ለሁለንተናዊ ብልጽግና የአምስት ዓመታት ውጤቶች

ኢትዮጵያ በሕዝብ ጥያቄ ለውጥ ከመጣ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ብልጽግና እንደፓርቲ ተቋቁሞ ሀገር መምራት ከጀመረ አምስት ዓመታት ሁኖታል። በእነዚህ ዓመታት በርካታ ለውጦችና ፈተናዎች ተስተውለዋል፡፡

ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝብ የሚፈልገውን የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊና የፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብልጽግና ፓርቲ ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እስከ ኢንዱስትሪው፤ ከሌማት ትሩፋት እስከ ኮሪደር ልማት የመጡ ውጤቶች እንደ ማሳያ የሚገለጹ አብነቶች ናቸው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት በማስመልከት የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‹‹ለውጡና የለውጡ ፍሬዎች›› በሚል ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሕዝብ ግፊትና በፓርቲ ሳቢነት የመጣው ሀገራዊ ለውጥ፣ የመጀመሪያውን ምእራፍ እየተሻገረ ነው፡፡ በዚህም የለውጡ ሃሳቦች በቃልና በተግባር ተገልጠዋል፡፡ የለውጡ ፈተናዎችም አካል ገዝተው በሚገባ በመገለጣቸው ሕዝብ አውቆ እንዲታገላቸው ተደርጓል፡፡ ይሄም የለውጡን ፍሬዎች ለማጎምራት፣ የለውጡን ፈተናዎችንም ለመርታት ዕድል መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ነባሮቹን ፖለቲካዊ ዕሴቶች በሚያጎለብትና የፖለቲካ ስብራቶቻችንን በሚጠግን፤ መልኩ ተመሥርቷል ያሉት ፕሬዚዳቱ፤ ይህም የለውጡ አንዱ ፍሬ ነው፤ ፓርቲው የዳርና የመሃል፤ ዋና እና አጋር፣ አርብቶ አደርና አርሶ አደር፤ ተራማጅና አድሃሪ፤ ጠላትና ወዳጅ፣ የሚባሉትን ግንቦች በማፍረስ በሃሳብ ላይ ብቻ የተመሠረተ የፖለቲካ አደረጃጀት መፍጠር እንደተቻለ በመልዕክታቸው አስፍረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎች ከቃል አልፈው ተግባራዊ ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ለአብነት የፖሊሲ፣ የሕግ እና የአሠራር ብቻ ሳይሆን የባህል ለውጥ መጥቷል፡፡ ለውጡ ያለፉት የሀገሪቱን ስብራቶች የሚጠግን፣ ዛሬን የሚዋጅና የነገውን የኢትዮጵያ ጉዞ ያቀና ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የእምነት ተቋማት ከለውጡ በፊት በመንግሥት ጣልቃ ገብነትነት፣ ጥገኛነትና የህልውና ፈተና እንደነበረባቸው በማስታወስ፤ ከለውጡ በኋላ የእምነት ተቋማት ልዕልና ተከብሯል፡፡ ይሄንን ልዕልና ለማስከበርም መንግሥት በተቋማቱ ላይ ሲያደርግ የኖረው ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት ቀደም ሲል የነበረውን የተንሸዋረረ አመለካከት በማስተካከል፣ ለሀገር በሚበጅ መልኩ በአዲስ ሕግና አደረጃጀት እንዲዋቀሩ አድርጓል፡፡ ከለውጡ በፊት አንድ ሺህ 900 የነበሩት የሲቪክ ማህበራት ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ሶስት ሺህ 300 አዳዲስ ሲቪክ ማህበራት መመዝገባቸውን አመላክተዋል፡፡

የዴሞክራሲ ተቋማት ከነበረባቸው ችግር በመላቀቅ ነጻ፣ ገለልተኛና ተአማኒ እንዲሆኑ የሚያስችል የሕግና የአደረጃጀት ለውጦች ተደርጎባቸዋል፡፡ በተመሳሳይም የሚዲያ የብዝኃነት እንዲሻሻል አሣሪ ሕጎች ማሻሻል፤ የሚዲያ ተደራሽነትን ማበረታታት፣ ሚዲያዎች እርስ በርስ ራሳቸውን የሚቆጣጠሩበትን ሥርዓት የመዘርጋት ሥራዎች ስለመከናወናቸው አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በለውጡ ዘመን የግብርና ኋላ ቀርነትን ቀርፎ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተሠራው ሥራ የባህል ለውጥ መጥቷል፡፡ ዝናብ ላይ መሠረት ያደረገውን የግብርና ባህል መስኖን በመጠቀም፣ በኩታ ገጠም እርሻና መሬት ጦም እንዳያድር በተሠራው ሥራ፣ ዓመቱን ሙሉ የሚመረትበት ባህል እያመጣ ነው፡፡

ስንዴን፣ ሩዝን፣ ገብስን፣ በቆሎንና የፍራፍሬ ምርቶችን ትኩረት አድርጎ በተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ወደ ውጭ መላክ ተሸጋግራለች። በሌማት ትሩፋት በተሠራው ሥራም የወተት፣ የዶሮና የማር ምርቶች በየቤተሰቡ ሌማት ላይ እንዲገኙ ሰፊ ሥራ መከናወኑን አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማዘመን በተሠራው ሰፊ ሥራ የኢንዱስትሪ ምርታማነት ሥራ ላይ ከፍተኛ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተቻለ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ማዘመን ያለ ድጂታላይዜሽን የሚረጋገጥ ባለመሆኑ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚያደርገው ምርምር እና የሚያፈሰው ሙዓለ ንዋይ እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት፡፡

በገበታ ለሸገር በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡት የቱሪስት መዳረሻዎች በተጨማሪ፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በጎርጎራ፣ በወንጪ፣ በሐላላ ኬላና በኮይሻ የቱሪስት መዳረሻዎች ተገንብተው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በገበታ ለትውልድ ደግሞ በሌሎች ሰባት የሀገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ያሉት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ለማዘመን ከተደረጉ ጥረቶች መካከል ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያን ከተሞች ለዜጎች ምቹ፣ ጤናማና አካታች ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደርሷል ነው ያሉት፡፡

የጸጥታና የደህንነት ተቋማትን ለማዘመን በተሠራው ሥራ ሠብዓዊ፣ መዋቅራዊና ቴክኖሎጂያዊ ብቃት ያላቸው የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ተፈጥረዋል ያሉት ዐቢይ( ዶ/ር)፤ ተቋማቱ ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርገው ተልዕኳቸውን እንዲያከናውኑ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነዋል፡፡ የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሪፎርም በማድረግ ኢትዮጵያን የሚመጥኑ ተቋማት እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ለውጡ እንዲመጣ ገፊ ከሆኑ ሀገራዊ ስብራቶች አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት መሆኑን በመልዕክታቸው ያሰፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቱ ለመጠገን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመተግበር ሁሉን አቀፍ ሥራ ተሠርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ዓለም በብዛት እንዲቀበለው ለማድረግ ተችሏል፡፡ በዓለም አቀፍ መድረኮችም ብሔራዊ ጥቅሞቿን ሊያስከብሩ በሚችሉ የሁለትዮሽና ባለ ብዙ ወገን ትብብሮች ላይ በጉልሕ እንደምትሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አስፍረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ እንደሀገር ከዚህ ቀደም የነበሩ መዛነፎችን ብልጽግና በመደመር እሳቤ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን ማድረጉን በመጥቀስ፤ ድህነት ለማሸነፍ ፈርጀ ብዙ ፋይዳዎች ያሏቸው ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ያሉ አንጡራ ሀብቶች፤ እሴቶች፤ ባሕሎች፣ እሴቶችና አቅሞችን በመደመር ታላቅ ሀገራዊ አቅም ፈጥረናል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የሰላምና የልማት ሥራዎችን በማጠናከር በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ ኢትዮጵያ የሚገባትን የመሪነት ሚና መጫወት እንደሚኖርባት ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብልፅግና ፓርቲ ያለ ዕረፍት በመሥራት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ያደርጋል ነው ነው ያሉት፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፤ ብልጽግና ፓርቲ በለውጥ ትግል ውስጥ ተወልዶ በአዲስ እይታ፣ አዲስ ምዕራፍ ከፍቶ እያደገ ያለ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የተጓዘችው የአምስት ዓመት ጉዞ ስኬት ያስመዘገበችበትና ፈተናም የተጋፈጠችበት ነው፡፡ ሆኖም ግን በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲ መስክ ያስመዘገበቻቸው ድሎች ታላላቅ ናቸው።

ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያቀፈ፣ ኅብረ ብሔራዊ፣ ሀገራዊና ወጥ ፓርቲ ሆኖ በመፈጠሩ ምክንያት ኢትዮጵያውያን በአንድ ጥላ ስር መሰባሰብ የቻሉበት ነው። ፓርቲው ከተመሠረተ ወዲህ የትርክት ለውጥ መጥቷል፤ ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን እና አብሮነትን የሚፈጥሩ ትርክቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ መቻሉን ይገልጻሉ፡፡

ቢቂላ(ዶ/ር)፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢኮኖሚው በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች በማካሔዱ ኢኮኖሚውን ከመንኮታኮትና ከውድቀት የታደገ ፓርቲ ነው፡፡ የእዳ ማስተካከያ እና የእዳ ሽግሽግ በማስደረግ የሀገሪቱን የእዳ ጫና በማቃለልም ትልቅ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ግብርና መር ብቻ ይባል የነበረው የኢኮኖሚ እሳቤ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እንዲሆን ግብርናን፣ ማኑፋክቸሪንግን፣ ማዕድንን፣ ቱሪዝምን እና የዲጂታል ኢኮኖሚን አንድ ላይ በማጣመር የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች ሚዛናቸውን ጠብቀው እና ተደጋግፈው እንዲያድጉ ማድረግ ያስቻለ ሥራ መሥራቱን አስረድተዋል፡፡

በሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You