በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ፤ ከውጪ የሚገቡ 90 ምርቶችን በሀገር ውስጥ ተክቶ ለማምረት ንቅናቄ ተፈጥሮ እየተሰራ ነው። ሆኖም በዘርፉ በርካታ ማነቆዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡
አንድ የመካከለኛ ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሽ ወደ ምርት ለመግባት በቀላሉ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ እንደሚፈጅበት ይነገራል፡፡ በኢንዱስትሪው ያሉ ማነቆዎች ውስብስብ በመሆናቸው የዘርፉ ተዋንያን ከማምረት ይልቅ ወደ አገልግሎት መግባትን ይመርጣሉ፡፡ በኢንዱስትሪው የሚታዩ የፋይንንስ፤ የመሰረተ ልማት፤ የማምረቻ ቦታ እጥረት፤ የሰለጠነ የኃይል አቅርቦት ካልተፈታ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አዳጋች ይሆናል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች እየገጠማቸው ያለው ማነቆ ምንድን ነው? ያሉትን ችግሮችስ መፍቻ መንገዶች ምንድን ናቸው? ሲል ኢፕድ ጠይቋል።
በአማራ ክልል የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሱሌማን ኢብራሂም እንደሚሉት፤ የማኑፋክቸሪንግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ። ካልተሟሉ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚባለው ነገር የማይታሰብ ነው።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርቶ ለማምረት የፋይናንስና የማምረቻ ቦታ እጥረት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፤ የመሰረተ ልማት ችግር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ምርትን እራሱ መንግሥት ያለመጠቀም ማነቆዎች አሉ ይላሉ።
አምራቾች ገንዘብ እያላቸው ወደ አገልግሎት ዘርፍ የሚገቡበት በርካታ ምክንያት አላቸው የሚሉት አቶ ሱሌማን፤ አምራች ዘርፉ በአጀማመር ወቅት በርካታ ወጪዎች እንዲሁም ጊዜ እንደሚጠይቅ ያስረዳሉ።
በዚህም ምክንያት የዘርፉ ተዋናዮች ወይም ዘርፉን መቀላቀል የሚፈልጉ አካላት ወደ ማምረት ከመግባት ይልቅ ወደ አገልግሎት መግባት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ይላሉ።
አምራቾች እንደምንም ተፍጨርጭረው ማሽን አምጥተው ስራ ይጀምራሉ፤ ባለው የሰለጠነ የሰው ኃይል፤ በሀይል አቅርቦት፤ በመሰረተ ልማት ችግሮች እየተዳከሙ ይሄዳሉ፤ ምርትና ምርታማነትም እየቀነሰ ይሄዳል ሲሉ ይገልጻሉ።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ፈትቶ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በአካባቢው ያለው አስተዳደር ያለውን የማምረቻ ቦታ እጥረት መፍታት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግርን መቅረፍ፤ ባንኮች ያለውን የፋይናንስ ችግር ማስወገድ፤ ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ አሰራር መዘርጋት ተገቢ መሆኑን አፅንዖት ይሰጣሉ። ከቴክኒክና ሙያ የሰለጠነ የሰው ኃይል በመቅጠር የሰው ኃይል እጥረትን መፍታት እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
ማኑፋክቸሪንጉን አበረታትቶ በሚፈለገው ልክ ለማሳደግ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከውጪ የሚያስመጡትን ምርት ትተው በሀገር ውስጥ የሚመረትን ምርት መግዛት እንዳለባቸውም ነው የሚያስገነዝቡት።
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የሀገርን ምርት መጠቀም መመሪያ ሆኖ ሊወርድ እንደሚገባ በመጠቆም፤ በኢትዮጵያ ታምርትና የኢትዮጵያን ይግዙ ንቅናቄ የመንግሥት ተቋማት የሀገር ውስጥ ምርትን ገዝተው በማሳየት ለዜጎች ግንዛቤ መፍጠር እንደሚኖርባቸው ነው የተናገሩት።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የፋይናንስና የማምረቻ ቦታ እጥረት፤ የመሰረተ ልማት፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል፤ የኃይል አቅርቦት ችግሮች ይስተዋሉበታል የሚሉት ደግሞ የኦሮሚያ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አበበ በንቲ ናቸው።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተስተዋሉ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት አስፈላጊ ነው ይላሉ አቶ አበበ።
መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ ያለው ስራ ጥሩ መሆኑን የሚያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ መንግሥት ተግባራዊ እያደረጋቸው የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እስከ ታች ወርደው ተግባራዊ መደረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ ይጠቅሳሉ።
ሠራተኛን አሰልጥኖ ወደ ኢንዱስትሪው የማምጣት፣ ከባንኮች፣ ከተለያዩ ልማት ድርጅቶችና ከመንግሥት መዋቅር ተሳስሮ የመሥራት ጉዳይ ላይ ክፍተት መኖሩን የሚያነሱት አቶ አበበ፤ ማኑፋክቸሪንጉን ለማሳደግ፣ ማነቆዎችንም ለመፍታት በቅንጅት መስራት ተገቢ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
የሠራተኛውን ደህንነት መጠበቅ፣ የመሰረተ ልማት ችግሮችን፣ የፋይናንስ እጥረትን መፍታት ከተቻለ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ውጤት የሚያመጣ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በበኩላቸው፤ ኢንዱስትሪው ውስብስብ ችግር ያሉበት ዘርፍ መሆኑን ያነሳሉ።
በዘርፉ የሚታየውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ለማኑፋክቸሪንግ የሚሰጠው ብድር እንዲጨምር የማድረግ፤ ልማት ባንክንና የተለያዩ የብድር ዘዴዎችን በመክፈት 80 በመቶ ብድር የማቅረብና ብድራቸውን ከፍለው ሲጨርሱ ቦታውን እንዲወስዱ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ያብራራሉ።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ያለውን የማምረቻ ቦታ እጥረት ለመፍታት የማኑፋክቸሪንግ ክላስተሮችን የማስፋት ስራ የመስራት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሀገር ውስጥ አምራቾች ገብተው እንዲሳተፉ የማድረግ ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ያስረዳሉ።
ክልሎች የራሳቸውን ክላስተር በመገንባት ኢንዱስትሪዎች በክላስተር ገብተው እንዲሰሩ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ በመጠቆም፤ በዚህም አሰራር በርካታ ኢንዱስትሪዎች ለምተዋል፤ ምርትም እያመረቱ ይገኛሉ ይላሉ።
በተጨማሪም የማምረቻ ቦታ እጥረትን ለመፍታት ባለሀብቶች ሼዶችን እየሰሩ ለአምራቾች እንዲያከራዩ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
መንግሥት የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህል እንዲዳብር ምርቶችን ገዝቶ ከመጠቀም ባሻገር ለሀገር ውስጥ አምራቾች ልዩ የግዥ ሥርዓት የመፍጠር፣ እንዲሸጡ የማድረግ፣ የመንግሥት ተቋማትም ገዝተው እንዲጠቀሙ የማበረታታት ስራ እየሰራ ይገኛል ሲሉ ይናገራሉ።
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት ጥራት ያለው ምርት በማምረት ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ እየተሰራ ያለው ስራም ውጤት እያስገኘ ነው ሲሉ ነው ያብራሩት።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም