አዲስ አበባ፡– የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብሩ ሴቶች በተሰማሩበት መስክ ምን ያህል ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ማሳያ ነው ሲል የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ በ2016 የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂና የ12ኛ ክፍል ሴት ተማሪዎች እውቅና ሽልማት በትናንትናው እለት አበርክቷል።
በወቅቱ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ወይንእሸት ዘሪሁን እንደገለጹት፤ የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብሩ ዋና ዓላማ ሴቶች በተሰማሩበት ዘርፍ ምን ያህል ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ለማሳየትና ታዳጊ ሴቶችም ከእነዚህ ውጤታማ ተማሪዎች ትምህርት እንዲወስዱ የሚያስችል ነው።
ቢሮው የሴቶችን ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል። ከዚህ ውስጥ ዋነኛው የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ማሳደግ ነው ብለዋል።
ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ ያለውን የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ እንዲጨምር የተለያዩ ስራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።
የሚከናወኑት ስራዎች ሴቷን ትምህርት ላይ ማሳተፍ ብቻም ሳይሆን ከወንዱ ጋር ተወዳድራ የተሻለ ውጤት ይዛ እንድትወጣም የሚያደርጋት መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድም ሴቶች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ስራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪ ሊሆኑ ይገባል ያሉት ወይዘሮ ወይንእሸት፤ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችም እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደው በስራ ገበታቸው ላይ ውጤታማ መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ የሴቶች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዝናሽ ከተማ በበኩላቸው፤ የእውቅና ሽልማቱ መርሃ ግብሩ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ መካሄዱን ገልጿል።
ተመራቂ ተማሪዎች ጠንካራ ስራ ፈጣሪዎች በመሆን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ፤ በቀጣይ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምትገቡ ተማሪዎችም ጠንክራችሁ በማጥናት ብቁ ዜጋ ለመሆን መጣር ይኖርባችኋል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የእውቅናና ሽልማቱ ለ30 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ሴት ተማሪዎችና ለ50 ሴት ተመራቂ ተማሪዎች ተበርክቷል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም