– በሩብ ዓመቱ ከሬሚታንስ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ተገኘ
አዲስ አበባ:- ዳያስፖራውን የሀብት ምንጭ ብቻ አድርጎ የመመልከት ሁኔታን በመሰረቱ የሚቀይር፣ በሀገሩ ጉዳይ የበለጠ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ በማድረግ ሚዛኑን የሚያስጠብቅ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖሊሲን ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።
በ2013 እ.አ.አ በወጣው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖሊሲ ላይ በወሎ ዩኒቨርሲቲ መሪነት ጅማ፣ ጅግጅጋ እና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳታፊ ሆነው ባደረጉትት ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ውይይት ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንዳሉት፤ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ የዳያስፖራውን ተጠቃሚነት ለማስፈን ፖሊሲውን ማሻሻል አስፈልጓል። በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖሊሲን ለማሻሻል የመጨረሻ ምእራፍ ላይ ደርሷል፡፡
አሁን በስራ ላይ የሚገኘው ፖሊሲ ግዴታ የሚጥል መሆኑን በመጥቀስ፤ ፖሊሲው መብትን በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲቃኝ በማድረግ ማሻሻያ እንደሚደረግበት ጠቁመዋል፡፡ ፖሊሲው ለዜጎች መብት የሚቆረቆር፣ ሚዛንን የሚያስጠብቅ መብትንም የሚያከብር ይደረጋል ብለዋል አምባሳደር ፍጹም፡፡
ፖሊሲው ሲጠና አናውቀውም የሚሉ የዘርፉ አካላት መኖራቸው፣ በኢኮኖሚ ዘርፍ የተደረገው ማሻሻያ፣ ዲጂታላይዜሽን መምጣቱ ፖሊሲውን ለማሻሻል ገፊ ምክንያት ከሆኑት መካከል እንደሚካተቱ አምባሳደር ፍጹም ጠቅሰዋል።
የተለያዩ ለውጦች መጥተዋል፤ በርካታ ኢትዮጵያ ውያን ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን፣ በሀገራቸው በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ንቁ ተሳትፎ ማድረ ጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ወቅቱን በዋጀ መንገድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መምጣቱ፣ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየተደረገ ያለው ሽግግር እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት በፖሊሲው ትግበራ ሂደት አዲስ ቅኝት ያመጡ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ፖሊሲው እንዲሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በጥናቱ መለየቱንም ጠቁመዋል።
የጥናት ቡድኑ አባል ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ፖሊሲውን ማእከል በማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ፖሊሲው ሲዘጋጅ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንጂ አሁናዊ አዝማሚያዎችን ያገናዘበ እንዳልነበረ ነው ያስታወሱት፡፡
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን፣ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ጨምሮ በየጊዜው ተግባራዊ የተደረጉ ኢኮኖሚያዊ እቅዶችን ባገናዘበ መልኩ የተዘጋጀ እንዳልነበረ እና በየወቅቱ ማሻሻያ የተደረገበት አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሰነዱ በዕድሜው መርዘም ምክንያት በየጊዜው እየወጡ ያሉትን ሀገራዊ እቅዶች አለማካተቱም በትግበራ ሂደት እንደክፍተት ማጋጠሙም ተነስቷል።
በሩብ ዓመቱ ከሬሚታንስ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን፣ በዚህ ሂደት ከቀጠለ በዓመቱ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ፤ ነገር ግን ከዚህም በላይ ለማግኘት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም