የለውጡ ጉዞ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እያቃረበ ነው!

በሀገራችን ስር ነቀል በሚባል መልኩ ለውጥ ማየትና ለውጡን ማጣጣም ከጀመርን እነሆ አምስት ዓመታት ሆነን። በእነዚህ የአምስት ዓመታት ቆይታ የታዩት የለውጥ ፍሬዎች ረጅም ዓመታትን ባሳለፍንባቸው ዘመናት ያልታዩና ይሆናሉ ተብለው የማይጠበቁ አስደናቂ ክስተቶች ናቸው። በሀገራችን ትልቅ ተግዳሮት ሆነው ይነሱ የነበሩ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፣ የመደራጀትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ፣ ኢፍትሃዊነት፣ የኋላ ቀርነት አስተሳሰብ፣ የምግብ ዋስትና ችግር፣ የኢኮኖሚ ስብራት የመሳሰሉት ኢትዮጵያ ትከሻዋ እስኪጎብጥ ተሸክማ የኖረቻቸው ችግሮቿ ነበሩ።

እነዚህ ዛሬ ከትከሻዋ የወረዱ፣ አሁንም ጨርሰው ያልወረዱ የኢትዮጵያውያን ችግሮች ከዓመታት በፊት በሀገራችን ለውጥ እንዲመጣ ገፊ ምክንያቶች ነበሩ። ለውጡን አቀጣጥሎ ወደፊት የተራመደው መንግሥትም በእያንዳንዱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥልቅ ጥናት በማድረግና ችግሮችን ከመሠረታቸው በመለየት ዘላቂ መፍትሄ በሚሰጥና ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና ማማ ሊያወጣ በሚያስችል መልኩ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል። ሀገሪቷን እግር ከወርች ጠፍረው አላሰራ ያሉ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አዋጆች፣ ሕጎችና ደንቦችን ጨምሮ በአፈፃፀም የሚታዩ ግድፈቶችን ሁሉ ባገናዘበ መልኩ በርካታ የማስተካከል ርምጃዎች ተወስደዋል። በሪፎርም ህሳቤ አዳዲስ አሠራሮች የመዘርጋትና አሻጋሪ አስተሳሰቦችን የማመንጨትና የማስረጽ ሥራዎች ተሠርተዋል ። በዚህም ዜጋው ብቻም ሳይሆን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር በሚረዳው መልኩ ለውጡን ተጨባጭ ማድረግ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ሁሉም ዜጋ የአምስት ዓመቱን የለውጥ ፍሬዎች አይቶ እያደነቀ ፣ ቀምሶ እያጣጠመ እና እየኖረው ይገኛል።

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪካችን ሕዝብ ፖለቲካን በሩቁ ብሎ እሳትን እንደሚፈራ ህጻን ፖለቲካን ፈርቶና ርቆ እንዲኖር ያስገደዱ ነበሩ። እርስ በእርስ ከመቀራረብ ይልቅ ጥላቻንና ቅራኔን አስፋፍተዋል። ይሄ የጥላቻና ያለመተማመን የፖለቲካ ሴራ ዛሬም ድረስ ነጸብራቁ አልጠፋም። ይሄን አካሄድ የማደስና የማረቅ ጥረት በለውጡ መንግሥት ተደርጓል። በትጥቅ ትግል ጎራ ለይተው ለሀገር ጭምር ስጋት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ገብተው በፖለቲካ ሜዳው የተሳትፎ መብትን ተጎናጽፈዋል። ከፌዴራል እስከ ክልል በካቢኔ እንዲሳተፉም ተደርጓል። ከጽንፍ ፖለቲካ በመራቅ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል።

ሕገ መንግሥቱ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሲል ቢደነግግም ከለውጡ በፊት ግን የእምነት ተቋማት የመንግሥት ጥገኛነትና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲያምሳቸው እንደነበር የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ዛሬ ይህንን ታሪክ ወደ ማድረጉ ተሸጋግረናል። የእምነት ተቋማት ልዕልና ተከብሯል። ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የነበረባቸውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል። ውጤቱም በተጨባጭ ታይቷል።

በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተሠራው ሥራ የተደረሰበት የባሕል ለውጥ ሌላው የለውጡ ቱርፋት ነው። ከዚህ በፊት የዝናብ ወቅት ብቻ ይጠብቅ የነበረው የግብርና ሥራ መስኖና የበጋ እርሻን በመጠቀም፣ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በመከተል፣ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል ከፍተኛ ምርት ማምረት ተችሏል። በተለይ በስንዴ እና ሩዝ ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ በተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች። ከርዳታ ተቀባይነት ወጥታ ወደ ላኪነት ተሸጋግራለች።

የሌማት ትሩፋት የለውጡ ሌላኛው ቱሩፋት ሲሆን ወተት፣ የዶሮና የማር ምርቶች የቤተሰብ ምግብ መሆን ችሏል። በዚህም የዶሮ ሥጋን ምርት ከነበረበት 70 ሺህ ቶን ወደ 208 ሺ ቶን፤ የወተት ምርት ከነበረበት ሰባት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ሊትር ወደ 10 ቢሊዮን ሊትር ደርሷል። የማር ምርት ደግሞ ከ 129 ሺህ ቶን ምርት ወደ 272 ሺህ ቶን ለማሳደግ ተችሏል። አንድም በኢኮኖሚ የማደግ ሌላም ተመጣጣኝ ምግብን የማግኘትና ገበያን በማረጋጋት ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከታታይ ዓለምን ያስደመመ ፣ ተፈጥሮን የለወጠ ፣ ዐሻራን ለትውልድ ያስቀመጠ የአረንጓዴ ልማት ሥራም ተሠርቷል። በዚህም 40 ቢሊዮን የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን መትከል ተችሏል። ይህም 50 ነጥብ 4 በመቶ የደን ዛፍ ፣ 48 ነጥብ 6 በመቶ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ፣ የፍራፍሬ፣ የመኖና የማገዶ የእንጨት ዛፎች ናቸው። ይህም በእያንዳንዱ ግለሰብና ቤተሰብ ባህል ሆኖ ቀጥሏል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በሁሉም መስክ ኢትዮጵያ ወደፊት እየተስፈነጠረች ትገኛለች። በኤከስፖርት ገቢ በኢንዱስትሪ ዕድገት በቴክኖሎጂ ወዘተ የተመዘገቡ ድሎች የዚህ አባባል እውነተኛነት ማረጋገጫዎች ናቸው።

ዛሬ ዓለም የደረሰበት ዲጂታላይዜሽን ዘመን ላይ ቆመን ኢትዮጵያ የበይ ተመልካች እንዳትሆን የለውጡ መንግሥት ወገቡን አስሮ የቴክኖሎጂው ባለቤት ለመሆን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በዘርፉ በርካታ ሰዎችን በማሠልጠን ከፍተኛ በጀት በመመደብ በተሠራው ሰፊ ሥራ አስገራሚ ውጤት ተገኝቷል።

የዲጂታል አካውንት ብዛት ከነበረበት 52 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዛሬ ወደ 205 ነጥብ 4 ሚሊዮን ደርሷል። በዘመናዊ የክፍያ ዘዴ የተላለፈው የገንዘብ መጠን ደግሞ ወደ 9 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር አድጓል።

በቱሪዝም ገቢን የሚያሳድጉና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሥራዎች ተሠርተዋል። ገበታ ለሸገር ፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ኮሪደር ልማቱን ማንሳት ብቻ ከበቂ በላይ ነው። ተበላሽተውና ወደ ውድቀት እያመሩ የነበሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችም በልዩ ክትትል በማጠናቀቅ ለፍሬ በቅተዋል። ለዚህም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋነኛ ማሳያ ነው።

እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ለለውጡ ምክንያት ከሆኑት መካከል የሚጠቀስ ነው። እነዚህንና ሌሎች ያልተጠቀሱ የለውጥ ፍሬዎች ሀገር እንደ ሀገር እንድትቆምና ብልጽግናዋ እንዲረጋገጥ ያደረጉ በመሆናቸው እያጣጣምን ልንጠቀምባቸው፤ የበለጠ አሳድገን የኢትዮጵን ሁለንተናዊ ብልጽግና ልናረጋግጥ ይገባል!

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You