ትርጉም ያለው ግንኙነት ለመገንባት

ፈጣን በሆነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ትርጉም ያለው ግንኙነት መገንባት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። መልካም ግንኙነት ለሕይወታችን፣ ዓላማችን ግብ መምታት፣ ለደስታ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማግኘት እድል ይሰጣል። በቤተሰብ አባላት መካከል ያለው ትስስር፣ ከጓደኞች ጋር ያለው እምነት፣ ወይም ከሥራ ባልደረቦች ጋር የገነባነው ግንኙነት ማንነታችንን ይቀርጹታል። በተጨማሪ የሕይወት ውጣ ውረዶችን የምንፈታበት ብስል አዕምሮ እንድናዳብር ይረዳናል።

በእያንዳንዱ ትርጉም ያለው ግንኙነት ውስጥ ሶስት አስፈላጊ ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ‹‹መተማመን›› ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹መግባባት›› ነው። የመጨረሻውና ሶስተኛው ቁልፍ የግንኙነት መሠረት ‹‹መከባበር›› ነው። እነዚህን ባሕርያት ማዳበር እና ግንኙነቶችን ማሳደግ ጊዜ፣ ትዕግስት እና ጥረት ይጠይቃል።

መተማመን

መተማመን የማንኛውም ጠንካራ ግንኙነት መሠረት ነው። ሰዎች አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እምነትን ማግኘታቸው ደህንነት እንዲሰማቸው የሚፈቅድላቸው ቁልፍ የግንኙነት መሠረት ነው። እምነት ከሌለ ግንኙነቶቹ ደካማ ይሆናል። በርግጠኝነት በሁለቱ አካላት (በቤተሰቦች መካከል፣ በባለ ትዳሮችና በጓደኞች መካከል) በማይታወቅ ጥርጣሬ የተሞላ ግንኙነት ይፈጠራል። መተማመንን መገንባት የሚጀምረው ግንኙነት ለፈጠርንለት ወገን ታማኝነትን በማሳየት ነው። ሁልጊዜ እውነት መናገር አስቸጋሪ ቢሆንም ግንኙነቱን ግልጽነት የሰፈነበት ለመሆን በቂ ዋጋ መስጠት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ስህተት ከሰራህ ከመደበቅ ይልቅ አምኖ መቀበል ታማኝነትህን ያሳያል።

ቃል ኪዳኖችን መጠበቅ ሌላው የመተማመን አስፈላጊ አካል ነው። የኛ የምንላቸው ሰዎች የሆነ ነገር ሲፈጽሙ (በቤተሰብ ዝግጅት ላይ መገኘትም ሆነ ጓደኛን በጀመረው ፕሮጀክት ዙሪያ) አጋርነታችንን ማሳየት ከሆነ፤ ልንረዳቸው ቃል ከገባን ያንን መፈፀም በመካከላችን ያለውን መተማመን በእጅጉ ይገነባዋል። መተማመን የበለጠ የሚጠነክረው ወጥነት ያለው ባህሪና ድርጊትን በማሳየት ነው። በደስታም፣ በሀዘንም እንዲሁም በሁሉም አጋጣሚዎች ተመሳሳይ ባህሪን ማሳየት ዘላቂ ግንኙነት ለመፍጠር መሠረት ይጥላል። አንድ የሥራ ባልደረባህን ደጋግሞ ርዳታ ጠይቆህ ዛሬ ነገ እያልክ ቃልህን የማታከብር ከሆነ በርግጠኝነት በመካከላችሁ መተማመን ይሸረሽራል። በጊዜ ሂደት ተግባሮችህ የእሱን እምነት ስለሚሸረሽሩ በአንተ ላይ አመኔታን ለመጣል አስቸጋሪ ያደርግበታል። በአንጻሩ ደግሞ በአስቸጋሪ ጊዜያት ያለማቋረጥ የሚደግፍ ጓደኛ በታማኝነት ረገድ መልካም ስም ይገነባል።

መግባባት

መግባባት ጠንካራ ግንኙነቶችን ለመፍጠር ከመተማመን እኩል አስፈላጊ ነው። ማውራት ብቻ ሳይሆን መደማመጥና መረዳትም ጭምር የመግባባት ቁልፍ መሠረቶች ናቸው። ብዙዎቹ አለመግባባቶች የሚፈጠሩት በመጥፎ ግንኙነት ወቅት ነው። ንቁ ሆኖ ማዳመጥ፣ ሌላው ሰው በሚናገረው ላይ ሙሉ በሙሉ ማተኮርና ሁኔታዎችን ለመገንዘብ መሞከር፣ በመረዳት ውስጥ የተፈጠሩትን ክፍተቶችን ለማስተካከል ይረዳል። ባላጋራችሁን ሳታቋርጡ ወይም በሚናገረው ጉዳይ ላይ ሳትፈርዱ ስታዳምጡ ያን ጊዜ የእነርሱም ሃሳብና ስሜታቸው አስፈላጊ መሆኑን ልትረዱ ትችላላችሁ።

አለመግባባትን ለመቅረፍና ወደ መግባባት ለማምጣት ሃሳብን የመግለጽ ችሎታም እንዲሁ አስፈላጊ ነው። ግልጽ የሆኑ ቃላትን መጠቀም ለትርጉም እንዳንጋለጥ ያደርገናል። ሃሳባችንን እና ስሜቶቻችንን ሌሎች ሊረዱት በሚችሉበት መንገድ መግለጽ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ‹‹ተናድጃለሁ›› ከማለት ይልቅ፣ ‹‹በሁኔታው መበላሸት ቅር ተሰኝቻለሁ›› ብሎ ማስረዳት በግንኙነቱ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማርገብ ይጠቅማል። ይህ ግልጽነት ግራ መጋባትን ይከላከላል እና ሌሎች በትክክል ምላሽ እንዲሰጡም ያስችላቸዋል። ትዕግስት የግንኙነት ቁልፍ ገጽታም ነው። ሁሉም ሰው በተመሳሳይ መንገድ ወይም ፍጥነት አይግባባም። ስለዚህ ለሰዎች ጊዜ መስጠት የጋራ መግባባትን ያመጣል።

እርስ በእርስ መከባበር

እርስ በእርስ መከባበር ትርጉም ላለው ግንኙነት ሦስተኛውና ዋነኛው ምሰሶ ነው። ሌሎችን ማክበር ማለት አስተያየታቸውን፣ ድንበራቸውን እና ግላዊነታቸውን መገምገምና ያንን ፍላጎታቸውን ማክበር ማለት ነው። ሁለቱም ወገኖች በማንነታቸው ሲታዩ እና ሲመሰገኑ ግንኙነቶቹ ይበለጽጋሉ። ልዩነትን መቀበል ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም ሰዎች አንድ ዓይነት አይደሉም። ለምሳሌ፣ ጓደኛህ የማትጋራው የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ወይም እምነት ሊኖር ይችላል። ይህንን ምርጫዋን (ምርጫውን) ማክበር በግለሰብ ደረጃ በመካከላችሁ መከባበር መኖሩንና እንድምትቻቻሉ የሚያሳይ ቁልፍ አጋጣሚ ነው።

የአንድን ሰው ፍላጎቶች የሚጥሱ ድንበሮችን ማወቅ አሊያ ለራስ ማዘጋጀት እና ያንንም ማክበር ሊመጣ የሚችልን ቅራኔ ከወዲሁ ለመቅጨት ይረዳል። ለምሳሌ አንድ የቤተሰብ አባል በአስቸጋሪ ጊዜ ሆኖ ችግሩን በራሱ ለማጤን አሊያም ለመፍታት ግላዊነትን ከጠየቀ እርሱን ማክበር ያስፈልጋል። ከዚህ በተቃራኒው ሆኖ ወደ ዝርዝር ውስጥ መግባትና ማስጨነቅ ግንኙነትን ያበላሻል። የሚበጀው አማራጭ ወደማይፈልገው አቅጣጫ ከመግፋት ይልቅ ጥያቄውንና ያበጀውን ድንበር ማክበር ለዚያ ሰው እንደምናስብ እንዲሁም እንክብካቤ እንዳደረግንለት እንዲያስብ ያደርገዋል።

ሌላው የመከባበር ማሳያ፤ ቤተሰቦቻችን፣ የፍቅር አጋራችን፣ ጓደኞቻቸን ላደረጉልን መልካም ነገር እውቅናን መስጠት አንዱ ነው። ‹‹አመሰግናለሁ›› ማለት ወይም የአንድን ሰው ጥረት እውቅና መስጠት ያሉ ትናንሽ የምስጋና ተግባራት ሰዎች የተከበሩ እንደሆኑ እንዲሰማቸው በማድረግ በጋራ ግንኙነቱ ረጅም ርቀት እንዲጓዝ ያደርገዋል።

ልክ እንደ ቤተሰባዊ ግንኙነት የምቆጥረው (የሚጠራ) ጓደኝነት በሕይወታችን ላይ ልዩ ቦታ የምንሰጠውና በጣም ጠቃሚ ከሆኑ ግንኙነቶች መካከል አንዱ ነው። ሆኖም ልክ እንደሌላው ማንኛውም ትስስር ጤናማ አድርገን ለማቆየት ጥረት ይፈልጋል። በተለይ በጋራ ጥራት ያለው ጊዜ ማሳለፍ፣ ለቡናና ሻይ መገናኘት፣ ማዕድ መጋራት፣ ወይም በቀላሉ በስልክ ማውራት ግንኙነቶችን ያጠናክራል። የልደት ቀኖች በጋራ በማክበር፣ በግል ስኬት የሚመጡ አጋጣሚዎችን ወይም ደግሞ የግል ስኬቶችን ለማሰብ፤ ለጓደኛችን ወይም ለቤተሰባዊ ግንኙነቱ በቂ ጊዜን መመደብ እርስ በእርስ መከባበራችንንና አንዳችን ለሌላኛችን ያለንን መልካምነት ያንፀባርቃል።

በአስቸጋሪ ጊዜያት ጓደኞቻችንን መደገፍ አስፈላጊ ነው። አንድ ጓደኛህ (ፍቅረኛህ አሊያም የቤተሰብህ አባል) አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲገባ ጆሮ መስጠቱ ወይም በፈተናው ወቅት ጊዜህን መስጠት ሁሉንም ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። በሌላ በኩል ቅናት እና ፉክክር ጓደኝነትን ሊጎዳ ይችላል። ለጓደኞቹህ፣ ለቤተሰብህ አባል ስኬት እውነተኛ ደስታ ሲሰማህ አዎንታዊ ግንኙነትን ይገነባል፤ ወዳጅህን ያበረታታል እና ግንኙነቱን ዘላቂ እንዲሆን ያጠናክራል።

ከሰው ልጆች ግንኙነት መካከል ምናልባት የቤተሰብ ግንኙነቶች መልካም እንዲሆን ለማድረግ እንደ ቀላል ይቆጠራል። ብዙ ኃይል እንደማይጠይቅም ይታሰባል። ልክ እንደ ሌሎቹ ግንኙነቶች ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የቤተሰብ ግንኙነት መንከባከብ ጠቃሚ ነው። ከቤተሰብ አባላት ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ግንኙነቱን ለማጠናከር ይረዳል። እንደ ምግብ መጋራት፣ ጨዋታዎችን መጫወት ወይም በወጎች ውስጥ መሳተፍ ያሉ እንቅስቃሴዎች ሁሉንም ሰው የሚያቀራርቡ ትዝታዎችን ይፈጥራሉ። በቤተሰብ ውስጥም ግልጽ ግንኙነት አስፈላጊ ነው። አለመግባባቶችን በርጋታ መነጋገር እና የሌላውን አመለካከት መረዳት ግጭቶችን መፍታት እና ቂምን ለመከላከል ይረዳል።

ፍቅርን እና ምስጋናን መግለጽ የቤተሰብ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ሌላኛው መንገድ ነው። ለምሳሌ ባለቤትህን/ሽን ‹‹እወድሻለሁ/ሀለሁ›› ማለት አንዱ የግንኙነት ማጠናከሪያ መንገድ ነው። የቤት ውስጥ ሥራዎች ላይ መሳተፍ እንዲሁ መልካም ነው። ሌላው ከቤተሰብ አባላት ጋር ግንኙነትን የሚያጠናክረው ወንድም ወይም እህት እንደ መጠየቅ ያሉ ቀላል መንገዶችን መከተል ነው፤ ይህንን ማድረግ በመካከላችሁ መተሳሰብ መኖሩን ለማሳየት ይጠቅማል። ከቤተሰብ አባላት ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት መፍጠር ትዕግስት ይጠይቃል፣ በተለይም የባህሪ ወይም የአመለካከት ልዩነቶች በሚፈጠሩበት ወቅት ነገሩ ይበልጥ ሊከብድ ይችላል። የጋራ ፍላጎቶች ወይም ግቦች መፈለግና ለዚያም በመተባበር መሥራት ችግሩን ያቃልለዋል ተብሎ ይታሰባል፤ በተለይ ክፍተቶች ለማጥበብ ይረዳል።

ግንኙነቶችን መገንባት እና ማቆየት በመጨረሻው ውጤቱ የሚክስ ቢሆንም፣ እዚያ ላይ ለመድረስ ግን መንገዱ ሊረዝም ተግዳሮቶችም ሊያጋጥመን ይችላል። ነገር ግን በምድር ላይ ማንኛውም ነገር ያለ ፈተናና ጥረት ሊመጣ እንደማይችል ልናውቅ ይገባል። አለመግባባት የሚጠበቅ ነው፤ በነገሮች ላይ ያለን የሃሳብና የፍላጎት መለያየት ውጥረት ሊፈጥር ይችላል። የቅርብ የምንለውን ግንኙነቶችን እንኳን ሊያበላሽ ይችላል። እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ ዋናው ነገር ፊት ለፊት በመነጋገር ለመፍታት መሞከር ነው። ስለ ችግሮች ቁጭ ብሎ መነጋገር፣ ውይይቶችን ማድረግ ሁለቱም ወገኖች ስሜታቸውን እንዲገልጹ እና የጋራ መፍትሔ እንዲፈልጉ ያስችላቸዋል። በአጋርህ ላይ ስህተት ስትሠራ ይቅርታ መጠየቅ፤ አንተንም የሚያስከፋ አጋጣሚ ሲፈጠር ይቅር ማለት መተማመንን ለመጠገን እና ወደፊት ለመራመድ ወሳኝ ርምጃ ነው።

በእያንዳንዱ ግንኙነት ውስጥ ጊዜን እና ጥረትን ማድረግ (ኢንቬስት) አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የአትክልት ቦታ ስትንከባከበው እንዴት እንደሚያምር አስብ። ትኩረት ስትነፍገውና ስትተወው ደግሞ ምን ያህል እንደሚበላሽም አስተውል። ስለዚህ ግንኙነቶችህ እንዲያብቡ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ልትገነዘብ ይገባል። ሁሌም ከሰዎች ጋር የሚኖርህን ግንኙነት በመደበኛነት መፈተሽ ይኖርብሃል። አስደሳች ጊዜዎችን በጋራ ማክበር እና በአስቸጋሪ ጊዜያት እርስ በእርስ መረዳዳት ግንኙነቶችን ህያው እና ትርጉም ያለው እንደሚያደርጉት እወቅ። ፍፁም መሆን ባይቻልም ትክክለኛ እና እውነተኛ ለመሆን ጥረት ልታደርግ ይገባል። በሕይወትህ ውስጥ ላሉ ሰዎችና ባንተ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ምስጋናን ልታሳያቸው ይገባል። እነዚህ ከሰዎች ጋር ያለህን መልካም ግንኙነት አሊያም ትስስሮች የበለጠ ያጠናክሩታል።

ሳጠቃልልህ ትርጉም ያለው ግንኙነት በአንድ ጀምበር አይገነባም። ትጋትን፣ መረዳትን እና አብሮ ለማደግ ፈቃደኛነትን ይጠይቃል። መተማመንን፣ መግባባትን እና መከባበርን በማስቀደም ሕይወታችንን የሚያበለጽጉ ግንኙነቶችን መፍጠር እና የጊዜ ፈተናዎችን መቋቋም ቀዳሚው የሕይወት ልምዳችን ማድረግ ይገባናል። ጓደኛ፣ የቤተሰብ አባል ወይም የሥራ ባልደረባ፣ እነዚህን ግንኙነቶች ለመንከባከብ ጊዜ መውሰዱ ዘላቂ ደስታን እና ርካታን እንደሚያመጣለት አውቆ ከዛሬ ጀምሮ ይህንን የብልህ መንገድ ምርጫው ያድርግ። ሰላም!!

ዳግም ከበደ

 አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You