አዲስ አበባ፡- የሕዝቡ ስቃይ እንዲያበቃና ሀገር ሰላም እንዲሆን የሰላምን መንገድ መምረጣቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የቀድሞው ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ ገለጹ። የሰላም ስምምነቱ በሰላም እጦት ለተሰቃየው ሕዝብ እፎይታን እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡
ጃል ሰኚ ነጋሳ የሰላም ስምምነቱን አስመልክተው ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ሕዝቡ እርስ በእርስ በተፈጠረው ግጭት ብዙ ችግር አሳልፏል። በሰላም እጦት ተጎጂ የሆነው ሕዝብ ስቃይ እንዲያበቃ የሰላምን መንገድ መርጠናል፡፡
ሕዝቡ እርስ በእርስ ግጭት ሲሰቃይ ቆይቷል ያሉት ጃል ሰኚ፤ በቡድኑ መካከል በሚደረጉ ግጭቶች በገጠርና በጠረፍ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ጥፋት አድርሷል ብለዋል።
ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣው ችግር የሰላም አማራጭ እንዲመርጡ ማድረጉን ጠቅሰው፤ በክልሉ ያለው ሁኔታ በጦር ሜዳ መፍትሔ እንደማያገኝ መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሕዝቡ ላይ እየተሠራ ያለውን ግፍ ከሕዝቡ መረዳት ይቻላል ያሉት ጃል ሰኚ፤ ሕዝቡ በማያገባው ጉዳይ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው ብለዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ለሕዝቡ እፎይታን እንደሚያስገኘ ገልጸው፤ ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡና ለተግባራዊነቱም ሦስት ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሕዝብ ከጦርነት ይልቅ ከሰላም አትራፊ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት የሰለጠነ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱን አስመልክተው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጩ ያሉ አሉባልታዎች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን የገለጹት ጃል ሰኚ፤ የሰላም አማራጭን የወሰዱት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስና ሰላምን በመምረጣችን ነው ብለዋል፡፡
አሁን ወደ ካምፕ እየገባ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሆኑን ጠቅሰው፤ አሉባልታውን ከሚያሰራጩት አካላትም እንዴት ወደ ሰላም መመለስ እንደሚችሉ ጥያቄ እየቀረበላቸው መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በጋራ መልሶ መገንባት እና ቅራኔ የተፈጠሩባቸውን አካባቢዎችም ማስታረቅ የስምምነቱ አካል መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በሰሞኑ ቆይታቸውም በአዲስ አበባ እና በተለያዩ አካባቢዎች የተሠሩ የልማት ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸውን ያነሱት ጃል ሰኚ፤ የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች መልካም መሆናቸውን እና ከዚህ በተሻለ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመግለጫውም ሌሎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች የተገኙ ሲሆን፤ ባለፈው እሁድ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራር በነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም