የሞተር ስፖርት አሶሴሽን በመንገድ ደኅንነት ዙሪያ እየሠራ ነው

አዲስ አበባ ፡- ከስፖርቱ ጎን ለጎን በመንገድ ደኅንነት ላይ እየሠራ መሆኑን የኢትየጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን አስታወቀ።

የአሶሴሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አዲስ ዓለማየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ያለባት ሀገር በመሆኗ ፌዴሬሽኑ ከስፖርቱ በተጨማሪ በመንገድ ደኅንነት ላይ ለመሥራት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሠራ ይገኛል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፣ አሶሴሽኑ በመንገድ ደኅንነትና አካባቢ ጥበቃ ላይ ለመሥራት የፓይለት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በጎሕ ካርትና በአውቶሞቲቭ ክለቦች ላይ ሥራውን ጀምሯል። በመንገድና ትራፊክ ደኅንነት ዙሪያ በተከናወኑ የፕሮጀክት ሥራዎችም አባሎችንና ደጋፊዎችን ማግኘት ተችሏል።

አሶሴሽኑ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግን በተመለከተ በሳምንት ቋሚ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቀርፆ በመንገድ ደኅንነት ላይ የማስተማር እቅድ ነድፏል። በእቅዱ መሠረትም የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት በኢትዮጵያ መንገድ ደኅንነት ላይ ዐሻራውን ለማሳረፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

አሶሴሽኑ በዚህ ዓመት ስለ ስፖርቱ በዓለም አቀፍ ተሞክሮ ላይ ተመሥርቶ በሳምንት ቀጣይነት ባለው መልኩ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በካይ ጋዝ፣ አካባቢ ጥበቃ እና በዋናነት ከመንገድ ደኅንነት ጋር የተያያዙ የግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎችን ከዪኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር ይሠራል። በዚህም የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እየተለወጠ እንደሚሄድ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ የሞተር ስፖርት ማኅበር እራስን ከአደጋ ተከላክሎ በማሽከርከር እና በመንገድ ደኅንነት ዙሪያ ሥልጠና መሰጠቱን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ከመሰል ሥልጠናዎች የሚገኙ ተሞክሮዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት በመንገድና ትራፊክ ደኅንነት ዙሪያ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በአሶሴሽኑ እቅድ መሠረትም በዓመቱ ዓለም አቀፍ ልምዶችን ለመቅሰም ታስቦ ባለፈው ሁለት ወር ውስጥ ሲውዘርላንድ፣ ኬንያና ዱባይ ላይ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እና የተለያዩ ሥልጠናዎችን ማግኘት እንደተቻለ አክለዋል።

የሞተር ስፖርት በባሕሪው በመኪና መንገዶች ላይ የሚካሄድና ለአደጋ ተጋላጭና አጋላጭ በመሆኑ ለወጣቶች እንዴት እራስን ከአደጋ ተከላክሎ ማሽከርከር እንደሚችሉ የጥንቃቄ ሥልጠና መስጠት ተችሏል። ‹‹በሞተር ስፖርት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ስለሚሰጥ በዚህ ውስጥ አልፎ ወደ ውድድር የሚገባ አሽከርካሪ አደጋ የማድረሱ ዕድል ጠባብ ነው›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህን ከስፖርቱ ውጪ ባሉ አሽከርካሪዎች መጠቀም ከተቻለ የተሽከርካሪ አደጋን በመቀነስ ረገድ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ይህንንም ሲያብራሩ፣ አሽከርካሪዎች የሞተር ስፖርት ተወዳዳሪ እንኳን ባይሆኑ ሥልጠናውን ከወሰዱ መንገድ ላይ በሚያሽከረክሩበት ወቅት አደጋ የማድረስ ዕድላቸው ጠባብ እንደሚሆን ያስረዳሉ።

የሞተር ስፖርት ከቱሪዝም መዳረሻነት፣ ከትራፊክ አደጋ፣ ከተሽከርካሪ አማቂ ጋዞች፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግርና ከሌሎች መንገዶች ጋር በተያያዘ ለሀገር ትልቅ አበርክቶ ያለው ስፖርት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው፣ ይህንን ለመጠቀም አሶሴሽኑ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመንገድ ደኅንነት ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ውይይት በማድረግ ግንዛቤ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪ አሶሴሽኑ ከመንገድ ፈንድና መንገድ ደኅንነት ጋር አብሮ ለመሥራት ውይይት በማድረግ የመግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቋል። ከእነዚህ አካላት ጋር በትብብር በትራፊክ አደጋና መንገድ ደኅንነት ዙሪያ በመሥራት ለውጥ ለማምጣት ብዙ እቅዶች እንዳሉትም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You