የአምባጓሮ ውጤት

ተሰማ ታመነ ታደለ በደቡብ ክልል በወቅቱ ቦዲቲ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ አሎ ጎጥ ከአቶ ታመነ ታደለ እና ከአለቴ አይሳ በ1984 ዓ.ም ሲወለድ፤ እዚህ ይደርሳል ብሎ የገመተ አልነበረም:: አዲስ አበባ ሲገባ ቤተሰቦቹ በእጅጉ ሕይወታችንን ይቀይራል ብለው ተስፋ አድርገውት ነበር:: በልጅነቱ ድል በትግል 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን እስከ አምስተኛ ክፍል ሲከታተል ቆይቶ፤ ብዙም ሳይዝልቅ አቋረጠ::

ትምህርቱን ብዙም ባይቀጥልም አዲስ አበባ ውስጥ ዕድል ቀንቶት የባሕል ልብሶችን በመሸጥ ምርጥ ነጋዴ ሆኖ ትዳር መስርቶ ቤተሰቡን ማስተዳደር ጀመረ:: አንዳንዴ የሕይወት ስኬት በትምህርት ብቻ አይወሰንም ቢባልም፤ አለመማሩ ስሜቱን እንዳይቆጣጠር አድርጎት በመጨረሻም ሕይወቱ ተበላሸ::

የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆነው ተሰማ፣ ከጓደኞቹ ጋር መዝናናት ያበዛል:: በተለይ ደጉ ጮማ ስጋ እና ግሮሰሪ ቤት እየጠጣ መዝናናት መለያው ነው:: ገንዘብ ቢያገኝም ከማስቀመጥ ይልቅ እየተዝናና ያለውን ገንዝብ ይረጫል:: በወረሃ ጥቅምት ገበያው ደርቶ ከፍተኛ ገቢ ያገኝ የነበረው ተሰማ፤ እንደተለመደው ከጓደኞቹ ሳሬ ሳልፈቶ፣ ታሪኩ በቀለ እና መርካቶ አድነው አለሬ እንዲሁም ከደምመላሽ ዳታ ጋር አብረው እየጠጡ ሲጫወቱ ቀን ስምንት ሰዓት በግሮሰሪው የገቡ ምሽት አራት ሰዓት ሆነ::

ገና በጊዜ ወደ ስጋ ቤቱ የገቡት እነ ተሰማ፣ ሞቅ ብሏቸው ወደ ስካር አምርተዋል:: ነገር ግን ከምሽቱ አራት ሰዓት ቢሆንም ቤታቸው መግባት አልፈለጉም:: ስካር ነውረኛ ድርጊትን ከመፈፀም አልፎ፤ ሕይወትን እስከ ወዲያኛው የሚያበላሽ ድርጊትን ለመፈፀም እንደሚገፋፋ አልተረዱም:: ተሰማ፣ ቤተሰቡን ረስቶ እየጠጣ ሲያውካካ ከደጅ ፋሲካ እንግዳሰው የተባለ ሌላ ደንበኛ ወደ ግሮሰሪው ገባ::

ፋሲካ፣ እንደገባ የእነ ተሰማን ጓደኛ ደመላሽን ‹‹ አንተ ዶርዜ›› ሲል ሰደበው:: ሳሬ ተቆጣ፤ ፋሲካ ላይ እያፈጠጠ ‹‹ ለምን እንዲህ ብለህ ትሰድበዋለህ?›› ብሎ ተጠጋው:: ነገሩ ተባብሶ ሕይወት የመጠፋፋት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብሎ ያልገመተው ፋሲካ፤ ‹‹ እኛ ጓደኛሞች ነን፤ ለምን በእኛ መሃል ትገባለህ?›› ብሎ ፋሲካ ለሳሬ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት::

ተሰድቦ ሁኔታውን ችላ ብሎ ያለፈው ደመላሽ የጠጣውን ለማስወጣት ወደ መፀዳጃ ቤት ሔደ:: ሳሬ ጓደኛው መሰደቡ ቆጭቶታል:: ፋሲካ ችላ ቢለውም እርሱ ግን ነገር ነገር አለው:: መጠጡም እየገፋፋው ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት ወደ ፋሲካ ቡጢ ሰነዘረ:: ሁለቱም ተያያዙ፤ የሳሬ ጓደኞች ተነስተው የቢራ ጠርሙስ እና ብርጭቆ መወራወር ጀመሩ:: ተሰማ ቤተሰቡን ረስቶ ከእርሱ ጋር አብረው በነበሩ ጓደኞቹ መካከል ፀብ ሲነሳ፤ የቢራ ጠርሙስ እና ብርጭቆ ከመወራወር ያለፈ ከባድ ድርጊት ፈፀመ::

ተሰማ ዘሎ በግሮሰሪው ባንኮኒ ውስጥ ለሎሚ መቁረጫ ተቀምጦ የነበረውን ቢላዋ አንስቶ፤ ፋሲካ እንግዳሰውን መውጋት ጀመረ:: በስካር ውስጥ የነበረው ተሰማ የያዘውን ቢላዋ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ መሰንዘር ቀጠለ:: የሕክምና ማስረጃው እንዳረጋገጠው ፋሲካ በተሰማ የቀኝ ደረቱ፣ የቀኝ ሆዱ፣ የግራ አንገቱ እንዲሁም የግራ ጭኑ ተወጋ:: ፋሲካን በቢላዋ የወጋው ተሰማ፤ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ላይ እንደገለፀው፤ ደጋግሞ መውጋቱን እንጂ በየትኛው የፋሲካ የሰውነት ክፍል ላይ እንደሰነዘረ አያስታውስም::

ሁለተኛውና የፀቡ አነሳሽ ሳሬ ሳልፈቶም በ1980 ዓ.ም የተወለደ ሲሆን፤ እርሱም በተመሳሳይ መልኩ ከደቡብ ክልል ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሥራ ጀምሯል:: የካ ክፍለ ከተማ የሚኖረው ሳሬ፣ ፋሲካን በቦክስ ከመምታት አልፎ የቢራ ጠርሙስ ወርውሮበታል::

ሌላኛው በ1973 ዓ.ም አዲስ አበባ የተወለደው እና እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምሕርቱን የተከታተለው ታሪኩ በቀለም፤ በተመሳሳይ መልኩ የቢራ ጠርሙስ እና ብርጭቆ ወርውሯል:: ይህ ሁሉ ሲሆን ተሰዳቢው ደመላሽ ግን ስድቡን ከቀመሰ በኋላ ወደ መፀዳጃ ቤት ሔዷል::

ደመላሽ ከመፀዳጃ ቤት ሲመለስ ግሮሰሪው በብርጭቆ እና በቢራ ጠርሙስ ስብርባሪ ተሞልቶ ፋሲካ መሬት ላይ ወድቆ ደሙ እየፈሰሰ ነበር:: አብሮ ከእነ ተሰማ ጋር ሲጠጣ የነበረው ታደሰ ካቡሬ ግን ከመመልከት ውጪ ሚና አልነበረውም:: በመጨረሻም የቢራ ጠርሙስ ስባሪ እና ብርጭቆ ሲወረወርበት እንዲሁም በስለት ሲወጋ የነበረው ፋሲካ የሚያግዝለት፤ ተከላክሎ በፍጥነት ሕክምና ቦታ የሚያደርሰው በማጣቱ ሕይወቱ አለፈ::

ወንጀል መፈፀሙን መረጃ የደረሰው የፖሊስ ምርመራ ቡድን ተጎጂውን ሃኪም ቤት ከመውሰድ አልፎ የወንጀል ድርጊቱን ማን እንደፈፀመው ማጣራት ጀመረ:: ድርጊቱን የፈፀሙት እነ ተሰማ ፋሲካ ላይ ከባድ ጉዳት ካስከተሉ በኋላ ሁሉም ጠፍተው ነበር:: ሆኖም የፖሊስ ምርመራ ቡድን ከፍተኛ ክትትል በማድረግ የወንጀል ድርጊት የፈፀሙትን በሙሉ በቁጥጥር ሥር አዋላቸው::

የፖሊስ ምርመራ ቡድኑ ወንጀሉ መፈፀሙን የሚያመለክቱ መረጃዎችን በሙሉ አደራጅቶ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት አቀረበ:: ከምርመራ ቡድኑ የተደራጀ መረጃ ያገኘው ዐቃቤ ሕግም የወንጀል ድርጊቱን በዝርዝር ለፍርድ ቤት አቀረበ::

የወንጀሉ ዝርዝር

ተከሳሽ ነዋሪነታቸው የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የሆኑት ተሰማ ታመነ ታደገ፣ ሳሬ አልፈቶ፣ ታሪኩ በቀለ እንዲሁም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪነቱን ያደረገው መርካቶ አድነው በተጠረጠሩበት ወንጀል ከሳሽ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ሆኖ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አደረገ::

ክሱ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32(1) (ሀ)፣ 35 እና 577 (3) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ መሆኑን የወንጀል ዝርዝሩ ላይ በግልፅ ተቀምጧል::

ተከሳሾች ጥቃትን ለመመለስ ራስን ወይም ሌላውን ለመከላከል ወይም ጠበኞችን ለመገላገል በማሰብ ሳይሆን፤ በሰኔ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት አራት ሰዓት ከሰላሳ፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ደጉ ስጋ ቤት እና ግሮሰሪ ውስጥ ደመላሽ ዳታ የሚባለው አንደኛው መስካሪ ወደ ግሮሰሪው ውስጥ ሲገባ ሟች ፋሲካ እንግዳሰው ምስክሩን ደመላሽን ስለሚተዋወቁ በቀልድ መልክ ‹‹ አንተ ዶርዜ›› በሚል ይሰድበዋል::

ሁለተኛ ተከሳሽ ማለትም ሳሬ ሳልፈቶ ‹‹ለምን እንደዚህ ብለህ ትሰድበዋለህ?›› ሲለው፤ ‹‹ ጓደኛሞች ነን ለምን በእኛ መሃል ትገባለህ›› የሚል ጥያቄ ሟች ፋሲካ እንግዳሰው አቀረበ:: ተከሳሽ ሟች ላይ ቦክስ ሰንዝሮ ሲመታው ተያያዙ:: ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር አብረው መጠጥ ሲጠጡ የነበሩት 1ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ማለትም ተሰማ ታመነ፣ ታሪኩ በቀለ እና መርካቶ አድነው የቢራ ጠርሙስ እና ብርጭቆ በመወርወር ሟችን የተለያዩ የሰውነት ክፍሉን መትተውታል::

አንደኛ ተከሳሽ ተሰማ ታመነ በድጋሚ በስለት ሟችን የቀኝ ደረቱን ፣ የቀኝ ሆዱን፣ የግራ አንገቱን እንዲሁም የግራ ጭኑን በመውጋት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል:: በመሆኑም በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆኑ በፈፀመው የአምቧጓሮ ወንጀል እርሱ እና ግብርአበሮቹ ተከሰዋል::

ሁለተኛው ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ ሲሆን፤ ወንጀሉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 539(1)(ሀ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ነው:: ተከሳሽ ሰውን ለመግደል በማሰብ በሰኔ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ደጉ ስጋ ቤት አካባቢ በተነሳ ፀብ ምክንያት ተከሳሹ ከእነ ግብርአበሮቹ ለሎሚ መቁረጫነት አገልግሎት የሚውል የነበረውን ቢላዋ የግሮሰሪው ባንኮኒ ውስጥ ዘሎ ገብቶ በመውሰድ ጨካኝነቱን እና ነውረኛነቱን በሚያሳይ ሁኔታ የሟችን ወሳኝ አካላት ወግቷል::

የቀኝ ደረቱን በስተጀርባ የግራ ደረቱን፣ የቀኝ ሆዱን፣ በግራ በኩል አንገቱን እና ጭኑን ደጋግሞ በስለት በመውጋት ሕይወቱ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ ከባድ የግድያ ወንጀል ፈፅሟል ሲል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቷል::

የማስረጃ ዝርዝር

ክሱ ሲመሠረት የተለያዩ ማስረጃዎች የቀረቡ ሲሆን፤ አስራ አራት የሰው ምስክሮች ቀርበው ግድያው መፈፀሙን እና በምን መልኩ እንደተፈፀመ ምስክርነት ሰጥተዋል :: በተጨማሪ የሰነድ ማስረጃም ቀርቦ በፍርድ ቤቱ ታይቷል:: ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል የሕክምና ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥር ጳሀ8/4820 የተላከ የአስክሬን ምርመራ ውጤትም በማስረጃነት ቀርቧል::

የካቲት 12 ሆስፒታል በሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ሟች ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያመለክት የሕክምና ማስረጃም ቀርቧል:: በተጨማሪ የሟችን ማንነትና የደረሰበትን ጉዳት የሚየሳይ 31 ፎቶግራፍም ለፍርድ ቤት ቀርቧል::

ውሳኔ

ተከሳሽ ተሰማ ታመነ ታደሰ፣ በተከሰሰበት ወንጀል ጉዳይ በክርክር ላይ የነበረና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የነበረው ክርክር መቋጫ አግኝቶ በሕዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ተሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ድርጊት ፈፃሚዎቹን ያርማል ሌሎችን ያስተምራል በሚል በሰጠው ውሳኔ አንደኛ ተከሳሽ ማለትም ተሰማ ታመነ በአስር ዓመት ፅኑ እስራት፤ 2ኛ ተከሳሽ ሳሬ ሳልፈቶ በአስር ዓመት ፅኑ እስራት፤ እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ ታሪኩ በቀለ በአስር ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት በተጨማሪ 4ኛ ተከሳሽ በነፃ ይሰናበት ሲል ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You