በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ የጉንፋን ምልክቶች ባሉት አዲስ በሽታ ምክንያት ቢያንስ 79 ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር የጤና ሚኒስቴር እንዳለው ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 18 ያሉ ታዳጊዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ትኩሳት፣ የራስ ምታት፣ ሳል፣ ለመተንፈስ መቸገር፣ ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ እና የደም ማነስ የበሽታው ምልክቶች ሲሆኑ፣ እስካሁን ከ300 በላይ ሰዎች እነዚህን ምልክቶች ማሳየታቸው ታውቋል። የሕክምና ባለሙያዎች በሽታው በስፋት ታይቶበታል ወደ ተባለው ክዋንጎ ግዛት አምርተው የበሽታውን ባህሪ እና ህመምተኞችን እየመረመሩ ይገኛሉ።
ሴፎሪዬን ማንዛንዛ የተባሉ የሲቪል ማኅበረሰብ መሪ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ ሁኔታው አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። “ፓንዚ ገጠራማ የጤና ዞን ነው። በዚህ ምክንያት የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት አለ” ሲል ግለሰቡ ተናግሯል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ቢሮ ባለሥልጣን “ወደ ሥፍራው አንድ ቡድን ልከን ናሙና ሰብስቦ በቤተ-ሙከራ ምርመራ ለማድረግ አቅደናል” ሲሉ ተናግረዋል። የአካባቢው ባለሥልጣናት ማኅበረሰቡ ሁኔታዎችን በእርጋታ እና በንቃት እንዲጠባበቅ አሳስበዋል።
በሥፍራው የሚገኙ ነዋሪዎች እጃቸውን በሳሙና እንዲታጠቡ፣ በጋር ከመሰባሰብ እንዲቆጠቡ እና የሟቾችን አስከሬን ብቁ ከሆኑ የጤና ባለሙያዎች ፈቃድ ውጪ እንዳይነኩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።
የአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 10 እስከ 26 ቀን 2024 ባለው ጊዜ 67 ሰዎች በበሽታው ምክንያት መሞታቸውን ተናግረዋል።
“የፓንዚ ሆስፒታሎች በመድኃኒት እጥረት ሳቢያ ወረርሽኙን ማስቆም አልቻሉም። በፍጥነት እርዳታ ያስፈልገናል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ከዚህ አዲስ ወረርሽኝ በተጨማሪ በኤምፖክስ ወረርሽኝ ምክንያት አደጋ ላይ ወድቃለች። ካለፈው ዓመት ጥር እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ 14 ሺህ 500 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል።
አዳዲስ በሽታዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱባት ዲሞክራቲክ ኮንጎ በኢቦላ ቫይረስ ሳቢያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ብዙ ፈተናዎችን አልፋለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም