አዲስ አበባ፡- እስካሁን በአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል መሰብሰቡን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ:: ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በመኸር አዝመራ 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኗን ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ እና መንግሥት ትኩረት በሚያደርግባቸው ጉዳዮች ላይ ትናንት መግለጫ ሲሰጡ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በቆላማና ከፊል ደጋማ አካባቢዎች የመኸር አዝመራው እየተሰበሰበ ይገኛል:: እስካሁንም በአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ተሰብስቧል።
በደጋና በአብዛኛው ወይናደጋ አካባቢዎችም የሰብል አዝመራው በጣም ጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በያዝነው ኅዳር እና በመጪው ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም የመኸር አዝመራው ሙሉ በሙሉ የሚሰበሰብ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በመኸር አዝመራ 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኗን አውስተው፤ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥም 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘመነ መልኩ በክላስተር የተሸፈነ ነው:: ይህም የኢትዮጵያ ግብርና ከሚታወቅበት ባሕላዊ የአስተራረስ ዘይቤው በመሠረታዊነቱ እየተቀየረ መሆኑን የሚጠቁም ነው ብለዋል::
ኢትዮጵያ ያለመችው ከፍተኛ ምርት እና ይህ የሚሰጣት መንሠራራት ሊሳካ የሚችለው ክረምቱን ሁሉ ርብርብ ያደረግንበትና በአሁኑ ወቅት ጥሩ የሚባል ይዞታና ቁመና ላይ የሚገኘው ሰብል በወቅቱና በጥራት ያለብክነት መሰብሰብ ሲቻል ነው:: ይህ ደግሞ የአምራቹን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል ብለዋል::
ለዚህም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮችና አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ሁሉንም የሰብል መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እና የመንግሥት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች እንዲሁም የመንግሥት ፀጥታ አካላት በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማነሳሳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል::
በመኸር አዝመራ እና በበልግ ላይ ብቻ በመመሥረት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደማይቻል የጠቆሙት ለገሠ (ዶ/ር)፤ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ በተለይም ለስንዴ ምርት ትኩረት በመስጠት አኩሪ ሥራ ሠርታለች:: በምግብ ምርት ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድረግም በበጋ ከፍተኛ ምርት ለማምረት የመስኖ ግድቦች እና መሠረተ ልማቶች እንዲፋጠኑ እየተሠራ ነው ብለዋል::
በዚህ ዓመት ብቻ የመስኖ እምቅ አቅም ባላቸው 10 ክልሎች ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 173 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ምርት ለማግኘት ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል::
የኢትዮጵያን የማንሠራራት ዘመን እውን ለማድረግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ የጤና እና የትምህርት ተደራሽነት ላይ ያተኮሩ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። የዋጋ ንረትን በመቀነስና የኑሮ ውድነትን በማስወገድ፣ የሥራ ዕድልን በማስፋት በሁለንተናዊ መልኩ ማንሠራራት የሚቻልባቸው ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: ያለፉ ስብራቶችን ለመጠገንም ምክክር እና የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ በማድረግ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ይሠራል ሲሉም ገልጸዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የላቀ አስተዋፅዖ እንዲያደርግ እየተሠራ ነው ያሉት ለገሠ (ዶ/ር)፤ የተሠሩ ፓርኮች እና የኢኮ ቱሪዝም ሎጆች ሀብት ወደ መፍጠር መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባን የማስዋብ ሥራው ውጤታማ መሆኑን እና በዚህም በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ታላላቅ ጉባዔዎችን ማስተናገድ መቻሉን ጠቅሰዋል:: ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን በንግግር ለመፍታትም በሀገራዊ ምክክሩ የተጀመሩ ሥራዎች እውን እንዲሆኑ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም