የቤት ባለቤት መሆን የተረጋጋ ሕይወት ለመኖር ዋናው እና መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑ መቼም ለማንም ግልጽ ነው። ይህን ፍላጎቴን ለማሟላት ደግሞ ወደዛ ወደዚህ ስል አንድ (ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው) ሪል ስቴት ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ በሚገኘው የሽያጭ ማዕከሉ ጋብዞኝ በክብርና በትህትና አስተናገደኝ። ሠራተኞቹ ሪል ስቴቱ የሚሠራውን ለማስረዳት እና ለመሸጥ የሚያደርጉት መስተንግዶ የሚደነቅ ነው። እኔም ማድነቅ ብቻ ሳይሆን ለሠራተኞቹ ያለኝን አድናቆትና ምስጋና ከፍ ያለ መሆኑን ገለጽኩላቸው።
በአጠቃላይ ከሪል ስቴቱ የተገለጸልኝ ነገሮች፤ መሀል አዲስ አበባ ላይ የተለያየ መጠን ያላቸው አፓርትመንቶች ለሽያጭ ማቅረባቸውን፣ የሽያጭ ዋጋቸው በካሬ ሜትር 1026 የአሜሪካ ዶላር መሆኑን። ክፍያ ሲፈፀም ክፍያ በሚፈፀምበት ዕለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዶላር በሚሸጥበት ምንዛሬ ታስቦ እንደሆነ። እንዲሁም ቅድሚያ ክፍያ 15 በመቶ ሲሆን ቀሪውን ቤቱ ተሰርቶ እስከሚያልቅ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት በሰላሳ ወራት ስለመከፈሉ አብራሩልኝ።
በተጨማሪም በረጅም ጊዜ ክፍያ መግዛት ለሚፈልግ ግለሰብ ደግሞ 60 በመቶ እና በ40 በመቶ የሽያጭ አማራጮችን ስለማቅረባቸው አስረዱኝ። ይህም 60 በመቶውን በ30 ወራት ከፍሎ ቀሪውን 40 በመቶ ደግሞ ከ20 እስከ 30 ዓመት ብድር ከ9.5 በመቶ ወለድ ጋር የሚከፈል ማለት ነው አሉኝ። ሪል ስቴቱ የቤት መሥሪያ ቁሳቁስ ስፔስፊኬሽን ማዘጋጀቱንም አከሉልኝ።
መቼም ለእንደኔ ዓይነት ቤት ፈላጊ ከላይ በገለፃ የተዘረዘሩት መልካም የሚባሉ ቢሆኑም አንዳንድ ግልጽ ያልሆኑልኝ ጉዳዮች ነበሩ። ለዚህም ገለፃቸውን ሲጨርሱ ጠብቄ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጀመርኩኝ። ለምከፍለው ቅድመ ክፍያ የባንክ ዋስትና አለው ወይ? ቤቱን የምትሠሩት ሁሉንም ወጪያችሁን በውጭ ምንዛሬ የማትገዙት ስለሆነ እንዴት 100 በመቶ በውጭ ምንዛሬ ሂሳብ ትሸጣላችሁ? የቤት መሥሪያ ወጪያችሁን ለመሬት፣ ለቁሳቁስ ለዲዛይን ለሠራተኛ ዓይነት በዓይነት ዘርዝራችሁት ከoverhead እና profit (የትርፍ ህዳግ) ጋር ልታሳውቁኝ ትችላላችሁን? የሚሉ ነበር።
እነርሱም በጥያቄዎቹ ደስተኛ ባይሆኑም ያው መልስ መመለስ ስለነበረባቸው እያቅማሙ ተከታዩን መልስ ሰጡኝ፤ በቅድመ ክፍያ ለተከፈለው ብር የምንሰጠው ጋራንቲ (ዋስትና) የለም። ሁሉም ገዥዎች ድርጅቱን አምነው ነው የሚገዙት አሉኝ። ይህ ማለት ድርጅቱ ወይም ሪል ስቴቱ ከከሰረ አብረው ይከስራሉ ማለት ነው ሲሉ ገለጹልኝ። እኔም መንግሥት የመገንባት ፈቃዱን ቢሰርዝበት አብረው ይከስራሉ ማለት ነው ብዬ ስጠይቅ በአዎንታ እራሱን ነቀነቀልኝ። ይህ ማለት ለእንደኔ ዓይነት ያለችውን ጥሪት አሟጦ ቤት ለሚገዛ ግለሰብ ከባድ አደጋ ወይም ጉዳት ያስከትላል ማለት ነው የሚል ድምዳሜ አለው።
ሌላው ደግሞ ቤቶቹን ለምን መቶ በመቶ በውጭ ምንዛሬ ሂሳብ ስለሚሸጡ ግልጽ አይደለም። ሲጀመር በውጭ ምንዛሬ ወይም በዶላር መሸጥ ተገቢ አይደለም፣ ሲቀጥል ለመሬት በብር የሊዝ ከፍሎ፣ ለሠራተኛ በብር ደመወዝ ከፍሎ፣ በቀላሉ ለአሸዋ፣ ሲሚንቶና ለጠጠር በብር ከፍሎ አሰርቶ ሁሉን ነገር ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ የሚሠራ ይመስል በዶላር ማድረግ ከሕገ ወጥ ግብይቱም በላይ ዜጎችን መዝረፍ ነው የሚል ድምዳሜ አለኝ። ከሁሉም በላይ ግን በይፋ እንደዚህ ሲሰሩ የመንግሥት ዝም ማለት የሚለው ግርምት ፈጠረብኝ።
ምክንያቱም መታለፍ የሌለበት ጉዳይ የአልሚው ወጪ በዝርዝር በማይታወቅበት ሁኔታ ይህን የመሰለ የብዙ ሚሊዮን ብር ግዥ ያውም አልሚው ሰርቶ ሊያስረክብ ቃል በገባበትና ገዥው በተባለው ጥራት በተባለው ጊዜ ለመሠራቱ ውል ሲዋዋል ተስፋ ከማድረግ ውጭ ርግጠኛ ባልሆነበት ሁኔታ እንዲሁም የጥራት መጓደል እና የመሳሰሉት ችግሮች ቢያጋጥም በገዥ ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመገመት አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ ሪል ስቴቱ ቃል የገባውን ተለዋጭ ጄኔሬተር ባያቀርብ ወይም አቅሙ ዝቅተኛ የሆነ ቢያቀርብ ሻጭ ለገዥ ምን ያደርግለታል የሚለው መልስ የለውም። ምክንያቱም ሪል ስቴት አልሚው እመኑኝ ብቻ ነው እያለ ያለው።
ይህ አሠራር ሲበዛ ኋላቀርና ዘመናዊነት ያልነካው አሠራር ነው። በተጨማሪም አሠራሩ ዜጎችን ለዘረፋ የሚያጋልጥና ጥበቃ የማይደረግበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሪል ስቴት አልሚዎች በራሳቸው ገንዘብ ሰርተው የሚሸጡ ባለሀብቶች ሳይሆኑ በመሬት ባለቤቱ መንግሥትና በመሬት ፈላጊው ቤት ሠሪ መሀል ያሉ ደላሎች ሆነው የሚንቀሳቀሱ ናቸው ማለት ይቻላል።
ምክንያቱም ቤቱ የሚገነባው ገዥው በየጊዜው ለአልሚ ነኝ ባዩ የሚከፈል ገንዘብ ስለሆነ የሪል ስቴት ባለቤት ነኝ ባዩ የሚያወጣው ቅንጣት ገንዘብ የለም። በጥሩ ምላስ ከከተማ አስተዳደሮች ወይም ክፍለ ከተማዎች ጋር ተግባብቶ በምትኩ መሬት ተረክቦ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ሽጦ የሚበለጽግ ጥገኛ ነው።
በሀገራችን ለቃላቸው የታመኑ ሪል ስቴት አልሚዎች ቢኖሩም በዘርፉ የሚሠራውን ሥራ ቀርቦ ወይም ተጠግቶ ለታዘበ ሰው አብዛኛዎቹ ሪል ስቴት አልሚዎች ነን የሚሉት ትላልቅ ደላላዎች ናቸው ቢባል የተሳሳተ አይሆንም። ከታናናሽ ቤት አሻሻጭ ደላላዎች የሚለዩት በመንግሥት የታወቁ፣ በጠበቃ የሚወከሉ፣ ቋሚ አድራሻ ያላቸው መሆናቸው ነው።
ለሚቀበሉት ገንዘብ ዋስትና የማይሰጡ፣ በአብዛኛው ማለትም ከ70 እስከ 85 በመቶ በሀገር ውስጥ ምርት የሚሠራን ቤት በዶላር አስበው የሚሸጡ ናቸው። በዶላር ባይሸጡም እንኳን አብዛኛው አልሚ ትርፍ ለማግበስበስ እንጂ ሀገር ለመጥቀም የሚሰሩ አይደለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።
የሪል ስቴት ገበያ በኢትዮጵያ አዲስ አሠራር ስለሆነ ህብረተሰቡ መሠረታዊ የሆነ የግንዛቤ ችግር ቢኖርበት የሚገርም አይደለም። በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የሚሰማው ሮሮ እና ምሬት አንድ የሪል ስቴት አልሚ የራሱ መሬት፣ ገንዘብ፣ ካፒታል እና ቴክኖሎጂ ኖሮት ቤት ጨርሶ ገንብቶ ቢፈልግ በኪራይ ቢፈልግ ደግሞ በሽያጭ ለሌላ የሚያስተላለፍ ተቋም ደረጃ የደረሰ ተቋም ያለ አይመስልም።
ሁሉም ሪል ስቴት በሚባል መልኩ ስም አለን፣ ታማኝ ነን፣ የተመሰከረልን ይሉና በማግስቱ ክህደት ሲፈጽሙ ይታያሉ። ሰው ያለውን ገንዘብ አሟጦ ከሰጣቸው በኋላ አንዴ ለቤት አይደለም አክሲዮን ነው የገዛኸው ይሉታል። አንዳንዱ ሪል ስቴት ደግሞ በ18 ወር ገንብቼ የቤት ባለቤት አደርጋለሁ ይልና እንኳን በ18 ወር በ12 ዓመትም ቃሉን መጠበቅ ተስኖት ይታያል።
ሌላው ህብረተሰቡ የግንዛቤ ችግር አለበት ሲባል በሁለት መንገድ ማስረዳት ይቻላል። አንደኛ፣ የሪል ስቴት መንደሮች በሚገነቡበት መንደር ውስጥ የጋራ መጠቀሚያ እንደ አዳራሽ፣ የጽሕፈት ቤት ወዘተ ዓይነት አገልግሎት መስጫዎች ተካተው ይሠራሉ። እያንዳንዱ የቤት ገዥ ለእነዚህ የጋራ መጠቀሚያዎች በመንደሩ ውስጥ ለራሱ ከገዛው ቤት አንፃር ተነፃፃሪ የሆነ ባለቤትነት አለው።
ሁሉም ቤቶች ከተሸጡ አልሚው በእነዚህ የጋራ መጠቀሚያዎች ላይ ምንም ዓይነት የባለቤትነት ድርሻ አይኖረውም። ምክንያቱም ገዥዎች በየድርሻቸው ቤት ሲገዙ ተከፋፍለው የከፈሉበት ስለሚሆን። ይሁን እንጂ የቤት ገዥዎች በጋራም ይሁን በተናጠል መብታቸውን ስለማያውቁ፣ አልሚዎች ሁሉንም ቤቶች ሸጠው የጋራ መጠቀሚያውን በስማቸው በማድረግ ለብቻው ለባንክ ብድር ወይም ለኢንሹራንስ ዋስትና እንደሚያሲዙት በግልፅ የምናይበት ሁኔታ ነው።
የሚገርመው ገዥዎች የሕግ ዕውቀት ማነስ ገጥሟቸው ወይም እርስ በእርስ መነጋገር አቅቷቸው ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ አቃታቸው ብንል እንኳን የተደራጀ ቀጥተኛ የሕግ አገልግሎት ያላቸው ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች በተለይም ደግሞ ከተማ አስተዳደሮች እንዴት በቤት ገዥዎች ጀርባ ይህን ዓይነት ደባ ይፈጽማሉ ብሎ ሲቆጣጠር አይታይም።
ሌላው ከላይ እንደገለጽኩት አልሚው በራሱ መሬት እና ገንዘብ ቤቶቹን ገንብቶ አጠናቆ ለግዥ ወይም ለኪራይ ማቅረብ ሲኖርበት ነገር ግን ግንባታ ዕውቀትም ሆነ ገንዘብ በበቂ ሁኔታ ስለሌለው አማላይ ማስታወቂያ በማስነገር (በርግጥ ማስታወቂያዎች አማላይ ብቻ ሳይሆኑ የሚያስፈራሩም ናቸው ለምሳሌ ኢንፍሌሽንን እንደ አንድ ማሳመኛ የሚጠቀሙ አሉ) ከቤት ፈላጊዎች በቅድመ ክፍያ ዓይነት ገንዘብ ተሰብስቦ የሚገነቡ ናቸው።
ያልተጠናቀቀ የመሬት፣ ሊዝ ዋጋ እና የግንባታ ወጪዎች በዚህ ዓይነት ከቤት ፈላጊዎች የሚሰበሰቡ ናቸው። በብዙ ሚሊዮን ብር በዚህ ዓይነት ከቤት ፈላጊዎች ሲሰበሰብ ለቤት ፈላጊዎች የሚሰጣቸው ምንም ዓይነት ዘመናዊ ዋስትና የለም። ዋስትና አለን ብለው ቢያስቡ እንኳን በከፈሉት ገንዘብ መጠን ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ መክፈል ከሚችል ከታወቀ ዋስትና ሰጪ ድርጅት፤ እንደ ባንክ፣ ኢንሹራንስ ወይም ሌሎች የገንዘብ ተቋማት ሳይሆን ከራሱ ከአልሚው ገንዘብ ተቀብያለሁ የሚል ደረሰኝ ብቻ ነው።
ይህ አሠራር ቤት በመፈለግ ገንዘብ የሚከፍሉ ሰዎችን ከፍ ያለ የገንዘብ አለመመለስ ወይም ቤት ያለ ማግኘት ስጋት ሰለባ ያደርጋቸዋል። ከአደጋዎቹ መካከል አንዱ በቤት አልሚዎቹ ላይ የሚወሰድ ሕጋዊ ርምጃ ነው። ለምሳሌ አልሚው መክፈል የነበረበትን ግብር ሳይከፍል ቢቀር ድርጅቱ ከፍተኛ ቅጣት ቢጣልበት እና ከሌላ የገንዘብ ምንጭ መክፈል ባይችል የቤት ፈላጊዎች ገንዘብ ሊከስር ይችላል።
አልሚው በንብረቱ ከፍተኛ ገንዘብ ቢበደርበት እና መክፈል አቅቶት ወይም ገንዘቡን በሌላ መንገድ ቢያሸሸው ቤት ፈላጊዎች ከባንኩ የተለየ ቅድሚያ ገንዘባቸውን የማግኘት መብት ስለማይኖራቸው ከስረው እና አልቅሰው የሚቀሩበት ሁኔታ አለ። ከአቅም በላይ የሆኑት ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው አልሚ ነኝ ባዩ ለሌላ ሰው ቤቶቹን ቢሸጣቸው እንኳን ለተስፈኛ ቤት ገዥዎች የሚኖራቸው አማራጭ አሰልቺ የፍርድ ቤት ክርክር ነው።
ስለዚህ አሠራሩ ከፍተኛ ስጋት የተደቀነበት ነው ማለት ይቻላል። በዚህ ዓይነት በሚሊዮን ገንዘብ የሚሰሩ አልሚ ነን ባዮች ከሥራ ጥራት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን ስጋት ወደ አስተማማኝ ዋስትና ሰጪ ስለማያስተላልፉት ቤት ተረካቢዎች ለብዙ ጊዜ የሚቆይ ከፍተኛ የሆነ የጥገና ወጪ ይኖርባቸዋል።
ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አልሚ ነን የሚሉት በከፍተኛ ደረጃ ቤት ፈላጊዎችን የሚያጭበረብሩበት ሁኔታ አለ። ቤት ተገንብቶ ሲያልቅ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ውሃ ቧንቧ፣ ፍሳሽ ማስወገጃ፣ ኤሌክትሪክ መስመሮች አሠራር እና የዕቃውም ጥራት ኑሮን በቤት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ሊያውክ የሚችሉበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አደጋ እና ወጪም የሚያስከትሉ ናቸው።
ለእነዚህ እና ሌሎች የግንባታ ግድፈቶች አልሚው፣ ገንቢው ተቋራጭ እና ዲዛይኑን የሠራው እና ጥራቱን የተቆጣጠረው አርክቴክት/ኢንጂነር በጋራ እና በተናጠል ኃላፊነት ቢኖራቸውም እንደ ገንቢ ተቋራጭ፣ ዲዛይነር እና ተቆጣጣሪ ኢንጂነሮች ቤት ፈላጊዎች እንዳያውቋቸው ስለሚደረግ በሆነ መንገድ አልሚው ቢከስር አለመታወቃቸው ከተጠያቂነት ነፃ ያደርጋቸዋል።
ለማጠናቀቅ ያህል ቤት አልሚ ነን የሚሉት ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የመንግሥት እና ሕዝብ ገንዘብ የሆነውን መሬት ወስደው የሚሰሩት የሪል ስቴት ሥራ ሕጋዊ ቢመስልም ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ተጠያቂነታቸው ያልሰፈነበት አሠራር ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም መንግሥት ምንም እንኳን በገበያ ጣልቃ ባይገባም ነገር ግን ተቋም አቋቁሞ የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት።
በተለይም ቤት ፈላጊዎች ቅድመ ክፍያ ከከፈሉበት ቀን ጀምሮ ቤቱ በስማቸው ሆኖ የባለቤትነት ካርታ ኑሯቸው፣ ግንኙነታቸውም የቤት ባለቤት እና የቤት ገንቢ ተቋራጭ መሆን አለበት። ይህን አሠራር የማይከተል ወይም የማይፈልግ አልሚ ካለ ደግሞ አልሚዎች በራሳቸው ገንዘብ አጠናቀው የሚጨርሱ መሆን አለባቸው።
መኮንን ፀጋው (ኢንጂነር)
አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም