የነፃ አገልግሎቱ ተደራሽነት

መስከረም(ስሟ የተቀየረ) ትባላለች ደቡብ ወሎ ውስጥ ከሚገኝ ገጠራማ ስፍራ ከመጣች ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ እንደሆናት ትገልፃለች። አካባቢው አሁንም ድረስ ያለእድሜ ጋብቻ የሚፈፀምበት በመሆኑ እርሷም በአስራ ሰባት ዓመቷ ትምህርቷን አቋርጣ ተድራ እንደነበር ትጠቅሳለች። ነገር ግን ያገባት ሰው በእድሜ ከእርሷ ብዙም ያልራቀና ብስለት የሌለው በመሆኑ እንዲሁም በመጠጥ ሱስ ተገፋፍቶ የተለያዩ ጥቃቶችን ያደርስባት ስለነበር በወቅቱ ከወላጅ እናቷ ጋር በመመካከር ልጅ ላለመውለድ እንደወሰነች ትናገራለች።

ስለሆነም ለሶስት ወር የሚያገለግለውን መርፌ በአካባቢዋ ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ እየሄደች በየጊዜው ትወጋ እንደነበር አስታውሳ፤ ለዚህ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ለተወሰነ ጊዜ ስልሳ ብር ከዛ በኋላ ደግሞ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የቆየ ትዳሯን ፈትታ ወደ አዲስ አበባ እስከመጣችበት ጊዜ ደግሞ አንድ መቶ ብር እየከፈለች አገልግሎቱን ስታገኝ እንደነበር ትገልፃለች። አገልግሎቱን ካገኘች በኋላም መከላከያው ከመቼ እስከመቼ እንደሚያገለግል ከሚገልፅ ወረቀት ውጪ ምንም አይነት ደረሰኝ እንደማትቀበል ታስረዳለች።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጤና ዘርፍ የቤተሰብ እቅድ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ገነት ድረስ በበኩላቸው እንዲህ አይነት መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው፤ ለአገልግሎቱ ክፍያ የሚቀበል የጤና ተቋም ካለ ግን እንደሚቀጣ ይገልፃሉ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልል ወደ ዞን ከዞን ወደ ወረዳ እያለ በአገልግሎቱ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮች ላይ ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንዳሉትም ያስረዳሉ።

መድኃኒቱ በነፃ እስከቀረበ ድረስ የሚሸጥበት ምክንያት የለም የሚሉት ባለሙያዋ፤ የዚህ አይነቱ አሰራር ሪፖርት ካለ ግን እርምጃ እንደሚወሰድበት ይገልፃሉ። መንግሥት ለእነዚህ መድኃኒቶች በዓመት እስከ አርባ ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጣም ጠቁመዋል። በመድኃኒት አቅርቦቱ ላይ ይህን ያክል ገንዘብ ወጪ የሚደረገው አገልግሎቱን በነፃ ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነም ያብራራሉ።

በዓለም ላይ ከሚከሰቱ እርግዝናዎች 61 በመቶው በውርጃ ይጠናቀቃሉ ያሉት ባለሙያዋ፤ የእንዲህ ያሉ ጥናቶች ትኩረት ካደጉት ሀገራት ይልቅ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ላይ መሆኑን ያስረዳሉ። በኢትዮጵያም ከህክምና ተደራሽነት ችግር፣ ከግንዛቤ እጥረት፣ ከሴቶች አለመማር፣ ከያለዕድሜ ጋብቻና ከሌሎችም ችግሮች አንፃር ያልተፈለገ እርግዝናና ውርጃ መጠን ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ያነሳሉ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከእርግዝና በፊት ጀምሮ እስከ ከወሊድ በኋላ እስካለው አንድ ሺህ ቀናት ድረስ ያለው አገልግሎት ላይ የሚሰራ ራሱን የቻለ ዘርፍ እንዳለውም ይገልፃሉ። ስለሆነም የአገልግሎት ተደራሽነቱን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዛ ባሻገር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት ላይ በተለይ ሚዲያው መስራት እንዳለበት ገልጸው፤ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮችን እስከ ቀበሌ ድረስ በማዘጋጀት የጎሳ መሪዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን እንዲሁም ለህብረተሰቡ ወሳኝ የሚባሉ አካላትን በማሳተፍ ውይይት እያደረጉ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። የሕዝብ ተወካዮች አባላትም በተመረጡባቸው አካባቢዎች የቤተሰብ እቅድ ሀገራዊ ጉዳይ በመሆኑ ድጋፍ በማድረግና በጀት በማስመደብ እንዲሰሩ ለማድረግ የተለያዩ መድረኮች እየፈጠሩ እንደሚገኝ ያብራራሉ።

የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በበኩላቸው፤ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለመጨመር ከመገናኛ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደእርሳቸው ገለፃ በተለይ የሚዲያ ባለሙያዎች ግንዛቤ በመፍጠርና የአገልግሎት ተደራሽነቱን በመጨመር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በስነተዋልዶና በሌሎች የጤና ጉዳዮች ዙሪያ በየጊዜው የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You