አርባ ምንጭ:- ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በግብርና፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራታቸውን የጋሞ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ መምሪያ አስታወቀ።
የጋሞ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ግርማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ ጋሞ ዞን ለተለያዩ የልማት ሥራዎች እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ነው። ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በዞኑ በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
በዞኑ በኢንቨስትመንት ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ተመዝግቧል ያሉት ኃላፊው፣ ከዚህ ውስጥ በግብርናው 15 ሺህ ሄክታር መሬት ለአልሚዎች ተሰጥቷል። አልሚዎችም እያለሙ ይገኛሉ ብለዋል።
በዞኑ 99 አልሚዎች በተለያዩ የግብርና ዘርፎች የተሰማሩ መሆኑን አመልክተው፤ እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በአገልግሎት ዘርፍም 113 አልሚዎች መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።
በኢንዱስትሪ ዘርፍ 30 አልሚዎች መሰማራታቸውን ገልጸው፤ የአልሚዎችን ቁጥር ለማብዛት ከሦስተኛ ወገን ነፃ የሆነ የኢንቨስትመንት ቦታ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ፣ በአገልግሎት ዘርፍም በነዳጅ ማደያ፣ በሆቴል፣ ሞቴል፣ በሪዞርትና መሰል ዘርፎች ተሰማርተው እየሠሩ ያሉ አልሚዎች አሉ። በቅርቡ ወደ አገልግሎት የሚገባ ሪዞርቶች፣ ሎጂና ሆቴል እንደሚኖርም ጠቅሰዋል። ይህም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ሲሆን ጎብኝዎችን በስፋት እየሳቡ እንደሚገኙ አንስተዋል።
በጋሞ ዞን በኢንዱስትሪ የተሠማሩ 30 አልሚዎች በጨርቃጨርቅ የተሰማሩ አልሚዎች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህም የዞኑን እምቅ አቅም በመጠቀም እንደ ሀገር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል። ወደፊትም ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የአካባቢውን ፀጋ በሚገባ ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲሉ አንስተዋል።
በዞን ያሉ ዕድሎችን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ምቹ የመሠረተ ልማት ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
የጋሞ ዞን ለኢንዱስትሪ ምቹ ቢሆንም አልሚዎች በስፋት አልተሳተፉም ያሉት ኃላፊው፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች እንዲጨምሩ የክልሉ መንግሥት በስፋት እየሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል። እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ዓመቱን ሙሉ የቲማቲም፣ የፓፓያና የሙዝ ምርት መኖሩን በመግለጽ፣ በሚቀጥሉት አጭር ጊዜያት የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አልሚዎች ወደ ሥራ እንደሚሰማሩ አመልክተዋል።
በሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም