ባንኩ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ

አዲስ አበባ፦ የእስያ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ጂን ሊኲን ጋር በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሚጠናከሩበት ሁኔታዎች ላይ ትናንት ተወያይተዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ጂን ሊኲን በወቅቱ ፤ ባንኩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፤ በመሠረተ ልማትን ለማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖችን መከላከል በሚቻልባቸው መንገዱች ላይ የፋይናንስ ድጋፍ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ጋር መግባባቶች እንደተፈጠሩ ገልጸው፤ ተቋማቸው ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚሁ ውጤታማነትም ከሌሎች አጋር የፋይናንስ ተቋማት ጋር እንደሚሠሩ ገልፀዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ ደርሰዋል ብለዋል።

የረጅም ጊዜ የእድገት ፕሮግራም፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና ሌሎችንም ተግባራት ኢትዮጵያ እያከናወነች መሆኑን ለባንኩ አመራሮች አስረድተናል ያሉት አቶ አህመድ፤ ኢትዮጵያ ለምትገነባው አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ሆነው የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተወያይተናል ነው ያሉት።

ባንኩ መሠረተ ልማቶችን ፋይናንስ የሚያደርግ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋሙ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲሳተፍ ተወያይተናል። በተጨማሪም የታዳሽ ኃይል ምንጭ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ መግባባታቸውንም ጠቁመዋል።

ከባንኩ ፕሬዚዳንት ጋር የተደረገው ውይይት ውጤታማ መሆኑንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በርካታ ሳቢ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሏት የገለፁት አቶ አህመድ ሽዴ፤ ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ለሀገራዊ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የግሉን ዘርፍ ማሳደግ ይገባል። ለዚህም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ህዳር 20/2017 ዓ.ም

Recommended For You