ኢትዮጵያ 20ኛውን የሥራ ድርጅት ጉባዔ ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፡ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ግንቦት ወር ላይ 20ኛውን አህጉር አቀፍ ሥራ ድርጅት ጉባዔ እንደምታስተናግድ ተገለጸ፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው 20ኛው የሥራ ድርጅት ጉባኤ ከግንቦት 11 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም የአፍሪካ መዲና እና የብልጽግና ማሳያ እየሆነች በመጣችው አዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ጉባኤው በየሁለት ዓመቱ በተለያዩ ሀገራት የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የዘንድሮውን ጉባኤ አዘጋጇ ኢትዮጵያም ዝግጅት እያደረገች መሆኗን አስታውቀዋል።ጉባዔው የኮንስትራክሽን፣ የመሠረተ ልማትና ሌሎች ኢንቨስተሮች የሚሳተፉበት በመሆኑ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሀገራት እንደ የመኪና መንገድ፣ የባቡር ሀዲድ፣ አየር መንገድ፣ ግድብ፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የከተማና የገጠር መሰረተ ልማት ዝርጋታ ባሉ ትላልቅ መሰረተ ልማቶች ላይ ተሞክሮ የሚቀስሙበትና ለሥራ እድል ፈጠራም በጉባዔው አስቻይ ሁኔታዎችን የሚያመላክቱበት እንደሚሆንም ነው የጠቀሱት፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ጉባኤው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወጣጡ የፖሊሲ አማካሪዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ተወካዮችና ባለ ድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ነው።ሰፊ የሥራ እድል ሊፈጥሩ በሚችሉ የመሰረተ ልማት ክንውኖች ላይ ሰፊ ውይይቶች ይደረጋሉ።ይህም ለሥራ እድል ፈጠራ ትልቅ ሚና ያለው ነው።ጉባኤው የተሳካ እንዲሆንም 15 የመንግሥት ተቋማት ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከመሆኗ ባሻገር የአፍሪካዊያን መቀመጫ እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ማዕከል በመሆን የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባዔዎችን እያስተናገደች መሆኗን ጠቅሰዋል።ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን የማስተናገድ ሚናዋ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የዓለም የሥራ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ በበኩላቸው፤ ጉባዔው ለኢትዮጵያ በርካታ እድሎችን እንደሚሰጥ ገልጸዋል። የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ጨምሮ የኢትዮጵያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ስኬት ተሞክሮ ለሌሎች የማሳየት ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።ኢትዮጵያ በወጣቶች የልማት ፕሮግራሞች አጠቃቀም ላይ ያላትን የረዥም ጊዜ ልምድ እንደምታካፍልም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ባህላዊ ቅርሶችን ፣ተፈጥሮአዊ ውበቶችን እና ጉልህ ታሪካዊ አሻራዎችን ያቀፈች ሀገር በመሆኗ ከጉባዔው ጎን ለጎንም እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች የመጎብኘት እድሎች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

ጉባዔውን በዋናነት የኢትዮጵያ መንግሥትና የዓለም የሥራ ድርጅት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር የሚያዘጋጁት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በኩል የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሚያስተባብሩት መሆኑ ታውቋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You