“ብልፅግና ፓርቲ በአምስት ዓመታት አስደማሚ ሁለንተናዊ ስኬቶችን አስመዝግቧል” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፡- ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች አስደማሚ ሁለንተናዊ ስኬቶችን አስመዝግቧል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ሀገራዊ ማጠቃለያ መርሐ ግብር በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ትናንት ሲካሄድ እንዳሉት፤ ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመተግበር፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በፍትህና ጸጥታ ተቋማት፣ በዲፕሎማሲና በኢንዱስትሪ ሪፎርሞች ካመጣቸው ስኬቶች ጎን ለጎን በበጋ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኮሪደር ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በጽዱ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አስደማሚ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን የብልፅግና ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ፈርጀ ብዙ ሥራዎች ተተግብረው የሚታይ ውጤትና ፍሬ ማምጣት ጀምረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፓርቲው ኢትዮጵያን የላቀ ከፍታ ላይ ለማድረስ ሙሉ ዕይታ ይዞ በሁሉም ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ብልፅግና እንደ ማንኛውም የፓርቲ ስም ሳይሆን ብልፅግና የልብ መሻታችንን ለሕዝባችን የምንገልጽበት ስያሜ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ስያሜ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በድህነት አረንቋ ለተዘፈቁ ሀገራት ስም ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ሁሉ የወል እውነት ነው ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ችግር መውጣት የማይሻ ኢትዮጵያዊ የለም ነው ያሉት፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ህልሙንና ራዕዩን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ሲችል ከብልፅግና የሚጎድል ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር ገልጸው፤ በብዛት መንገዶች ቢገነቡ፣ ከተሞች ቢዘምኑ፣ የግብርናው ምርታማነት ቢጨምር፣ ኢንዱስትሪው ቢስፋፋና ሌሎች ዘርፎች ቢያድጉ ከብልፅግና የማይጠቀም ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ጉዞ ፓርቲው እውቀት፣ ጥበብና እውነትን ባይሰንቅ ኖሮ በቀላሉ የማይታለፉ ችግሮች አጋጥመውት እንደነበር አውስተው፤ ብልፅግና ፓርቲ እነዚህን ችግሮች በጽናት በመቋቋም ጥበቡን ተጠቅሞ ወደ ዕድል እንደቀየራቸው አመልክተዋል፡፡

ብልፅግና ሙሉዕ ዕይታ ያለው ፓርቲ ነው። ቅድሚያ ግብርና፣ ቅድሚያ ከተማ፣ ቅድሚያ ኢንዱስትሪ አይልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ፓርቲው በአንድ ጊዜ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪን፣ ቴክኖሎጂ፣ ከተማን፣ ገጠርን፣ ዲፕሎማሲንና ሌሎች ዘርፎችን አስተሳስሮ መምራት የሚሻና የሚችል መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል፡፡

የሌሎችን ሀገራት የፖለቲካ ሥርዓት ሙሉውን መቅዳት፣ ኃይልና ሃሳብን መቀላቀል፣ ዲሞክራሲያዊነት አለመኖር፣ የወዳጅና የጠላት ፖለቲካ ማራመድና አካታችነት ጉድለት ያለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብራቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ብልፅግና ፓርቲ ከእነዚህ ስብራቶች ትምህርት በመውሰድ አዲስ ሀገራዊ የፖለቲካ እሳቤን ተግባራዊ ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም ብዙ ስኬቶች ማስመዝገብና ተግዳሮቶችን ማለፍና ወደ ድል መቀየር እንደቻለ አብራርተዋል፡፡

መዳረሻችን ሁለተኛዊ ብልፅግና፣ መንገዳችን መደመር፣ ገዥ ትርክታችን ህብረ ብሔራዊነት፣ ማሳለጫችን ምክክር፣ትብብር፣ ቅንጅት፣ አጋርነት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ነው ያሉት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ የታሪክ እጥፋት የተመዘገበበት መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡

ፈተናን ወደ ድል መቀየር የብልፅግና ፓርቲ ተጨባጭ መገለጫዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ፓርቲው በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም እነዚህን ፈተናዎች ወደ ድል በመቀየር አንጸባራቂ ውጤቶች ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

የትግላችን መዳረሻ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ቃልን በተግባር መፈጸም የብልፅግና ፓርቲ ተጨባጭ መለያዎች ናቸው ብለዋል።

በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፤ “በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ ውጤቶቻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል።

ጌትነት ምህረቴ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You