– እስከአሁን 125 ሺህ ኩንታን በርበሬ ተሠብስቧል
አዲስ አበባ፡- በምርት ዘመኑ ከለማው 26 ሺህ 116 ሄክታር መሬት 346 ሺህ ኩንታል በርበሬ ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑን ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡና እና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ እስከ አሁን ድረስ 125 ሺ ኩንታን በርበሬ መሰብሰቡን አመልክቷል፡፡
በማዕካዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡና እና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቶፊቅ ጁሃር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በዘንድሮ የምርት ዘመን በክልሉ ባሉ ዞኖች ሁሉ በርበሬን በስፋት ለማምረት እቅድ ተይዞ ተሠርቷል፡፡ በዚህም 28 ሺህ 467 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ የ26 ሺህ 116 ሄክታር መሬት ለምቷል፡፡ ይህም የእቅዱን 98 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡
በምርት ዘመኑ በዋናነት ስልጤ፣ ሃላባ ፣ ምስራቅ ጉራጌ በከፊልና ማረቆ አካባቢዎች የበርበሬ ክላስተር ተብለው የተለዩ አካባቢዎች መሆናቸወን አንስተው፤ ‹‹ዘንድሮ የበርበሬን ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጎ በመሠራቱ ሃላባ ሰባት ሺህ ሄክታር ፤ ስልጤ ስምንት ሺህ 800፤ ምስራቅ ጉራጌ ሶስት ሺህ 200 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል›› ብለዋል፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በበርበሬ እምብዛም በማይታወቁ በጉራጌ፤ ሃድያና ከንባታ ዞኖች ላይ በስፋት እንዲለማ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
‹‹የዘንድሮ ምርት ካለፉት ዓመታት ከነበረው ተሞክሮ አንፃር በተሻለ መልኩ ምርታማነት ጨምሯል›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም በተለይም ምርታማነትን ሊቀንሱ የሚችሉ የበርበሬ በሽታዎችን፣ ተባይና አረሞችን የመከላከል እንዲሁም የማሳ እንክብካቤ ሥራዎች በስፋት መሠራታቸውን አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቆላና ወይና ደጋ የክልሉ አካባቢዎች ከተመረተው ምርት 125 ሺህ ኩንታን ያህሉን መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የኤክስቴሽን ሥርዓቱን በመጠቀምና ከልማት ጣቢያ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት በቅድመ ሆነ በድህረ ምርት ወቅት የሚያጋጥሙ ብክነቶችን ማስቀረት በሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ቤት ለቤት በመዘዋወርና በማሳ ላይ መሠራታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ገበያዎች በርበሬ በ400 ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በገበያው ላይ ያልተገባ ንረት በሚፈጥሩ ደላሎችና የተንዛዙ አሠራሮችን ለማስቀረት ከሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹ዘንድሮ በተቻለ መጠን ግብይቱ በህብረት ሥራ አማካኝነት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ከተደረገባቸው አካባቢዎች ደግሞ ሃላባ፤ ሥልጤና ጉራጌ ላይ የህብረት ሥራ ዩኒየኖች ከአርሶ አደሩ በርበሬ ገዝተው እንዲያከፋፍሉ ውል ተፈፅሟል›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩልም ከአርሷ አደሩ ጋር በመቀናጀት ዛላውንም ሆነ እሴት ጨምረው ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚልኩ ነጋዴዎች ቁጥር መጨመሩን አመልክተው፤ ባለፈው የምርት ዘመን ክልሉ ለውጭ ገበያ ባቀረበው የበርበሬ ምርት ሰባት ሚሊዮን ዶላር ማስገባት መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
ዘንድሮ ደግሞ ምርቱንም ሆነ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለመጨመር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ‹‹በተለየ ሁኔታ ዩኒየኖች በወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ በግብይት ማዕከላት ጭምር በርበሬ እየገባ ሥራቱን የጠበቀ ግብይት እንዲከናወንና ገበያ የማፈላለግ ሥራ ተሠርቷል›› ብለዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም