጣጡ ትልልቅ ሙያተኞች ጋር ነው:: እኔና ቡድኔ ከተካፈልንባቸው ታላላቅ ውድድሮች መካከል ቀዳሚው ኢንተርናሽናል ሰርከስ ፌስቲቫል ሲሆን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞስኮ ላይ በመሳተፍ ዲፕሎማ፣ በቀጣይ ፈረንሳይ ላይ ልዩ ተሸላሚ እንዲሁም በስፔን ደግሞ ፐብሊክ አዋርድ ተሸላሚ ሆነናል:: ውድድሮቹ እጅግ ፈታኝ ቢሆኑም ጠንክረን በመሥራታችን ስኬታማ ነበርን:: ከዚህ ባለፈ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ሆነን ከሌላ የሰርከስ ቡድን ጋር በመሆን በአሜሪካ በሚካሄደው የተሰጥዖ (አሜሪካስ ጋት ታለንት) ውድድር በመወዳደር እስከ ግማሽ ፍጻሜ መጓዝ ችለናል::
አዲስ ዘመን፡- ወደ ውጪ ሀገር ለውድድር የወጣኸው በምን አጋጣሚ ነበር፤ እዚያ ያለውን በኢትዮጵያ ካለው የሰርከስ እንቅስቃሴ አንጻር እንዴት አገኘኸው?
ተገኘ፡- ጣሊያን ሚላን ላይ የድንቃ ድንቅ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ወርልድ) ውድድር ይካሄድ ስለነበር በዚያ አጋጣሚ ነው ከቡድናችን ጋር ሆነን የሄድነው:: ይህ ውድድር ከሌሎቹ የሚለየው በየትኛውም ዘርፍ የሚደረግ የታለንት ውድድር በመሆኑ ሌሎች የማይሠሯቸውንና ሊያስደንቁ የሚችሉ ነገሮች ብቻ የሚታዩበት መድረክ ስለሆነ ለየት ያለ ፈጠራ ያስፈልገዋል:: እኛም ተሳክቶልን ለመመዝገብ በቅተናል:: እንደ ኢንተርናሽናል ሰርከስ ፌስቲቫል ያሉ የውድድር መድረኮች ደግሞ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር የሚያፎካክር በመሆኑ ፈታኝ ነው:: እኛ ይህንን በመሰሉ ውድድሮች ተፎካካሪ ብንሆንም ከሌሎች ተወዳዳሪዎች አንጻር ያለን ልዩነት ግን እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው:: እነሱ በቴክኖሎጂ ታግዘው የሚሠሩ እንደመሆኑ ስፖርቱን አሳድገውታል:: ከልጅነታቸው ጀምሮም እንደ አንድ የታለንት ዓይነት ፍላጎታቸው ላይ ተመሥርተው የሚጀምሩት ሲሆን፤ እያሳደጉት ሕይወታቸውን የሚመሩበት የሥራ ዘርፋቸውም ጭምር ነው:: በአንጻሩ በኢትዮጵያ ሰርከስ እንደ ትርፍ ሥራ ነው:: አብዛኛዎቻችን በጂምናስቲክ ጀምረን ነው ወደ ሰርከስ የምንገባው፣ በጎንም ትምህርትና ሌሎች የሚደግፉንን ሥራዎች አሉን:: ነገር ግን ሰርከስ ተሰጥዖ በመሆኑ በስፖርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱት እንደ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ አሜሪካ ካሉ ተወዳዳሪዎች ጋር በእኩል ተመዝነን ውጤታማ ለመሆን ችለናል:: እነሱ በቁሳቁስና በቴክኖሎጂ ቢበልጡንም በሰርከሱ ግን ክብራችንን እንዳስጠበቅን አለን::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ በርካቶች በሰርከስ ወደውጪ ሀገራት ይሄዳሉ፣ ይህ ዕድል በምን ምክንያት ሊሰፋ ቻለ?
ተገኘ፡- በፊት በየክልሉ ቅርንጫፎች ያሉት (ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ አዳማ፣…) ሰርከስ ኢትዮጵያ ነበር እንዲህ ዓይነት ተሳትፎ የሚያደርገው:: ስለዚህ ይህንን መሰል ዕድል ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። በአጋጣሚ የሄዱትም ቢሆኑ በጊዜው አጥጋቢ ክፍያ ስላልነበረ ከሄዱበት ሃገር አይመለሱም ነበር:: በአንድ ወቅት ግን በመንግሥት በኩል በቻይና ሃገር የሰርከስ ሥልጠና ዕድል በመመቻቸቱ የኔነህ ተስፋዬ እና ቢንያም ነጋሽ የተባሉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆኑበት፤ ከዚያም አፍሪካን ድሪም የተባለውን ሰርከስ ቡድን (እአአ በ2010) አቋቋሙ:: በዚህም ውስን የነበረው ዕድል ሊስፋፋና የሰርከስ ባለሙያዎች በስፋት ተሳታፊ ሊሆኑ፣ ወጣቶችም በስፖርቱ ያላቸው ሕልምና ተስፋም እውን ስለመሆኑ እኔ ምስክር ነኝ:: በዚህ ዕድል ምክንያትም ቀድሞ በልማድ ይሠራ የነበረውን ሰርከስ በማዘመን ጊዜውን መምሰል ተችሏል:: ስለዚህም በየትኛውም የዓለም ጥግ ተዘዋውሮ ለመሥራት በመቻሉና የኢትዮጵያውያን ተፈላጊነት በመጨመሩ ትልልቅ የሚባሉ የከርከስ ተቋማት ውስጥ የመሥራት ዕድል ይበልጥ እየሰፋ ይገኛል:: ሌላው ደግሞ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ መጨመሩ ነው:: ቀድሞ ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርት ብቻ እንዲያልፉ ያደርጉ ነበር፤ አሁን ግን ተሰጥዖንም ያማከለ እየሆነ በመምጣቱ ፍላጎትና ብቃት ያላቸው ወጣቶች ተፈጥረዋል::
አዲስ ዘመን፡- በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ወርልድ) ላይስ በተደጋጋሚ ስምህን ማስፈር የቻልከው እንዴት ነበር?
ተገኘ፡- የመጀመሪያው እአአ በ2011 ሲሆን፤ በቋሚ ብረቶች ላይ የሚሠራ የሰርከስ ዓይነት ቁጥር በማሻሻል የተገኘ ነበር:: ሁለተኛው ደግሞ እአአ በ2013 በራሳችን የተያዘውን የቀድሞው ክብረወሰን በማሻሻል የተገኘ ነው፤ ከ12 ወደ 19 በማሳደግ ማለት ነው:: ቀጣዮቹ ደግሞ ሦስት ሆነን በሚሽከረከሩ ቀለበቶች ውስጥ በአንድ ደቂቃ 15 ጊዜ በመዝለል እንዲሁም በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆቹ ዓመት ደግሞ በሚወዛወዝ ቋሚ ብረት ላይ በደቂቃ 27 ጊዜ በመገለባበጥ ሌላኛውን ክብረወሰን ማሳካት ችለናል::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ከየትኛው የሰርከስ ተቋም ወይም ቡድን ጋር እየሠራህ ትገኛለህ?
ተገኘ፡- እኔ ያለሁበት ቡድን መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገ አፍሪካን ድሪም ሰርከስ የሚባል ሲሆን፤ አሁን አሜሪካ ከሚገኘው ዩኒቨርሶል የተባለ ተቋም ጋር በተለያዩ ግዛቶች እየተዘዋወርን በመሥራት ላይ እንገኛለን:: ከተቋማቶቹ ጋር የምንሠራው በኮንትራት ለተወሰነ ጊዜ በመሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የመሥራት ዕድልን ይፈጥራል::
አዲስ ዘመን፡- አንተን ጨምሮ በሰርከስ ከፍተኛ ደረጃ የደረሳችሁ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ስፖርቱ እንዲያድግና እንዲዘምን ለማድረግ ምን ሠርታችኋል? ስፖርቱን ለማሳደግ ከማን ምን ይጠበቃል ትላለህ?
ተገኘ፡- የመጀመሪያው ነገር በሰርከስ መድረስ የሚቻልበትን የስኬት ጥግ በማሳየት አርዓያ መሆን ነው:: በስፖርቱ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ስናገኝ ደግሞ በምክርና ቪዲዮዎችን በማሳየት ጭምር ለማገዝ እንሞክራለን:: ቡድኑን መቀላቀል የሚፈልግ የትኛውንም ሰው የምናስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ ባለመኖሩ እኛም እየሠራን በማሠልጠን እናበቃቸዋለን:: ከዚህ ባለፈ ግን በመንግሥት በኩል በየስፍራው ሰርከስ የሚሠራባቸው ማዕከላትና ጂምናዚየሞችን መሥራት ቢቻል ወጣቶች ተሳታፊ ሆነው ስፖርቱ ካለው ከፍተኛ የሥራ ዕድል አንጻር ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ::
ተገኘ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ብርሃን ፈይሳ